>
5:13 pm - Friday April 19, 7816

የሞትም ደረጃ አለው... በሲኖ ትራክ ጨፈለቁን...!!! (አብመድ)

የሞትም ደረጃ አለው… በሲኖ ትራክ ጨፈለቁን…!!!

አብመድ 

* ለወታደር በተኩስ መካከል መሞት ስራ፣ በጥይት ተመትቶ ማለፍ ክብር፣ በከባድ መሳሪያ መሰዋት አጋጣሚ ነው፡፡ ወታደር ሞትን አዝሎ ይዞራል፤ ከሌላው በተለየም ህይዎትን በኮንትራት ይኖራል፡፡ 
ትህነግ በሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመቸውን ክህደት በዝርዝር ለሰማ እና ላየ ግን ሰው ሆኖ መፈጠርን የሚያስጠላ፣ አለመፈጠርን የሚያስመኝ፣ የትውልድን አንገት የሚያስደፋ እና አሳፋሪ ክህደት ነው፡፡ 
አምሳ አለቃ ደረጀ አንበሳ በሰሜን ዕዝ የጥገና ክፍል አባል ነው፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከጠዋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ የአካባቢውን አርሶ አደር ማሽላ ለመቁረጥ መውጣታቸውን የሚናገረው አምሳ አለቃ ደረጀ የተመለሱት ምሽት 11 ስዓት አካባቢ እንደነበርም ነግሮናል፡፡ በስራ የዋለ እና የደከመ አካላቸውን ባሳረፉበት ሌሊትም በህገ ወጡ የትህነግ ቡድን አፈና ተፈፀመባቸው፡፡
ከአንዱ የማጎሪያ ጣቢያ ወደሌላው የማጎሪያ ጣቢያ ሲያንከራትቷቸው መሰንበታቸውን የሚናገረው አምሳ አለቃ ደረጀ በመጨረሻም አስነዋሪ ድርጊት ሊፈፅሙበት ወደአቀዱበት ቦታ 40 ኪሎ ሜትር በእግር እንዲጓዙ እንዳደረጓቸው ይናገራል፡፡
ህፃን ያዘሉ ሴቶች፣ ጓዝ የተሸከሙ ወታደሮች እና ህጻናት ያሉበት የነአምሳ አለቃ ደረጀ ታጋቾች ቡድን ቁጥራቸው 1ሺህ 200 ነው፡፡ አጋቾቹ በግራ እና በቀኝ መሳሪያ አቀባብለው ታጋቾቹን ከአስፓልት እንዳይወጡ ትዕዛዝ እየሰጡ እና እያስፈራሩ ወደፊት እንዲቀጥሉ አደረጉን ይላል፡፡
ቀኑ እየመሸ ሲመጣም መንገዳቸውን ያላቆሙት ታጋቾቹ መብራቱን ያጠፋ ሴኖ ትራክ ከኋላቸው መጥቶ ታሪክ የማይረሳው እና ትውልድ ይቅር የማይለው ድርጊት ፈፀሙባቸው፡፡ አንደበቱ እየተሳሰረ እና ዐይኑ አምባ እያቀረረ ድርጊቱን የሚገልፀው አምሳ አለቃ ደረጀ ሴኖ ትራክ ያገኘውን ተጓዥ እየጨፈለቀ ከአምሳ አለቃ ደረጀ ላይ ሲደርስ እግሩን ሰብሮ ወደገደል ገፈትሮ ጣለው፡፡
በወደቀበት ያደረው አምሳ አለቃ ደረጀ ክፉኛ የተጎዱ ጓዶቹን ጣር እና ጩኽት እየሰማ ሊረዳቸው ባለመቻሉ ህይዎታቸው ማለፉን በእምባ ሲገልፅ ያሳዝናል፡፡
ሌላው ያነጋገርነው እና ከሞት ያመለጠው አምሳ አለቃ ወንድማገኝ ወልደ ገበርኤል ለህወሃት አፋኝ ቡድን ትጥቅ ከመፍታታቸው በፊት ለሦስት ቀን ያለምግብ እና ውሃ መዋጋታቸውን ነግሮናል፡፡ በሦስተኛው ቀን የብርጌዷ አዛዥ ኮሎኔል ኃይላይ ገብሩ ከውጭ ተልዕኮ ተቀብሎ እና ቄስ ሆኖ መምጣቱን ይናገራል፡፡
መጀመሪያ ላይ የሃይማኖት አባት የመጡ መስሎን ነበር የሚለው አምሳ አለቃ ወንድማገኝ እየቆየ ሲሄድ እና በደንብ ተጠግተው ሲያዩት ግን የብርጌዳቸው አዛዥ መሆኑን አረጋገጥን ይላል፡፡ በመጨረሻም ግቢያቸው በአካባቢው ሚሊሻ እና በትግራይ ልዩ ኃይል በከባድ መሳሪያ መከበቡን ሲያረጋግጡ ትጥቃቸውን ፈቱ፡፡
ትጥቅ ከፈታን በኋላ የነበረው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ፍፁም ከባድ ነበር የሚለው አምሳ አለቃ ወንድማገኝ ዓቢ አዲ ታስረው እያለ ዓለም አቀፍ የቀይመስቀል ማህበር ይቀበላችኋል ተባሉ፡፡ ነገር ግን እሱ ቀርቶ ወደትግራይ መከላከያ ኃይል መቀላቀል፣ ትግራይ ውስጥ ሲቪል ሆነው መቀመጥ ወይም ወደየአካባቢያቸው መሄድን ምርጫ አድርገው እንዳቀረቡላቸው እና ሁሉም ወደአካባቢያችን እንሄዳለን የሚል ምላሽ እንደሰጧቸውም ነግሮናል፡፡ በታጋቾቹ ምርጫ የተበሳጩት የትህነግ ህገ ወጥ ቡድን በጠዋት መጥተው ውጡ አሏቸው፤ አንወጣም ሲሉ ከስዓት በኋላ ሃይል ጨምረው መጥተው አስወጧቸው፡፡ ከ1 ሺህ 300 በላይ ታጋቾች ረጂም መንገድ በምሽት እንዲሄዱ ትዕዛዝ ተሰጣቸው፡፡
ነገር ግን ይላል አምሳ አለቃ ወንድማገኝ ከተጠና አካባቢ ሲደርሱ ፊት ለፊታቸው ተኩስ ተከፈተ፡፡ ከተኩሱ ለመዳን አስፓልት ላይ የተኙት እነአምሳ አለቃ ወንድማገኝ ባላሰቡት መልኩ ሴኖ ትረክ መጥቶ እየጨፈለቃቸው በላያቸው ላይ አለፈ፡፡
መሰል ዘግናኝ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በወገን ላይ ስለመፈፀሙ ሰምቸ አላውቅም የሚለው አምሳ አለቃ ወንድማገኝ ጥቃት መፈፀም ቢፈልጉ እንኳን በጥይት ቢመቱን ክብር ነበር ይላል፡፡ ከዚያ አሳዛኝ የሞት ድግስ የተረፉት የመከላከያ አባላት ዛሬ ህክምና ውስጥ ናቸው፡፡
ስለመትረፋቸው ሳይሆን ድርጊቱ ስለመፈፀሙ ያዝናሉ፡፡
#አብመድ
Filed in: Amharic