>
5:13 pm - Saturday April 19, 0594

በመተከል ከዘር ጭፍጨፋው ባሻገር ያሉ 15 እውነታዎች...!!! (ጋዜጠኛ የኑስ ሙሀመድ)

በመተከል ከዘር ጭፍጨፋው ባሻገር ያሉ 15 እውነታዎች…!!!

ጋዜጠኛ የኑስ ሙሀመድ

1- ሕዝቡ ለ3 ዓመት አላረሰም። እንደምንም ማረስ የቻለም እህሉን ወደ ቤት አላስገባም።
2. ዘንድሮ ሰላም ይሆናል ብሎ አብዛኛው ሕዝብ በአካባቢው ያለውን የእርሻ መሬት አርሶ ነበር። ልክ አዝመራው ሲደርስ ጭፍጨፋው እንዳዲስ አገርሽቶ እህሉ እስካካሁን አልተሰበሰበም።
3- ርሃቡና ችግሩ ጠንቶበት፤ በርሃብ ከመሞት በጦርነት መሞት ይሻላል ብሎ እፍኝ እህል ሊያመጣ ወደ እርሻ ማሳው ያቀና አርሶ አደር የጉሙዝ ቀስት ቀለብ ሆኗል። ሬሳው ቤት ከደረሰ እድለኛ ነው።
4- የጉምዝ እናቶችና አባቶችም እንደ ዱሮው ያለቻቸውን መሬት አከራይተውና ቤት ያፈራውን  ሽጠው መኖር ስላልቻሉ ርሃቡና ችግሩ ከቃላት በላይ ሆኖባቸዋል። ከጉያቸው በወጡ ገዳዬች የተነሳ ከፍተኛ ስጋት ስላለባቸው መንደራቸውን ለቀው በየጫካው የሚያድሩበት አጋጣሚ አለ።
5- ከዚህ በፊት አማራና አገው ብቻ በቆዳ ቀለሙ ተለይቶ ሲጨፈጨፍ ቢኖርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሽናሻ ብሔር ተወላጆች የአስከፊ ጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል። እንዲሁም ሌሎችም ቀይ ጥቁር በሚል ተለይተው እየተገደሉ ይገኛሉ።
6- ሁሉም የመተከል ሕዝቦች ያለ ብሔር ልዩነት የርሃቡ ተጠቂ ናቸው። ይህም ጉዳይ መፍትሄ ስላልተገኘለት ሌብነትና ስርቆቱ አላስቀምጥ ብሏል። ግድያውንም አባብሶታል።
7- የሐገሪቱ ትልቁ ችግር ያለው መተከል ላይ ሆኖ እያለ መንግስት ግን መተከልን አያውቃትም። ኢትዮጵያ የትም አካባቢ ችግር ቢደርስባት በመተከል በኩል እንደሚደርስባት ችግርና ኪሳራ ግን የትም አካባቢ አይደርስባትም። መተከል የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ነው።
8- መተከል ውስጥ በብሔር ቁጥር ልክ የፖለቲካና የአስተዳደር ውክልና ከሌለ ችግሩ ዘላለማዊ እንደሆነ ይቀጥላል።
9- ጉሙዞች በሚኖሩበት የገጠር ቀበሌ ይሄ ነው የሚባል መሠረተ ልማት የላቸውም። በሁሉም የጉሙዝ ቀበሌዎች መንገድ ውሃ መብራት የለም። በስማቸው ሲነገድ ነው የኖረው።
10- ቤንሻንጉል ውስጥ ስልጣን የፈለገ አካል ወይንም ኢትዮጵያን በቤንሻንጉል ጉሙዝ በኩል መቅበር የፈለገ አካል አማራና ጉምዝን በሰከንዶች ውስጥ እንዲገዳደሉ በማድረግ ዓላማውን በቀላሉ ያሳካል። ወይንም ከሁለቱ አንዱን ራሱ በመግደል የእከሌ ብሔር እከሌን ገደለ በማለት በውሸት መረጃ እርስ በርስ እንዲጫረሱ ያደርጋል። ተጠያቂነትም አያሰጋውም።
11- መተከል ውስጥ ሁሉም ብሔሮች ሰላም ይፈልጋሉ። ግን ደካማና አንዱን ከሌላው የሚለይ የመንግስት መዋቅር ስላለ ሰላም ማግኘት አልቻሉም። ገዳይም ተገዳይም ፍትህ አግኝተው አያውቁም።
12- የአባይ ግድብ መገኛው መተከል ውስጥ ነው። በዚህ 3 ዓመት ውስጥ በነበረው ግድያና ጭፍጨፉ መንገዱ ለደህንነት ስጋት በመሆኑ የተነሳ የአባይ ግድብ ግንባታ ተስተጓጉሏል። ወደ አባይ ግድብ የሚላኩ የከባድ መኪና ሾፌሮች ሁሌም የሞት ስጋት አለባቸው። በአሁኑ ጊዜ በመከላከያ ታጅበው እንዲሄዱ ቢደረግም ሕወሃት ቀደም ብሎ ያሰለጠናቸው የጉሙዝ ሽፍቶች  ራሱን መከላከያውን ጭምር በመግደል መንገዱን ዘግተውታል።
13- መተከል ዞን ብቻውን የክልሉን 80 ፐርሰንት የቆዳ ሽፋን የሚያካልል ሲሆን የኢትዮጵያን የምግብ ፍጆታ እስከ 20 ፐርሰንት የመሸፈን አቅም አለው። አሁን ግን አምራችነቱ ወደ “ኔጌቲቭ” ወርዷል። የምግብ እርዳታ በቶሎ ወደስፍራው ካልተላከ ከሞት የተረፈው ሁሉ ስደተኛ ይሆናል።
14- መተከል እንደ ዞን ነው የተራበው ርዳታ የሚላከውና የሚታሰበው ግን አካባቢውን ለቆ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ለተጠለለው ብቻ ነው።
15- ሕወሃት ቀደም ብሎ በአባይ ግድብ መኪኖች ብዙ መሳሪያ ወደ አካባቢው ወስዶ የጉሙዝ ሽፍቶችን ከቀላል እስከ ከባድ መሳሪያ ስላስታጠቀና ስላሰለጠነ ነፍሰ ገዳዮችን ለማስቆም በሐገር ደረጃ መከላከያው በይፋ እንዲዘምት ካልተደረገ በስተቀር ችግሩ ሊፈታ አይችልም።
Filed in: Amharic