>

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ መግለጫ...!!!

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ መግለጫ…!!!


 

በቤንሻንጉል ጉሙዝ በአማራና በአገው ሕዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት በአስቸኳይ ይቆም ዘንድ ጥሪ ያደርጋል!
***
ሕዝባችንን ለበርካታ አስርተ ዓመታት በጠላትነት ፈርጆ ዘርፈ ብዙ ስርዓታዊና መዋቅራዊ ግፍ ሲፈፅምበትና ሲያስፈፅምበት የቆየውን የትሕነግ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ለማስወገድ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጓል፡፡ ትህነግ በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ክህደትና አረመኔያዊ ግፍ በመፈፀም አገሪቱን ለመበታተን ያደረገውን ሙከራ ለማክሸፍ ሕዝባችን ከፍተኛ ትግል አድርጓል፡፡
ይሁን እንጂ የሕዝባችንን ቅን ልቦናና ታግሽነት እንዲሁም የከፈለውን መስዋዕትነት ዋጋ የሚያሳጡና ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትኅ የሚኖርባትን አገር ለመገንባት ያነገበዉን ተስፋ ለማምከን እኩያን በጥምረት የተቀናጀ ጥቃት ከፍተውበታል፡፡
ሕዝባችንም ሲፈጸሙበት ከቆዩት ሰፊ ዘር-ተኮር ጥቃቶች ገና ባላገገመበት ሁኔታ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ በአማራ-ጠልነት መንፈስ ስልታዊ የዘር ማፅዳትና የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴዎች በአዲስ መልክ ተጠናክረዉ እየታዩ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግሥት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍና ትሕነግን ከሞት መንጋጋ ፈልቅቆ ለማውጣት፤ ይህ ካልተሳካም የአፍራሽነትና የጥላቻ አጀንዳውን ለማስቀጠል በቅንጅት የተሰለፉ ኃይሎች ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የሰብዓዊ ቀውስ ማዕከል አድርገውታል፡፡ በዚህ ጥቃት እየተሳተፉ ያሉ ጽንፈኛ የጥላቻ ኃይሎች በመካከላቸው መሰረታዊ የሆኑ የግብ ልዩነቶች ቢኖሯቸዉም በአማራና በአገዉ ሕዝባችን ላይ ያነገቡት የጥላቻና የጥፋት ፖለቲካ በጋራ እንዳሰሰለፋቸው ይታወቃል፡፡
በሕዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል መነሻ ምክንያቶችን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም፡-
1/ ትሕነግ በሕዝባችን ላይ በቀጥታ እንዲሁም በትርክት፣ በፖሊሲ፣ በመዋቅር፣ በሎጅስቲክስና በገንዘብ እገዛ እያደረገ ሲያስፈጽም መቆየቱ፤
2/ መነሻዉ ጽንፈኞች በሕዝባችን ላይ ያላቸው ጥላቻ ሲሆን በዋናነት ሕዝቡን ማኅበራዊ ረፍት ለመንሳት የታለመ መሆኑን፤
3/ ትሕነግ በጥላቻ፣ በአግላይነትና በአምባገነንነት የማዕከላዊ መንግስት ስልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያን በኃይል ወደ ትግራይ በማካለል፤ ሌሎች የአማራ አካባቢዎችን ደግሞ በሕገ-ወጥና በማንአለብኝነት ወደ ተለያዩ ክልሎች እንዳካተታቸው ይታወቃል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ውስጥ የሚኖረው ሕዝባችንም በሁሉም ዘርፎች የሚገለጹ ሰብዓዊ መብቶቹን ተገፎ፤ በተለይም አጠቃላይ ኅልውናው አደጋ ላይ ወድቆ መቆየቱንና በመተከል የሚኖረው የአማራና አገው ሕዝብ ወደ ነባር አማራዊ አስተዳደር ለመካለል ሕጋዊ የይገባኛል ጥያቄ አቅርቦ እንደሚገኝና ይሄን የመብት ጥያቄ ለማዳፈን ሰፊና የተቀናጀ ሴራ እየተተገበረ መሆኑን፤
4/ እስካሁን በሕዝባችን ላይ በርካታ ተደራራቢ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀሎች የተፈጸሙ ሲሆን ለመከላከልም ይሁን ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል አገራዊና መንግስታዊ ትጋት አለመኖሩ፤
5/ ዝቅተኛ የሆነውን ሕግ የማስከበርና ዜጎችን ከጥቃት የመከላከል መንግስታዊ ግዴታን ካለመወጣት ባለፈ በመንግስት መዋቅር ውስጥ በየእርከኑ የኃላፊነት ቦታዎችን የያዙ አመራሮችና ባለስልጣናት ጥቃት ለሚሰነዝሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ከለላ በመስጠትና በቀጥታ በመሳተፍ ጭምር ከፍተኛ የአፍራሽነት ድርሻ እንዳለቸው፤
6/ ዛሬም የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመሆን የአገሩን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ መስዋዕትነት ከፍሎ ያገኘውን ድል ለመንጠቅ፣ አመድ አፋሽ ለማድረግና ሕዝባችንን በጠላትነት ፈርጆ ለመቀጠል የሚፈልጉ ኃይሎች ከሚከተሉት የሕዝብ-አገት ፖለቲካ (hostage politics) ያልታቀቡ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመከላከያ ሰራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይል፣ በአማራ ሚኒሻና በሕዝባችን ራስን የመከላከልና አገርን የመታደግ ዘመቻ የተንበረከከው የትሕነግ ኃይል ታሪካዊና ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዳለበት የሚታወቅ ቢሆንም ከሞት በኃላ ቋሚ ማሳበቢያ ሊሆን እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል፡፡
በትሕነግ ምትክ አይዞህ ባይ ያገኘው የቤኒሻንጉል ክልላዊ መዋቅር በአማራና አገው ሕዝባችን ላይ ዘግናኝና አረመኔያዊ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ አስቻይ መድረክ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ የሚካድ አይደለም፡፡ ኮማንድ ፖስት በመመስረቱ ሊሻሻል ይችላል ብለን የጠበቅነው ዘር ተኮር ጥቃት ይልቁንም እየተባባሰና በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጭምር ጉዳት እየደረሰ ይገኛል፡፡
አብን ባለፉት ሁለት ከመንፈቅ ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የተሰራውን ርዕዮታዊ፣ሕጋዊና መዋቅራዊ የጥላቻና የጭቆና ሥርዓት ከናካቴው ለማስወገድና ሕዝባችን ኅልውናው ተከብሮ እንዲኖር ለማስቻል ቆራጥ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አብን ዛሬም የትሕነግን ውርስ ለማስቀጠል የሚመኙ ኃይሎች ከእንግዲህ ሕዝባችን በገዛ ቀየው ተሳዳጅና ተገዳይ እንደማይሆን እንዲገነዘቡ ለማድረግና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ትግል እንደሚያደርግ ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡
በአማራዊ ማንነት ላይ ያነጣጠረዉን ጥቃት ለመከላከልና በዘላቂነት ለመቀልበስ መላዉ የአማራ ሕዝብ፤ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ሁሉም የአማራ የፖለቲካ ድርጅቶች የማያወላዳ የጋራ አቋም መውሰድና ተፈጻሚነት ያለው የፖለቲካና የደኅንነት እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
ሕዝባችን ኅልዉናውን ለማስቀጠል ከባድ ትግል እያደረገ ባለበት ወቅት፤ በልዩ ሁኔታ የትሕነግን ኃይል እየተፋለመና በየእርምጃው የአማራ ወገኖቻችን በጅምላ ተጨፍጭፈዉ እየተቀበሩ ባለበት ሁኔታ መንግስታዊ ስልጣንን፤ ኃሳብን በነጻነት የመግልጽ መብትንና የብሔር ማንነትን ሽፋንና ከለላ በማድረግ አማራ-ጠልነትን ለማንበርና ለማስቀጠል በርካታ ጽንፈኞች እየተረባረቡ መሆኑን በመለየት በሁሉም ዘርፎች ተገቢ፣ የሚመጥን፣ ፈጣንና የማያወላዳ ተግባራዊ ስምሪት መውሰድና መፈጸምን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ አብን ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁነቱን ያረጋግጣል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መስተዳድር የሰላምና ደኅንነት ተቋም ወደዘር ማጥፋት እርከን ተሸጋግሮ የቀጠለውን ሰፊ ጥቃት ለመከላከል የአቅም እጥረት ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም እንደሌለው ፍንትው ብሎ የተገለጠ እውነታ በመሆኑ የፌዴራል መንግስትና የአማራ ክልል መንግስት በጋራ ሕዝቡን ለመከላከል የሚያስችል አስቸኳይ አቋም እንዲወስዱ አብን ጥሪ ያስተላልፋል ፡፡
በመንግሥት በኩል የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር ቁርጠኝነት እስካለ ድረስ የአማራ ሕዝብ  ከጎኑ እንደሚቆምና ይህ ካልሆነ ግን ሕዝባችን ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብቱን በመጠቀም ኅልዉናውን ለመታደግ፣ የጥፋት ኃይሎችን ለመመከት ብሎም ለሕግ ለማቅረብ በጽኑ እንደሚታገል እናሳውቃለን፡፡
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
አዲስ አበባ፥ ሸዋ፤ ኢትዮጵያ!
ታኅሣሥ 6 ቀን 2013 ዓ.ም
Filed in: Amharic