>
5:21 pm - Sunday July 20, 8064

እኔና ጓድ ፍቅረ ሥላሴ (ገነት አየለ)

እኔና ጓድ ፍቅረ ሥላሴ

 

(ገነት አየለ)

ሥልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ አላውቃቸውም። ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘኋቸው እስረኛ ሆነው ነው። ኮሎኔል መንግሥቱን ዚምባብዌ ሄጄ ካገኘኋቸው በኋላ አብረዋቸው የነበሩትን ጓዶቻቸውን ቃለ መጠይቅ ሳደርግ ፈቃደኛ ሆነው ካነጋገሩኝ የደርግ አባላት አንዱ እሳቸው ነበሩ። በጥያቄያቸው መሠረት ስማቸውን ሳልጠቅስ ጓድ ቁጥር… በማለት መለያ ሰጥቼ ምስክርነታቸውን ለታሪክ እንዲቀር አድርገዋል። በዚህም እሳቸውንና ጓዶቻቸውን አመሰግናቸዋለሁ። ከዚያ በኋላ ከእስር ተፈተው ሠላማዊ ኑሯቸውን ሲመሩ አልፎ አልፎ እንገናኝ ነበር። ባገኘኋቸው ቁጥር ረጋ ያለ ባሕሪያቸው፣ ትህትናቸውንና ቅንነታቸውን ለማየት ችያለሁ።

በተፈጥሮ ካላቸው ቁጥብነታቸው ጋር ብዙ ማውራት ባይፈልጉም ብዙ የሚያውቁ መሆናቸውን ተረድቻለሁ። ከሁሉ በላይ ግን ልቤን የነካውን ነገር ላካፍላችሁ። ከአንድ ወር ተኩል በፊት በትንሽ ነገር የተቀያየሙ ጓደኛሞች መኖራቸውን ሰማሁና በኔ አቅም ደፍሬ ሰዎቹን ለማስታረቅ መሞከር ፈራሁ። ካላቸው ተቀባይነት አንፃር ጓድ ፍቅረ ሥላሴ እንደሚረዱኝ ብተማመንም ትንሽ የጤና ችግር እንዳለባቸው ስለማውቅ ላስቸግራቸው አልፈለግሁም። እሳቸው ግን ያለ አንዳች ማመንታት በቀናነት የማስታረቁን ሂደት እንደሚመሩ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀው እቤቴ መጡ። እያመማቸው በተከታታይ ሽምግልናውን ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ሆነው ነገሩን አሳክተው ተመራርቀን ተለያየን።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ሆስፒታል መግባታቸውን ስሰማ ታመው እንዳስቸገርኳቸው እሳቸው ግን ለመልካሙ ሥራ ስቃያቸውን ችለው ፈገግታ ሳይለያቸው መካከላችን እንደተገኙ ሳውቅ አዘንኩ። ደግነታቸውን አደነቅሁ። የኔ ነገር መጠየቅ እወድ የለ ? ጠጋ ብዬ ስለወቅታዊው ሁኔታ ጠያየቅኋቸው። የሚሰማቸውን እየነገሩኝ ትንሽ ቆየንና እንዴት ነው አሁን ተሽሎዎታል አደል? አልኳቸው። “ምን ከእንግዲህ ወዲያ የኢትዮጵያን ጠላቶች መጨረሻ አየን አይደል እንዴ ? ” አሉኝ በፈገግታ። ይቺን ይዤያለሁ። ነፍስዎን ይማርልን ጓድ ፍቅረ ሥላሴ።

 

ምንጭ

Classy Entertainment
Filed in: Amharic