>

ዕረፍትና መዳን ከየት ነው? (ዶ/ር በቃሉ  አጥናፉ  ታዬ)

ዕረፍትና መዳን ከየት ነው?

ዶ/ር በቃሉ  አጥናፉ  ታዬ


በቅዱስ መጽሃፍ ውስጥ በመፅሐፈ አስቴር የሚከተለው ታሪክ ተከትቦ እናገኘዋለን፡፡ ለንጉስ አርጤክስስ ባለሟል(ባለስልጣን) ለነበረው ሐማ የንጉሱ ባሪያዎች ሁሉ ይሰግዱለት ነበር፡፡ አይሁዳዊው መርዶክዮስ ለሐማ እንዳልሰገደ ሐማን ባወቀ ጊዜ በአርጤክስስ መንግስት ስር የነበሩትን አይሁድን ሁሉ ሊያጠፋ ሐማ ፈለገ፡፡ ሐማ አይሁድን ሁሉ ለማጥፋት፣ ልጆችንም  ሽማግሌዎችን ህፃናትና ሴቶችን በአንድ ቀን ይጠፉና ይገደሉ ዘንድ ደብዳቤዎች ፃፉ፡፡ መርዶክዮስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፣ ማቅ ለበሰ፣ የመረረ ጩኸት ጩኸ፤ ፀለየም፡፡ ለሐማ ያልሰገደበትን ምክንያት ለአምላኩ እንዲህም አለ፡ ‘’ከመናቅ እንዳይደለ፣ በትዕቢት እንዳይደለ፣ አላዋቂ ለሆነ ለሐማ እንዳልሰግድ ይህንን ያደረግሁት ራሴን በማኩራትም እንዳይደለ አቤቱ አንተ ሁሉን ታውቃለህ’’ አለ፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ መርዶክዮስ ያሳደጋት እና የአጎቱ ልጅ የሆነች አንዲት አይሁዳዊት ቆንጆ አስቴር የምትባል በንጉሱ በአርጤክስስ ቤት ትኖር ነበር፡፡ አስቴር መልከ መልካም እና ቆንጆ ስለነበረች በንጉስ አርጤክስስ ፊት ሞገስ አግኝታ እና በንጉሱ ተወዳጅ ሁና _በቤተ-መንግስቱ ትኖር ነበር ፡፡ አይሁዶች ከመጣባቸው መከራ አስቴር ትሰውራቸው ዘንድ መርዶክዮስ አስቴርን ተማፀናት፡፡ ዳሩ ግን አስቴር ወደ ንጉሱ ካልተጠራች በቀር እንደማትገባ ለመርዶክዮስ ስትነግረው  መርዶክዮስ እንዲህ አለ፡፡ አንቺ በንጉስ ቤት ስለ ሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ አታስቢ፡፡ ‘’በዚህ ጊዜ ቸል ብትይ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል… ደግሞም ወደ መንግስት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል’’ 

መርዶክዮስ የነበረበት  ጭንቀት እና አጠቃላይ ቀውስ አሁን የኢትዮጲያ ህዝብ ያለበትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፤ሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ጋር ይመሳሰላል፡፡

የኢትዮጲያ ህዝብ እረፍት አጥቶ በዘረኝነት፣ በንሮ ውድነት፣ በስራ አጥነት፣ በፍትህ እጦት፣ እየናወዘ በነበረበት ጊዜ የለውጥ ኃይሎች ከተለያየ አቅጣጫ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ለውጡ ስኬታማ እንዲሆን በርካታ ኢትዮጲያውያን አስተዋጾኦ ያደረጉ ሲሆን በኢህአዲግ ውስጥ የነበሩት የለውጥ ኃይሎችም የበኩላቸውን ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ በተለይ በጥቂት የብአዴን እና የኦህዴድ አመራሮች ተሳትፎ ለውጡ ፍሬ ሊያፈራ ችሏል፡፡ 

በለውጡ ሂደት ውስት ለማ መገርሳ የለውጥ ሐዋሪያ ሁኖ የለውጥ ቡድኑ በእርሱ ስም ‘ቲም ለማ’ እየተባለ ሲጠራ አብዛኛው ኢትዮጲያዊ በለማ ላይ ከፍተኛ እምነት እና ተስፋ ነበረው፡፡ በተለይ ባህር ዳር ከተማ ሂዶ ‘ኢትዮጲያዊነት ሱስ ነው’ ብሎ የተናገረው ንግግር የብዙ ኢትዮጲያዊያንን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡ በቋንቋ ተከፋፍሎ ሊጠፋ የነበረውን ታሪካዊ ቁርኝት የለማ ቲም ይታደገዋል ብለን ተስፋ ጥለን ነበር፡፡ ዳሩ ግን ለማ የብሄርተኝነት ክር ስቦት ትክክለኛ ማንነቱ ዲሞግራፊ ለመቀየር ባደረገው ጥረት ታዬ፡፡ በለማ ላይ ተስፋ አድርገን ስንመረኮዝ የኢትዮጲያውያን ዕረፍት በለማ በኩል እንዳልሆነ ተረዳን፡፡ 

ዶ/ር አብይ አህመድ በሚናገሩት ቃላት የዜጎችን የልብ ትርታ ማንቀሳቀስ ችለው ነበር፡፡ አብዛኛው ኢትዮጲያዊ በዶ/ር አብይ ላይ ከፍተኛ ተስፋ እና እምነት ነበረው፤ ያ ተስፋ ግን ዕለት ዕለት እየሟሸሸ ቅርፅ አልባ እየሆነ መጥቷል፡፡ ቃል እና ተግባር ተዋህደው ሁኔታዎችን መለውጥ አልቻሉም፡፡ የንግግር ዝርው ቃል ስጋ ለብሶ  መታየት ስላልቻለ እና ፅንፈኛ ብሄርተኝነት በሀገሪቱ ላይ እንዲፈነጭ እድል ስለሰጡ  ተስፋችን ህልም ሆኖብናል፡፡ 

ለሶስት ዓመታት በየቀኑ የሰው ልጅ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በመተከል እና በወለጋ ህይወቱ ያልፋል፤ የዶ/ር አብይ አስተዳደር ግን መተከልን አያውቃትም፡፡ በቤኒሻነጉል – ጉምዝ የሀገሪቱ አካል እስከማትመስል ድረስ የፌደራል መንግስቱ ዝምታን መርጧል፡፡ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ በቤኒሻነጉል – ጉምዝ፣ በጉራ ፈርዳ፣በምስራቅ ወለጋ የሚፈሰው የንፁሀን ደም ለጠቅላዩ ምንም ስሜት አልፈጠረባቸውም፡፡ የተረኝነት ፖለቲካ በሀገሪቱ ላይ ገዝፎ የአብሮነት ጉዞውን ሲያወከው እና በዐይነ ቁራኛ የሚተያዩ ማህበረሰቦችን እንዲጠናከሩ ዕድል ሲሰጣቸው ስናይ በጠቅላዩ ተስፋችን እንዲደበዝዝ ምክንያት ሆኖዋል፡፡  በደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጉዳይ፣ በኮንዶሚየም ጉዳይ፣ በመሬት ችብቸባው፣ በአማርኛ ቋንቋ እና በተናጋሪዎች ላይ የሚሰራው ሸፍጥ፣የህሌና እስረኞች ጉዳይ(የባልደራስ አመራሮች እስር)፣ የብሄር አድሎዓዊነታቸውን፣ እና ከሰው ልጅ ህይወት ይልቅ ለመዝናኛ ቦታዎች የሚሰጧቸው ትኩረት ሲታይ ዶ/ር አብይ ኢትዮጲያን የሚታደጓት መሪ እንዳልሆኑ ለመረዳት  አያዳግትም፡፡ 

ታዲያ የኢትዮጲያ ዕረፍትና መዳን ከየት ነው? የኢትዮጲያ ዕረፍትና መዳን ከሰማይ ነው፡፡ ለተሰራው ግፍ፣ ለፈሰሰው ደም፣ ለዘመናት ለተጮኸው ጩኸት እግዚአብሄር መልስ መስጠት ጀምሯል፤ አሁንም ለሚሰራው ስልታዊ ጥቃት እግዚአብሄር መልስ ይሰጣል፡፡ እኛም ለሰማያዊው መንግስት ምድራዊ አምባሳደሮች ሁነን ኢ-ፍትሀዊ ስርዓትን፣ ብሄርተኝነትን፣ አድሎዓዊነትን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እናወግዝለን፤ስርዓቱም እንዲለወጥ እንታገላለን፡፡

Filed in: Amharic