>
5:13 pm - Monday April 19, 2782

በመንፈሳዊነትም የከሰረችው  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን...!!!   (አቻምየለህ ታምሩ)

በመንፈሳዊነትም የከሰረችው  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን…!!!  

አቻምየለህ ታምሩ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊነትም የከሰረች ተቋም ናት። ቤተ ክርስቲያኗ የሞራልና የመንፈሳዊነት ደረጃቸው ከሃይማኖት አባቶች ሁሉ ልቀው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ክብር ነፍጋ፤ መላ ኢትዮጵያን  የደም ምድርና የንጹሐን መታረጃ ቄራ ያደረጉትን፤ ቤተ ክርስቲያኗን ራሷን  ለማፍረስ የታገሉትን እንደ መለስ ዜናዊ አይነት ባንዳ ወሮበሎች በክብር አሳርፋ እንደ ፕሮፈሰር አስራት ወልደየስ አይነት አርበኛና የአገር ባለውለታዎች ግን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር እንዳያርፉ የከለከለች ተቋም ናት።
እነሆ ዛሬ ደግሞ ጉደኛዋ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዋና  አራጇ የሆነውን  የፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ  የቀብር ስነ ስርዓት   ነገ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለመፈጸም በዝግጅት ላይ ናት።
ደም የተጠማው ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ቤተ ክርስቲያኗ በጸሎተ ቅዳሴ ስማቸውን በየእለቱ የምታነሳውን  የቤተክርስቲያኗ የበላይ ጠባቂ የነበሩትን  ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን፤ ሁለተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትሪያርክ አቡነ ቴዎፍሎስን ያለ ፍርድ በግፍ የገደለ ነፍሰ በላ ነው። በጸሎተ ቅዳሴዋ ስማቸውን የምታነሳውን ንጉሧንና ፓትሪያርኳን በግፍ የገደለን ወንበዴ በክብር የምታስባቸው ሰዎች በሚያርፉበት ልዩ ቤተ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓቱ እንዲፈጸም የምትፈቅድ ቤተ ክርስቲያን ብትኖር የሽፍቶች መዲና የሆነችዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት!
ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ በግፍ የገደለው የቤተክርስቲያኗ የበላይ ጠባቂ የነበሩትን  ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ሁለተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ቴዎፍሎስን ብቻ አይደለም። የቤተክርስቲያኗ ሶስተኛው ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም የሞቱት የነ ፍቅረ ሥላሴን  የጭካኔ አገዛዝ ሲቃወሙ ነው። ብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዘመናቸው የነበረው የነ ፍቅረ ሥላሴ አገዛዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንን አሳልፈው እንዲሰጡ በርካታ ውትወታና ጫና ቢያደረግባቸውም ለምንም አይነት ጫና ሳይንበረከኩ የተሰጣቸውን የቤተ ክርስትያን አደራ ተወጥተው  በመጨረሻም በኃይል ቤተ ክርስትያኗን በፖለቲካው ስር ለማድረግ ደርግ እርምጃ ሲጀምር የርሃብ አድማ በማድረግ፤ ገፍቶ ሲመጣም «ሬሳዬን ተራምዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንን ትደፍራላችሁ» በማለት ጸንተው ስጋቸውን በርሀብ አመንምነውና 25 ኪሎ መዝነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ጀግና ነበሩ።
የነዚህ ታላላቅ ቅዱሳን አባቶች አደራ ያለባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ልጆቿን በዱልዱል ያረዱትን እነ ፍቅረ ሥላሴን በክብር ለመቅበር እየተሰናዳች ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የምትጠየፈው ማንን ይሆን? መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚባለውን ወንበዴ ከፍቅረ ሥላሴና መለስ ዜናዊ  ጎን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር ለማሳረፍ፤ ግራኝ አሕመድን አጽሙን አፍልሳ ከነ ፍቅረ ሥላሴና መለስ ዜናዊ ጎን ለመቅበር  ከወዲሁ ዝግጅት ጀምራ ይሆን?
እነ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስን ያከበረች ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊነት የከሰረች የሽፍቶች መዲና ናት!
 የታተሙት ሶስት ምስሎች ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ቀጥታ ተሳትፎ በማድረ በግፍ እንዲገደሉና እንዲሞቱ  ያደረጋቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ቴዎፍሎስና የብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፎቶዎች ናቸው።
Filed in: Amharic