>

"በዚህ የዘር ጭፍጨፋ ትዳር ተመልካች የሆነ ሁሉ ባለወር ባለሳምት እየተባለ የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆኑ አቀርም ...!!!" (ዶ/ር ታደለ ገድል ጸጋዬ)

“በዚህ የዘር ጭፍጨፋ ትዳር ተመልካች የሆነ ሁሉ ባለወር ባለሳምት እየተባለ የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆኑ አቀርም …!!!”
ዶ/ር ታደለ ገድል ጸጋዬ

*….ይህ የዘርና የሃይማኖት እሽኮለሌ፤ “ከክልሌ ውጣ ” እኩይ የወንጀለኞችና ሕገ ወጦች ድርጊት፤ የእብሪተኞች ሥራ ወደፊትም የባሰ አገራዊ ቀውስ እንዳይፈጥር ሕዝብን ለመከራ የዳረገው ሕገ መንግሥት መፈተሸና መስተካከል አለበት…!
 
ታላቁ ንጉሠ ነገሥት  ዓፄ ዮሐንስ በዶጋሊ በአሉላ አባ ነጋና በሌሎች ተዋጊዎቻቸው ተጋድሎ በግብጾች ላይ  ድል በአስመዘገቡበት ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ   እንዲህ በማለት አድንቋቸዋል፡፡
ከላይ የወረደው ከጽዮን መቅደስ፤
በአባቱ ሚካኤል በእናቱ ሠላስ፤
አጨደው ከመረው ያን ያሕዛብ ገብስ፤
ወቃው ደበደበው ሰጠው ለነፋስ፤
አሊሙ ነፍጠኛ  ዓፄ ዮሐንስ፡፡
ነፍጠኛ፡የጦር መሣሪያ የታጠቀ ወታደር ማለት ነው፡፡-በዚህ ግጥም መሠረት ዓፄ ዮሐንስ ነፍጠኛ የተባሉት የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር ኃይለኛና ብርቱ ተዋጊ፤ጀግና ወታደር  የነበሩ መሆናቸውን ለመግለጽ ነው፡፡ነፍጥ በጥንት ዘመን የነበረ የጠመንጃ ስም ሲኾን ዓፄ ቴዎድሮስ፤ዓፄ ዮሐንስ፤ዓፄ ምኒልክና ወታደሮቻቸው ይኽንኑ ጠመንጃ(ነፍጥ)ታጥቀው የሀገር ዳር ድንበር ሲጠብቁበት ነበር፡፡ነፍጠኛ ማለትም በጥንት ዘመን የሀገር ዳር  ድንበር ሲያስከብር የኖረና የጦር መሣሪያ የታጠቀ ጀግና ወታደር ማለት ነው፡፡ልክ በአሁኑ ጊዜ ባለሙያውን መድፈኛ፤ ታንከኛ እንደምንለው ማለት ነው፡፡
   ደርግ በዘመኑ ማንንም ፀረ አብዮተኛ እያለ ያለ ፍርድ ሰውን በአምባገነንነት ይገድል  እንደነበረው  በአሁኑ ጊዜ ደግሞ አቶ ኦባንግ ሜቶ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እንደሚሉት   አንዳንድ ዘረኛና  ጽንፍ ረገጥ ፖለቲከኞች  ነፍጠኛ የሚለውን ቃል  ከምኒልክ ትርክት ጋር በማያያዝ  በተለይ ለአማራ ተወላጅና ለሌሎች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አማኞች መግደያ የይለፍ ወረቀትና ፈቃድ አድርገውታል፡፡ የጀግንነት መገለጫ የሆነው ቃል ከነፍጥ በበለጠ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ በታጠቀው ኢሕአዴግና ጋሻጃግሬዎቹ ወደ ስድብ ድምጸት ተቀይሮ “ ነፍጠኛ; ትምክህተኛ ፤ጠባብ—” በሚል ሰውን በጠላትነት ፈርጆ  የፖለቲካ አጋና መጫወት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ሰው  አልቋል፡፡የሰላማዊው ሕዝብ ደሙ ደመ ከልብ፤ ጠያቂ አልባ፤ሀገር የለሽ እንዲሆን ግፍ ሲፈጽሙበት፤ቤት ንብረቱን ሲያስወድሙበት፤ ሲያዘረፉበት፤ ሲያፈናቅሉት ኖረዋል፡፡
ሀገሪቱም በሃይማኖትና በዘር እልቂት ውስጥ እንድትገባና እንድትበታተን በየቦታው የጥላቻ  ክብሪት ሲያቀጣጥሉ ቆይቷል፡፡አሁንም፡ሕዝብ፡በማንነቱ በየቀኑ እንደ በግ እየታረደ መሆኑ የተለመደ መርዶ ሆኗል፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነትና የመከራ ገፈት ቀማሽ በሆነው ሕዝብ ቻይነት አሰቃቂው ዘመን እየተገፋ ቢመስልም በተለየ ትኩረት ችግሩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ካልተገታ ሁሉም ባለወር ባለሳምት እየተባለ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደሚሆን ማሰብ አይገድም፡፡
    በመሠረቱ ይህ የዘርና የሃይማኖት እሽኮለሌ፤ ከክልሌ ውጣ እኩይ የወንጀለኞችና ሕገ ወጦች ድርጊት፤የእብሪተኞች ሥራ ወደፊትም የባሰ አገራዊ ቀውስ እንዳይፈጥር ሕዝብን ለመከራ የዳረገው ሕገ መንግሥት መፈተሸና መስተካከል አለበት፡፡ የዜጎች የመኖር ዋስትና ሊረጋገጥና ሰላምን በማደፍረስና የሰውን ልጅ በመግደል ቁማር የሚጫወቱ ቃኤላውያን ወንጀለኞች. ግፈኞች በመንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ተጋድሎ ከድርጊታቸው ካልተገቱ   የሰላማዊው ሕዝብ የመከራ ዘመን መራዘሙ አይቀርም፡፡ኢትዮጵያ የሁሉም ሰው መብት ተከብሮባት ሳትከፋፈል የ80 ቋንቋዎችና ሕዝቦች ዐፅመ ርስትና ጉልት ሆና ለመቀጠልና ለማደግ የምትችለው ዜጎች ሁሉ በየትኛውም ቦታና ጊዜ በሰላማዊ መንገድ ተንቀሳቅሰውና ሠርተው ለመኖር ሲችሉ ነውና ሕግ ለዜጎች ሁሉ ዋስትናቸው እንዲሆን ሕገ መንግሥቱ ሊፈተሸና ሊስተካከል ይገባዋል፡፡
መዝሙረ  ምኒልክ ዘዳግማዊ (2013)  ከተሰኘውና በቅርቡ ገበያ ላይ ከዋለው መጽሐፌ የተወሰደ፡፡
Filed in: Amharic