>

አቀበት ቁልቁለት ይበዛው ረዥሙ የአርቲስት ተስፋዬ ገሰሰ መንገድ...!!! (ይታገሱ አምባዬ)

አቀበት ቁልቁለት ይበዛው ረዥሙ የአርቲስት ተስፋዬ ገሰሰ መንገድ…!!!

ይታገሱ አምባዬ

 

አርቲስት ተስፋዬ ገሰሰ ማርቲን ሉተር ኪንግ ‘I Have A Dream’ በሚል ንግግር ባደረጉበት መድረክ የታደመ ኢትዮጵያዊ ነበረ…!!!
በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ትናንት ሌሊት በ84 ዓመቱ ህልፈተ ህይወቱ የተሰማው አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ ማርቲን ሉተር ኪንግ ‘I Have A Dream’ በሚል ንግግር ባደረጉበት መድረክ የታደመ ኢትዮጵያዊ ነበረ።
አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ በህይወት በነበረበት ዘመን በተለያየ ወቅት የህይወት ልምዱን በሚያካፍልበት ወቅት በአሜሪካ የትያትር ትምህርት በሚከታተልበት ዘመን የጥቁሮች የነጻነት ትግል የተጠናከረበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳል።
በኒው ዮርክ ኖርዝ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ የትያትር ትምህርት በመማር የመጀመሪያው ጥቁር የነበረው አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ፤ ጥቁሮች ለነጻነት በሚያደርጉት የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፍባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ነበሩ።
“እነ ማልኮም ኤክስ እና ማርቲን ሉተር ኪንግን በአካል አይቻቸዋለው” በማለት ይናገር የነበረው አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ፤ “ማርቲን ሉተር ኪንግ ‘I Have A Dream’ የሚለውን ንግግር ሲያደርግ እኔ እዚያው ነበርኩ” በማለት በህይወት በነበረበት ዘመን በተደጋጋሚ መናገሩ ይታወሳል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ጎሮጉቱ በሚባል አካባቢ ከአባቱ ከአቶ ገሰሰ ቆለጭ እና ከእናቱ ወይዘሮ በለጥሻቸው ያየህይራድ መስከረም 17 ቀን 1929 ዓ.ም ነው የተወለደው።
በስምንት ዓመት ዕድሜው በአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የገባ ሲሆን በትምህርት ቤቱ ስካውት ተሳትፎ ነበረው።
በልጅነቱም ደራሲ ከበደ ሚካኤል በደረሱት “የትንቢት ቀጠሮ” ቴአትር ላይ የሚያለቅስ ህጻን ልጅ ገጻ ባህሪይ ተላብሶ ተጫውቷል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር (በወቅቱ መጠሪያው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቴአትር ቤት) ከመጽሐፍ ቅዱስ የኢዮብን ታሪክ በመውሰድ በተዘጋጀ ተውኔት በመሪ ተዋናይነት የተጫወተ ሲሆን በተውኔቱ ዳይሬክተር ጋባዥነት ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ አርቲስት ተስፋዬ ሲተውን ተመልክተዋል።
አርቲስቱ በመሪ ተዋናይነት የተጫወተበት ይህ ተውኔት ወደ ቴአትር ሙያ እንዲገባ በር የከፈተለት እንደሆነም ይነገራል።
አርቲስት ተስፋዬ ገሰሰ በልጅ እንዳልካቸው መኮንን ወደ ፈረንሳይ ተልከው የሕግ ትምህርት ይማሩ ተብለው ከተመለመሉ ሰዎች እንዱ የነበረ ሲሆን የእሱም ፍላጎት የሕግ ትምህርት መማር ነበር።
ይሁንና ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ኢትዮጵያ በቴአትርና ስነ ጥበብ ብዙ ባለሙያዎች ስለሌሏት ውጭ አገር በዚሁ ዘርፍ ብትማር ይሻላል ብለው በወቅቱ ለአርቲስቱ ያቀረቡለትን ጥያቄ ተቀብሏል።
በ1951 ዓ.ም በጄነራል ሂውማነቲስ የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘ ሲሆን በ1953 ዓ.ም በኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ቤትም ተመርቋል።
አርቲስቱ በ1954 ዓ.ም ወደ አገሩ በመመለስ በቴአትር ሙያው መስራቱን ቀጥሏል።
ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ በሙያው ቴአትር መስራትና ማዘጋጀት የጀመረ ሲሆን “የሺ፣ እቃው፣ ፀረ ኮሎኒያሊስት፣ ተሃድሶ፣ “Cherchez Les Femmes” እና ፍርዱ ለእናንተ” የተሰኙ ቴአትሮችን አዘጋጅቷል።
በተለይም በ1968 ዓ.ም የደርግ ስርዓትን በሚተቸው “እቃው” ቴአትር ምክንያት በዋና ዳይሬክተርነት ተሹሞ ይሰራበት ከነበረው የአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ታግዶ ለእስር ተዳርጓል።
በፀረ-ኮሎኒያሊስትና ተሃድሶ ቴአትሮቹ በፖለቲካ ጉዳይ ያነሳቸው ሀሳቦች አወዛጋቢ እንደነበሩም ይገለጻል።
አርቲስቱ የብሔራዊ ቴአትር ቤት ዳይሬክተር ሆኖም አገልግሏል።
አርቲስት ተስፋዬ ገሰሰ በ2010 ዓ.ም “የመጨረሽታ መጀመርታ” የተሰኘ ታሪክና ሕይወት ቀመስ ሽሙጥ ልቦለድ መጽሀፍ ለንባብ አብቅቷል።
በዘመኑ የኡመር ካያምን ሩቢያቶች የግጥም መድበልን ጨምሮ በርካታ ድርሰቶች፣ ትርጉሞችና የተውኔት ጽሁፎችንም ለንባብ አብቅቷል።
የቴአትር ምሁር፣ ተዋናይ፣ ደራሲ፣ መምህር፣ ተመራማሪና ተርጓሚ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ በሙያው ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር መሰረት የጣለና ባለሙያዎችንም ያፈራ እንደሆነ ይነገርለታል።
አገር ወዳድ፣ ቅን፣ ታታሪና በሰዎች ስኬት የሚደሰት እንደሆነም የቅርብ ወዳጆቹና የሙያ አጋሮቹ ይመሰክራሉ።
አርቲስትና ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ የሦስት ወንዶችና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት የነበረ ሲሆን 10 የልጅ ልጆችንም አይቷል።
የአርቲስቱን የቀብር ስነ-ስርዓት የሚያስፈጽም ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ቀብሩም ነገ ከቀኑ 8 ሠዓት ከ30 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንደሚፈፀም ለማወቅ ተችሏል።
ከቀብር ስነ-ስርዓቱ በፊትም ነገ ከረፋዱ 4 ሠዓት በብሔራዊ ቴአትር ቤት የሽኝት መርሃ ግብር እንደተዘጋጀለትም ተገልጿል።
ENA
Filed in: Amharic