>

እውን አገር ሰላም ነው? (ከይኄይስ እውነቱ)

እውን አገር ሰላም ነው?

ከይኄይስ እውነቱ


‹‹የመከላከያ›› ኤታማዦር ሹም ነኝ የሚለው ብርሃኑ ጁላ አገር ላይ ሰላም እንደሰፈነ ተናግሯል፡፡ ለኦነጋውያን በጎጃም መተከል፣ በወለጋ እና በኮንሶ በአሸባሪው ኦነግ የሚጨፈጨፉ ዜጎች በተለይም የአማራው ሕዝብ እልቂት ምናቸውም አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ቁመና ያለው ሠራዊት የላትም የምንለው፡፡ በተለይም እንደ ብርሃኑ ጁላ ያሉ አብዛኛው ኦነጋውያን አመራሮች ከጐሣ ሳጥናቸው ወጥተው ትልቋን ኢትዮጵያ ማሰብ የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ ለመሆኑ አንድ ተራ ወታደርም ይሁን ወታደራዊ መኮንን በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ እንዲፈተፍት የትኛው ሕግና ሥነ ሥርዓት ነው የሚፈቅድለት? የቀድሞ አሳዳሪያቸው ወያኔ ውርስ ካልሆነ በቀር፡፡

እውነቱን ለመናገር ከፍ ብለን በጠቀስናቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች ብቻ ሳይሆን በመለ የሚካሄደው ወታደራዊ እንቅስቃሴ (ኦፕሬሽን) ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቀም፡፡ አገዛዙ ጁንታ ያላቸው የወያኔ አመራሮች በቁጥጥር ሥር ይዋሉ ወይም በወታደራዊ ኦፕሬሽን ይደምሰሱ ገለልተኛ በሆነ አካል የተነገረን መረጃ የለም፡፡ ባንፃሩም የሕወሓትን መዋቅር በትግራይ ከሚገኙ ማናቸውም የመንግሥት አካላት ማስወገድና አባላቱንም ከወሳኝ የኃላፊነት ቦታዎች ማንሳት  (አገዛዙ ይህንን ለመፈጸም ፍላጎቱ እንዳለው ርግጠኛ አይደለሁም) እና ዜጎቻችንን የማቋቋም ተግባር ይኖራል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በአገዛዙ ረገድ ያለን ሥጋት፣ በአሸባሪው ኦነግ ኃይሎች እየታረዱ ያሉ ዜጎች በርዝራዥ ወያኔዎች ነው እያለ አሳፋሪ ፕሮፓጋንደ የመሥራት ፍላጎት ካለው (የኢትዮጵያ አምላክ ይወቀው) የክህደት ብቻ ሳይሆን አጋንንታዊ ተግባር አድርጌ ነው የማየው፡፡ 

ዐቢይ መለ ሄዶ ሠራዊቱን የኔ የግሌ ወይም ‹የብልጽግና› አይደላችሁም ያለው እውነታውን ለመደበቅ ከሚጠቀምበት የከንፈር አገልግሎትነት ወይም ከቃላት ጅምናስቲክነት ወይም ተራ ፕሮፓጋንዳነት የሚያልፍ አይደለም፡፡ አገዛዙንና አገር አፍራሹን የወያኔ ‹ሕገ መንግሥት› እንዲጠብቅ ያደራጀው ሠራዊት መሆኑን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ሠራዊቱን ኦሮሞው ካማራው፣ አማራው ከሶማሌው ወዘተ. እያለ ሲጠራ የሠራዊቱ አደረጃጀት መሠረቱ ጐሣዊ ተዋጽኦ መሆኑን ንግግሩ ራሱ አሳብቆበታል፡፡ በብዙ መልኩ በየጊዜው የሚያደርጋቸው ንግግሮች ጥበብ/አስተዋይነት ይጎድላቸዋል፡፡ ኦነጋውያንን አማካሪ አድርጎ ማስቀመጡ መሠረታዊ ችግር ይመስለኛል፡፡ አንዳንዶቹም ‹ልጆች› ናቸው፡፡ የጎረምሳ ዘመን ሆነ፡፡ በእኔ እምነት የ60ዎቹ ፖለቲከኞች/‹የ ያ ትውልድ› አብዛኛው አባላት (ንስሓ ከገቡት በስተቀር) ያገራችንን ፖለቲካ በማሳደፍና ትክክለኛውን አቅጣጫ በማሳት ረገድ የአንበሳ ድርሻ እንዳላቸው ይሰማኛል፡፡ እነዚህን እንደ ጋሼ መሥፍን (ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልንና) በሽምግልና ሥር ያደፈጡ ‹ጎረምሶች› ነው የምላቸው፡፡ የአገር አመራርና ምክር በዕድሜ፣ በዕውቀት፣ በሕይወት ልምድ ብስለትን ይጠይቃል፡፡ አንዳንዶች በግልብነት በዚህ መልኩ የለዘቡትን/የሰከኑትን የማራቅ አልፎም የመጥላት አዝማሚያ አስተውዬአለሁ፡፡ አገርን በእጅጉ የሚያስከፍል ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ዛሬ በዓለማችን ያሉ የአገር መሪዎችን እናስተውል፡፡ ስንቶች በዕድሜ የገፉ ባለሙያች ናቸው በጡረታ ዘመናቸው እንደገና እየተጠሩ ለአገር ታላቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉት? 

ወደተነሳንበት ሃሳብ ለመመለስ በየትኛው የታሪክ ዘመን ነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጐሣ ተዋጽኦው ከዚህ ከዚህ እየተባለ ይነገር የነበረው? የአገር መከላከያ ሠራዊት እንደ መናኝ መነኩሴ ትውልዱ አይጠየቅም፡፡ እጅግ ነውርና ዓላማ አሳች ነው፡፡

አሁን ያለው ሠራዊት እውነተኛ ሳይንሳዊ አመራር ካለውና ታማኝነቱ ለሕዝብ ከሆነ፣ በየዕለቱ በመተከል፣ በወለጋ እና በኮንሶ በአሸባሪው ኦነግ የሚያልቁትንና የሚሳደዱትን ዜጎች ለመታደግ ጥቂት ኃይል አሠማርቶ ወንበዴዎቹን ለመቆጣጠር የማይቻል ሆኖ አይደለም፡፡ ከጦርነቱ በፊት ይህ ሠራዊት የት ነበር? በማንነታቸውና በሃይማኖታቸው ምክንያት በአሸባሪዎች የተጠቁትን ታድጓል? መልሱን ለሕዝቡ እተዋለሁ፡፡ አገዛዙ በቂ ኃይል የለኝም ካለ የአማራ ሕዝባዊ ኃይል ወገኑን ለመታደግ የሚያንስ አይደለም፡፡ በኮንሶም እንደዚሁ፡፡ ወንበዴው ኦነግ እንዲጠፋ ከልብ የምትፈልጉ ከሆነ በመንግሥት አመራር ሥር ሆነው ጠላትን ሊከላከሉ የሚችሉበትን መሣሪያ አስታጥቋቸው፡፡ በድኑ ብአዴንማ (ስሙን ሞት ይጥራውና) ከወያኔና ኦነግ ጋር ተባብሮ ሕዝቡ ራሱን የመከላከል ተፈጥሮአዊና ሕጋዊ መብቱን እንዳያስከብር ትጥቁን እያሳደደ ሲቀማ ነው የኖረው፡፡ ከዚህም አልፎ የባሕርይው በሆነው ባርነት ለኦነጋውያኑ አድሮ የጌቶቹን ፈቃድ ጠባቂ ሆኗል፡፡ ይህ ባገሩ ባይተዋር የተደረገ ሕዝብ ዛሬ ተጠሪና አለኝታ የሌለው በመሆኑ ሕፃናትና ሴቶችን እየተሽሎከለከ የሚገድለው የፈሪውና ጨካኙ ኦነግ መጫወቻ ሆኗል፡፡ ዛሬ ወገኖቻችን ካለቁ በኋላ መርዶ ነጋሪና አውጋዥ የፖለቲካ ፓርቲ አንፈልግም፡፡ በመተከል፣ በወለጋና በኮንሶ የሚያልቁ ወገኖቻችን ጉዳይ የአካባቢው ነዋሪ ሕዝብ ጉዳይ ብቻ የተደረገ ይመስላል፡፡ ነግ በኔን አስበህ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባንድነት ልትነሳ፣ ልትጮኽ ይገባል፡፡ 

ዜጎች በሚከፍሉት ግብር የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ራዲዮ መንግሥታዊ የኤፍ ኤም ጣቢያዎች ባንድ ወገን፣ በአገዛዙ ድርጎ የሚንቀሳቀሱ ግልብጥ ሎሌዎቹ ፋና እና ዋልታ በሌላ ወገን የአገዛዙን ልብ ትርታና የሙቀት መጠን እያዩ የሚሠሩ የውሸት/ቅጥፈት ማምረቻ ፋብሪካዎች ከሆኑ ይኸው የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ አስቆጠሩ፡፡ ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት ውስጥ ብንሆን አንድም አድርባይ ሆድ አደር እነዚህ ሜዲያዎች ውስጥ ተቀምጦና በዜጎች ሕይወት እየቀለደ የደም ገንዘብ ተከፋይ ባልሆነ ነበር፡፡ አንዳንዱን አድርባይ ብትጠይቁት ጫና ተደርጎብኝ፣ ለቤተሰቤ ስል የሚል ተልካሻ ምክንያት ሊሰጣችሁ ይችላል፡፡ ወገን! እንዲህ ዓይነት ወራዳ ሕይወት ከመምራት ተርቦ ለእውነት ማደር በምን ጣዕሙ? ቊጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች ለኅሊናቸው አድረው፣ የተለያየ ሞያ ባለቤት ሆነውና ለአገራቸው ብዙ ማበርከት ሲችሉ (ቤተሰብ ያላቸው ጭምር) ከአገር አፍራሾችና ከዘራፊዎች ጋር አንተባበርም ብለው ከወያኔም ሆነ ከወራሹ ኦነጋውያን አገዛዞች ለዓመታት ራሳቸውን አግልለው አሰቸጋሪ ሕይወት እየመሩ እንደሚገኙ ለብዙዎች እንግዳ ሊሆን ይችላል፡፡ 

ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና ለመሆኑ ብርሃኑ ጁላ ወይም አንደበቱን የተጠቀመው አለቃው ሰላም የሚሉት ጦርነት አለመኖርን ነው? የአገዛዞች ዓይነተኛ መገለጫ በመሆኑ ጦርነቱም አልቀረልንም፡፡ ዘመነ ወያኔን ትተን ያለፉት 3 ዓመታት ገደማ ኢትዮጵያ እያለፈችበት ያለውን ሁናቴ በምን እንገልጸዋለን? የሰው ልጅ ታርዶ ኩላሊቱ ተብልቷል እኮ! ነፍሰ ጡር እናት ከነፅንሷ ታርዳለች እኮ! ሕፃናትና አረጋውያን በዘግናኝ ሁናቴ ተጨፍጭፈዋል፤ ዜጎች በላባቸው ያፈሩት በርካታ ሀብትና ንብረት ወድሞአል፤ ባንድ አሸጋሪ ግለሰብ ምክንያት አገር ታምሷል፣ ዜጎች ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን አጥተዋል፤ ፍጅቱ አሁንም ቀጥሏል፤ መሳደዱ መፈናቀሉ አሁንም ቀጥሏል፤ በርትዕት ተዋሕዶ ቤክ የሚካሄደው መሳደድና አድልዎም ቀጥሏል፤ ኢኮኖሚው ዘረኝነቱ ባመጣው ቀውስ እና በዝርፊያ ተሽመድምዶ አብዛኛው ሕዝባችን የደሀ ደሀ ሆኖ በቀን አንድ ጊዜ ለመቅመስ የማይችልበት ደረጃ ደርሷል፤ በሚሊዮን የሚቈጠሩ ዜጎቻችን በቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፤ ዜጎች ተወልደው ካደጉበት፣ ወልደው ከብደው ከኖሩበት፣ ሀብት ንብረት ካፈሩበት አገራቸው ውጡልን እየተባሉ በሚሳደዱባት ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ሰላም ይሆን ያለው? በተረኞች የሚደረገው ቅጥ ያጣ የመሬት ቅርምት በቀጠለበት እንዴት ሰላም ሰፍኗል እንላለን? ከተሜ ጠል ተረኞች አዲስ አበባን ለመሰልቀጥ ወረራ ባደረጉበት እና ነዋሪውን በገዛ ከተማው ባይተዋር ባደረጉበት ሁናቴ ሰላምን ፈልጎ ማግኘት ይቻላል? እነ እስክንድርና ሌሎችም የኅሊና እስረኞች በግፍ ወኅኒ ቤት በተከረቸሙበት፣ የፍትሕ ሥርዓቱ የፖለቲካ ደንገጡር በሆነበት አገር ሰላም ከየት ይመጣል? ልጃገረድ ተማሪዎች በኦነግ ታግተው ይኑሩ/ይሙቱ ሳይታወቅ ካንድ ዓመት በላይ ባለፈበት እንኳን ስለ ሰላም መንግሥት አለ ማለት ይቻላል? አገሩ ሰላም ነው ማለት በኢትዮጵያውያን ማፌዝ አይደለም? የሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ እንዲሉ ይህንን ሁሉ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የፈጠረውና የአገርን ህልውና ሥጋት ላይ የጣለው የወየኔ አገር አፍራሽ ‹ሕገ መንግሥት› በቀጠለበት፣ ይሄም ‹ሕገ አራዊት› የዘረጋቸው የጐሣና ቋንቋ ፌዴራሊዝም፣ ‹ክልል› የሚባለው የመለያያ አጥር በቆመበት፣ ‹ልዩ ኃይል› የሚባል ሕገ ወጥ የሆነ የጐሣ ሠራዊት በየጎጡ በተደራጀበት ኢትዮጵያ ሰላም ይኖራታል ማለት ዘበት ነው፡፡ መቼስ ዐቢይም ሆነ ‹ጄኔራሉ› ጊዜው ‹የሽግግር› ነው ብለው ዋዛ ፈዛዛ እንደማይናገሩ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ‹ሽግግር› የለምና፡፡

 ብርሃኑ ጁላ የሚያወራው በምናቡ ስላለ ደሴት ካልሆነ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያለውን ጽድቅ በጭራሽ አያመለክትም፡፡ ‹ጄኔራል›! አንተኑ ነገድ ለኢትዮጵያ? (አንተ ለኢትዮጵያ እንግዳ ነህ?) ትዘ ይለኛል ይህንን ጥያቄ በሌላ ዐውድ ለአገር ከጂው ወያኔ ለጻድቃን አቅርቤለት ነበር፡፡ (26/07/2016 https://www.ethioreference.com/Amharic)

ካገር መሪ ቀጥሎ የመከላከያ ሠራዊትን በከፍተኛ ማዕርግ የሚመራ መኰንን ምናለበት ፖለቲካና ፕሮፓጋንዳውን ትቶ፣ በማይካድራ የዘር ፍጅት ስለተፈጸመባቸው ንጹሐን እና በሰሜን ዕዝ ላይ የጦር ወንጀል ስለተፈጸመባቸው የሠራዊቱ አባላት እንዲሁም የኢትዮጵያ ጠላት ከሆነው ሕወሓት ጋር ሲፋለሙ ሕይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን ሲል ከእውነቱ ቢታረቅ?

እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!! 

ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡

ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡

Filed in: Amharic