>

እንደ ኮሮና ሪፖርት ትኩረት የተነፈገው የአማራዎች ፍጅት...!!! (አሳዬ ደርቤ)

እንደ ኮሮና ሪፖርት ትኩረት የተነፈገው የአማራዎች ፍጅት…!!!

አሳዬ ደርቤ

 የሩዋንዳው ኢንተርሃሞይ ያካሄደው ጭፍጨፋ በሦስት ሳምንት ውስጥ 800 ሺህ ዜጎች እንደቀጠፈ በመጽሐፍ ተጽፎ አንብበነዋል፡፡ በፊልም አይተነዋል፡፡
ያም ሆኖ ግን የሮዋንዳው ጭፍጨፋ ጥቃቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ የተከሰተና ዘግናኝ እልቂት ያስከተለ ቢሆንም ውጤቱ ግን መልካም ነበረ፡፡  ማለትም በወንድማማቾቹ መሃከል እርቅ ተፈጽሞ የዘር ፖለቲካ በሕግ የታገደባት፣ የሰላም አየር የሚነፍስባት፣ የዓለም ኢንቨስተሮች የሚመኟት ጠንካራ አገር መፍጠር ችሏል፡፡
.
በአማራ ላይ የሚካሄደው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ግን ከሩዋንዳው ጋር ሲነጻጸር ለየት የሚያደርገው በስሜት ሳይሆን በስሌት የሚከናወን መሆኑ ነው፡፡ ማለትም ጥቃቱ በፕሮግራምና በጥበብ ቀስ በቀስ የሚከናወን በመሆኑ ግድያውን የውጩ ማሕበረሰብ አጀንዳ ሊያደርገው ይቅርና እኛም እንዲንለምደው ተደርገናል፡፡
ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት ‹‹ይሄን ያህል አማራ ተገደለ›› የሚል ዜና ‹‹ይሄን ያህል ሰው በኮሮና ሞተ›› እንደሚለው መረጃ ትኩረት የማይስብ ሆኗል፡፡
እንደውም በጥይትና በቀስት ከሚሞተው አማራ ይልቅ በኮቪድ የሚሞተው ዜጋ ባለቤት አለው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ሪፖርቱ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተጠናቅሮ ዶክተር ሊያ ገጽ ላይ ይለጠፋል፡፡
በመተከልና በወለጋ የሚኖረው አማራ ግን ሕይወቱን የሚታደገው ቀርቶ ‹‹ስንት ሰው ሞተ?›› እያለ አስከሬኑን የሚደምረው የለም፡፡ ከጥቃት የሚያተርፈው ይቅርና ሞቱን አጠናቅሮ በሪፖርት የሚያቀርበው አካል የለም፡፡
.
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በቁማርተኛ የክልል ባለሥልጣናት የሚጠፋው የአማራ ነፍስ በዝምተኛው የፌደራል መንግሥት ለዜና ሳይበቃ ተድበስብሶ እንዲቀር የሚደረግ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ሒደት አማራን መግደል እንደ መብት የሚቆጠርና አመራሮችን የማያስክስስ፣ ክልሎችን የማያስወቅስ ተራ ክስተት ሆኖ ሲታይ አማራውም በሰው እጅ ተገድሎ መሞቱን ‹‹ግዴታዬ ነው ብሎ›› መኖር ጀምሯል፡፡
.
ሞታችንን ከመለማመዳችን የተነሳ ጥቃቱን ማስቆም ይቅርና መታመምም ሆነ ማቄም የማንችል ሆነናል፡፡ ከዚህ ባለፈም ‹‹ይሄን ያህል አማራ ተገደለ›› ከሚል ፖስት ስር ላይክና ኮሜንት እንጂ ፍትሕ እንደማይገኝ ስላረጋገጥን ጥቃት በተከሰተ ቁጥር ፖስት ማድረጉም እየተዘነጋ መጥቷል፡፡
.
እኔ ግን እላችኋለሁ…
➺ሞትን አትለማመዱት!
➺በማንነታችሁ የመጣ ጥቃት ቤታችሁ እስኪደርስ ድረስ አትጠብቁት!
➺ዝምተኛው እና ቁማርተኛው መንግሥት አማራን መግደል ወንጀል መሆኑን አውቆ የመኖር መብታችንን እስኪያረጋግጥ ድረስ እንቢተኛ ሆናችሁ በምትችሉት ሁሉ ታገሉት፡፡
Filed in: Amharic