>

እነሽመልስ አብዲሣም ልክ እንደነስብሃት ነጋ … (ይነጋል በላቸው)

እነሽመልስ አብዲሣም ልክ እንደነስብሃት ነጋ …

ይነጋል በላቸው


አማራነትና ኢትዮጵያዊነት ዐይኑን ባፈጠጠ መልኩ ላለፉት አምስት አሠርት ዓመታት ከፍተኛውን ሙቀት በሚያመነጭ ሥሑል ነበልባላዊ እቶን ውስጥ መገኘታቸው ይታወቃል፡፡ አሁንም በዚያው ጊሎቲን ወኦሽትዊዛዊ ‹ቻምበር› ውስጥ ለመሆናቸው የአቢይ አህመድ የቀኝ እጅ የሆነው ሽመልስ አብዲሣ የሚያሽከረክረው ኦሮሙማ በመተከልና በወለጋ ጫካዎች የሚያፈሰው የአማራ ደም ምሥክር ነው፡፡ ሽመልስ ሆይ በምታፈሰው ደም ደስ ይበልህ!

ሙት ወቃሽ አያድርገኝና የወያኔው ቃል አቀባይ የነበረው ያ ገልቱ ጌታቸው ረዳ አቢይ አህመድ ሁሉንም ነገር እንደሸጠ ሲናገር የነበረው በተወሰነ ደረጃ እውነት መሆኑን መረዳት አይከብድም፡፡ እናም አቢይ፣ አማራንና ኢትዮጵያን ለሰይጣን አምላኪዎቹ ምዕራባውያን እንደሸጣቸው ቢታመን ከሚታየው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ብዙም ስህተት አይሆንም፤ እንዲህም ስል ሞት የተፈረደባቸውን የማኅበረሰብ ክፍል አባላት ጨምሮ በዚህ ብላቴና ፍቅር ያበዱና የከነፉ ብዙ ልበ ሥውራን ዜጎች እንደሚቃወሙኝ ምናልባትም ከዚያም ባለፈ ፋቱዋ እንደሚያዝዙብኝ አላጣውም – ፍቅር ዕውር መሆኑ የሚነገረው ለዚህ ይመስለኛል፡፡ እንጂ በአቢይ አግላይና ፍትኅ የተዛባበት አመራር ኢትዮጵያና አማራ ይበልጥ ጠፉ፣ ይበልጥ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕረፍት አጡ እንጂ ጮቤ የሚያስረግጥ ምንም የተለዬ ነገር የለም፡፡ መሸጥ ሲባል ደግሞ በግድ በገንዘብ አንጻር ብቻ መታየት የለበትም፡፡ ሽያጭ ሁሉ ከማቴሪያላዊ አስተሳሰብ ትንሽ ወጣ ባለ ሁኔታ ከነፍስም ከጨለማው ንጉሥ የቃል ኪዳን ውልና ከሌላ ሌላም ነገር ጋር ሊገናኝ ይችላል፡፡ ለምሣሌ አቢይ አህመድ አንድም ቁሣዊ ነገር ሳይቸግረው ነፍሱን ለአጋንንቱ ዓለም አንደዜ ፈርሞ በማስረከቡ ግና ቢሊዮን ዶላር ቢሰጡት አማራን ከመታረድ ሊያድን አይችልም፤ ጓደኞቹም እንደዚሁ – የ“ሙታንሳዎቹ” የነኢዩ ጩፋና እስራኤል ዳንሣ አለቃ ሆኖ ከማስመሰል ባለፈ የእግዚአብሔርን መንገድ ይከተላል ብሎ ማመን የዋህነት ነው፡፡ እርኩስ መንፈስ የተጠናወተው ሰው መልካም ነገር ለማድረግ የሚነሳሳው ያ የሚያደርገው መልካም ነገር ለዓላማው ስኬት አንዳች አስተዋፅዖ ካለው ብቻ ነው፡፡ ትርፍና ኪሣራቸውን አስልተው ነው ሰይጣናውያን ደግ ሰው በዋለበት ሥፍራ የሚውሉት፡፡ ነገሩ የገንዘብ ወይም የመብላት የመጠጣት ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የዓላማ ቁርኝትም እንጂ፡፡

በነፍስ ከቆየሁ ከትንሣኤ ወዲህ ወደዚህ ዓይነቱ የሰለቸኝ መድረክ ባልመጣ ደስ ይለኛል፡፡

እናላችሁ ዓላማ መጥፎም ይሁን ደግ ቀፍዳጅ ነው – የሰይጣንን ቀብድ በልቶ፣ ከሰይጣን ጋር ውል አስሮ በሰላም ተኝቶ ማደር ዕርም ነው፡፡ ወደህና ፈቅደህ የገባህበት ዓላማ በነፍስህም ሊመጣ ይችላልና መውጫው ጭንቅ ነው፡፡ ምናልባት በመጨረሻው አካባቢ ከነቃህና የሠራኸው ግፍና በደል አላስቆም አላስቀምጥ ካለህ ጨርቅህን ጥለህ ልታብድ ወይም ራስህን ልታጠፋ ትችላለህ፡፡ እጅግ በጣም ጥቂቶች ግን በንስሃ ጠበል ታጥበው የበደሉትን የሚክሱበት አጋጣሚ አለ – ልክ እንደፊተኛው ሳዖል (የኋለኛው ጳውሎስ)፡፡ ለበጎም ሆነ ለክፉ ሥራ መመረጥን ይጠይቃል፡፡

የአማራ ጠላቶች አሁን በሙሉ አጋንንታዊ አቅላቸው እየተንቀዠቀዡ ናቸው፡፡ ዘመኑ የመጨረሻቸው መሆኑን ሳይረዱ አልቀሩም፡፡ በአዲሱ አገላለጽ ከውጪም ከውስጥም ሆነው በከፍተኛ መናበብ አማራንና ኢትዮጵያን በነባሩ አነጋገር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድባቅ ለመምታት እየተራወጡ ይገኛሉ፡፡ የፌዴራል ተብዬውን የመንግሥት መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ከላይ እስከታች ተቆጣጥረው ያለ ቆንጣጭ ያለ ገልማጭ ያሻቸውን እያደረጉ ነው – ማግኘት ብርቁ የሆነ ሰው አያግኝ ወገኖቼ – ሰው አያስቀምጥማ! ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ወደ ኦሮሚያ ንግድ ባንክ ለመለወጥ በሚያሣዩት ቅጥየለሽ ሩጫ የወጪና ገቢ ቫውቸሮች ላይ የማንንም ቡራኬና ፈቃድ ሳይጠብቁ አማርኛንና እንግሊዝኛን አስከትሎ ኦሮምኛ በላቲን ፊደላት ከፊት እንዲጻፍ አድርገዋል፡፡ ኦሮምኛን ቀርቶ ቻይንኛንና ኩናምኛን ቢጽፉ ለኔ ግድ የለኝም፡፡ የቋንቋ ጠብ የጅሎችና የደደቦች ጠብ መሆኑን ስለምረዳ የኦሮምኛው መጨመር በራሱ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ቋንቋ ባለቤት የለውም፡፡ የሁሉም ነው፡፡

ችግሩ ሌላ ነው፡፡ ችግሩ ሽመልስና ቡድኑ አማርኛንና አማራን በእግረ መንገድም ኢትዮጵያን በአካልም በመንፈስም በሥነ ልቦናም አጥፍተው ኦሮሙማ የሚሉትን አዲስ ዘይቤ በመትከል ሰማንያውንም ብሔር ብሔረሰብ በአንድ አዳር ኦሮሞ እንዲሆን ካልፈለገም አንገቱ በሜንጫ ተቀልቶ እንዲሞት የሚያደርጉት ሁለገብ ዘመቻ ነው፡፡ በንግግራቸውም በድርጊታቸውም የምናየው ይህንኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኅልውና አደጋን ይደቅናል፡፡ በተወደደ የዘመናችን ምድራዊ ዕድሜ ሰማንያው ነገድና ጎሣ በአንድና በሁለት ወር ውስጥ ኦሮምኛን ለምዶ አማርኛን ደግሞ ረጋግጦ ሲጥል ይታያችሁ – ወይ ሞኝነት፡፡

     አማርኛን ከአማራ ያለመለየት ድንቁርና መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ቀደምት ገዢዎች ከየትም ጎሣ ቢመጡ የሚጠቀሙት የአስተዳደር ቋንቋ አማርኛን ነበር – የቅርቡን ወያኔን ጨምሮ፡፡ ያን ያደርጉት የነበረው የራሳቸውን ልሣን መጠቀም አቅቷቸው ወይም አማራ የተባለው ሕዝብ የርሱን ቋንቋ የጋራ እንዲያደርጉለት ለምኗቸው ሣይሆን ለአገዛዛቸው ከሌሎቹ ይበልጥ ምቹ ሆኖ ስላገኙት ነው፡፡ በዚያም ምክንያት አማርኛ እስከቅርብ ዓመታት ድረስ እጅግ ብዙው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይናገረዋል፤ ከኢትዮጵያም ባለፈ አሜሪካንንና ጀርመንን በዋናነት ጨምሮ በሌሎች ሀገራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እናያለን፡፡ ይህ ክስተት አክራሪ ኦሮሞዎችን ከማስቀናትና ከማስመቅኘት ይልቅ የራሳቸው ሀብት የሆነውን ይህን ቋንቋ በመግዣ መሣሪያት ቢገለገሉበት የአማርኛ ተናጋሪውን ብቻ ሣይሆን በዚህ ቋንቋ እንደሰምና ፈትል ተዋህዶ ከሚኖረው ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ዕርቅና ስምምነት በፈጠሩ ነበር፡፡ ለዚህ አልታደሉም፡፡

አሁን ሁሉም የአቢይ ልጆች ከፍተኛ ሥራ ላይ ናቸው፡፡ የማነ ንጉሤ የተባለው የአቢይ የጡት ልጅ ሳይቀር ጦርነት በባለ አራትና አምስት ኮከብ ሆቴል እየተንፈላሰሱ በሀገር ሀብት ፒዛ እንደመግመጥና ከቆነጃጅት ጋር እንደመማገጥ መስሎት “ልዩ ኃይላቸውን ከራያና ከወልቃይት ካላስወጡ አማሮችን ለመደምሰስ እኔም እንደሕወሓት በረሃ እገባለሁ!” በማለት ይሄን መከረኛ ጥርሳችንን ሳንወድ በግድ እያስገለፈጠ ነው፡፡ አማራ የፍየል ሥጋ የሆነባቸው አካላትና ግለሰቦች ሁሉ በአሁኑ ወቅት ከምን ጊዜውም በላይ ወብርተዋል፤ ለያዥ  ለገራዥ አስቸግረው ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ ነው፡፡ ታዬ ደንደኣ፣ አዲሱ አረጋ፣ ሕዝቅኤል ጋቢሣ፣ ፀጋየ አራንሣ፣ አሉላ ሶሎሞን፣ … ሁሉም እንደቀትር እባብ እየተቅነዘነዘ ነው፤ የታየው ነገር መኖር አለበት፡፡ አዎ፣ መጽሐፉም እኮ “አፍ ይፀውዖ ለሞት” ይላል፡፡

ለነሱ ባይታይ እኔ እማየውን ልንገራቸው፡፡ ከዚያ በፊት ግን አቢይ አህመድ ጀምበሩ ሳታዘቀዝቅ በተቻለው አቅም ሁሉ አማራን ይጨፍጭፍ፤ ያስጨፍጭፍ፡፡ ጠፍጥፈው የፈጠሩት የቀድሞ ጌቶቹ ለይስሙላ ያቆሙትን ወልጋዳ ህገ መንግሥት ተብዬ ሳይቀር እንዳሻው እየደፈጠጠ ኦሮሙማን በአፋጣኝ ይገንባ፡፡ ወትሮም ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም – እሱና እሱን መሰሉ ሽመልስ አብዲሣ ገና ንፍጣቸው ሳይደርቅ አባታቸው ሉሲፈር ፈቅዶ በሰጣቸው ሥልጣን ደጋግ አባቶቻቸው ያቆዩዋትን ሀገር ተል ተሎ ብለው ያፍርሱ፡፡ የደቡብ ሱዳን ዜጋ መሆኑ በሚነገርለት በቤንሻንጉሉ የቁጩ ፕሬዝደንት በአሻድሊ አማካይነት በመተከል የሚገኘውን አማራ ይጨርሱ – ከዚያ ሰሞኑን በ“ምን ታመጣላችሁ” የልጆች ዓይነት ብሽሽቅ እንዳሳዩን ኬክ እየቆረሱ ሲፈልጉ በለስላሳ ሳይፈልጉ በሻምፓኝ ይራጩ፤ ኦነግ ሸኔም ያለውዴታው በግድ በሠፈራ ፕሮግራም በደርግ መንግሥት ተወስደው በወለጋና በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ አማሮችን ቶሎ ቶሎ ይግደል፡፡ ኦነጎችም ይባሉ ኦህዲዶች ጊዜ የላቸውም፡፡ አበቅቴያቸው አልቋል፡፡ ሃሳዩ መሲሕ በእውነተኛው የሕዝብ ልጅ የሚተካበት ወርቃማ ዘመን እየገሰገሰ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመሰ(ሸ)ጋችሁ ጳጳሣትና ኤጲስ ቆጶሣት እንዲሁም ምድረ ትብታባም ደባትርና ካህናትም ውስልትናችሁንና ዘሟችነታችሁን በርቱና ቀጥሉ፡፡ የእናንተ ብልግናና የሰይጣን አገልጋይነት ነው ሀገራችንን ለዚህ ያበቃት፡፡ (ቅናት አይደለም – እኔ 33 ዓመታትን ሥራ ላይ ቆይቼ ብስክሊት የለኝም – ዕድሜው 30 ዓመት ያልሞላ የ… ቤ/ክርስቲያን ካህን ግን ቪትዝ አለው – አንድ ወይ ሁለት ብቻ ደግሞ እንዳይመስሉህ፤ ብዙ ጉድ መዘርገፍ እችላለሁ፤ ሕዝቡም ያውቃል) ጥምጥምን ማሳመርና ቃለ እግዚአብሔርን ቀን ከሌት መቀለጽ ብቻውን የትም እንደማያደርስ በተለይ ባለፉት 40 ዓመታት አየነው – ለዕውቀትማ ሊቀ ሣጥናኤልንስ ማን ያማዋል፡፡ በኖኅና በሎጥ ዘመናት የፈጣሪ መቅሰፍት የተላከው ልክ እንዳሁኑ መልካም እረኞች በዓለማዊነት ጠፍተው በጎች በቀበሮና በተኩላ በመበላታቸው እግዚአብሔር ተቆጥቶ ነው፡፡ የአሁኑም ከዚያ የተለዬ አይደለምና ራስህ ፍቅር ሳይኖርህ ዐውደ ምሕረት ላይ ቆመህ “ተአምሁ በበይናቲክሙ…፤ ፍቅርሰ ሰሃቦ ለወልድ ወልድሰ ሰሃቦ ለአብ…” እያልክ ከእዳሪ ለማያልፍ እህል ውኃ ብለህ አንተ እማትተገብረውን ቃለ እግዚአብሔር ካንተው ለማይሻለው ጠፍ ምዕመን የምትሰብክ ወምበዴ ሁላ ቀንህ ቀርቧል፤ ያንተን የተሳሳተ የሕይወት ጎዳና ተመልክቶ ባንተ የተሳሳተ አርአያነት ምክንያት በሰፊው ጎዳና የሚነጉደው “ሕዝበ ክርስቲያን” ወደ አምልኮ ቦታዎች ሄዶ “አንቺ ቅድስት ማርያም፣ የእገሌንና የእገሊትን መጨረሻ እስከዛሬ ወር ካሳየሽኝ አንድ ባኮ ሻማ ስለት አስገባልሻለሁ” እያለ በቀነ ገደብ የተወሰነ “ጸሎት” አድርሶ ሊመጣ የቻለው በእውነተኛ አባቶች መጥፋት ነው፡፡ ይህ አሁን የበሰበሰና የተግማማ የፖለቲካና የሃይማኖት ተቋም ሁሉ በመለኮታዊ ሠይፍ ድራሹ የሚጠፋበት ዘመን እየመጣ ነው፡፡ ዘረኝነት ታሪክ የሚሆንበት ተባራሪና ተሳዳጅ ሀገርን ተረክቦ በፍትኅ የሚያስዳድርበት ጊዜ ከፊት ለፊታችን ተገሽሮ ይታየኛል፡፡ ከተባለው የቀረ የለም፤ ከሚባለውም የሚቀር አይኖርም፡፡ ስብሃት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል፡፡ አሜን፡፡ 

EMAIL:  ma74085@gmail.com

Filed in: Amharic