>

ሕወሓትን እና ኦነግን አምርረን መጥላታችን  የደርግን አረመኔነት አያለዝብም (ከይኄይስ እውነቱ)

ሕወሓትን እና ኦነግን አምርረን መጥላታችን የደርግን አረመኔነት አያለዝብም

ከይኄይስ እውነቱ


ለዛሬው ርእሰ ጉዳይ መነሻ የሆነኝ የወታደራዊው ጁንታ ደርግ አገዛዝ ሁለተኛ ሰው የነበረው ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ዜና ዕረፍት ነው፡፡ 

እንደ ኢትዮጵያ ከሕይወት ይልቅ ለሞት ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ባህል ባለው ኅብረተሰብ ውስጥ፣ በተለይም ምነው ሞቶ በተገላገልኩ የሚለውን አረመኔ ሬሳ ከሆነ በኋላ ጻድቅ የሚያደርግበት አጉል ወግ በሠፈነበት ማኅበረሰብ ውስጥ እገሌ እንኳን ሞተ ብለን መናገር ተገቢ ላይሆን ይችላል፡፡ በርግጥ እንደ ክርስትናው አስተምሕሮ እና እንደ ሰው ልጅነትም ስናየው የአንድን ሰው ሞት መልካም አድርጎ መውሰድ ጤናማ አመለካከት አይመስልም፡፡ 

ነገር ግን መንግሥታዊ ሥልጣን በዓመፃ/በጉልበት ይዘው ታሪክ ይቅር የማይላቸው ዘግናኝ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን በሕዝብ ላይ ሲፈጽሙና ምድርን በደም አበላ ሲያጥቡ የነበሩ፤ ለዘመናት የተገነቡ መልካም ዕሤቶችን ከሥር ነቅለው በአገር ላይ ዘለቄታዊ ጥፋት ሲያስከትሉ የነበሩ እንደ ፋሺስቱ ሙሶሎኒ፣ ናዚው ሂትለር እና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እነዚህን መስለውና አክለው የተነሱ ግፋቸውና ጭካኔአቸው እስከ የሌለው አረመኔዎችና ያቆሟቸው የአገዛዝ ሥርዓቶች መወገድ እፎይታ መስጠቱን የሚክድ የለም፡፡ 

ያለ ፍርድ የጅምላ ፍጅትን በሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ያስተዋወቀና ያሠለጠነ ፋሺስታዊ አገዛዝ ደርግ ነው፡፡ ገና ከማለዳው ኢትዮጵያ በብዙ ድካምና ሀብቷን አፍስሳ ያፈራቻቸውን ባንድ ምእተ ዓመት የማንተካቸውን ታላላቅ ኢትዮጵያውያንን (አርበኞችና ሊቃውንትን) በተለምዶ 60ቹ የምንላቸውን የዓፄ ኃይለሥላሴ ባለሥልጣናትን በመረሸን ነው ደም አፍሳሽ አገዛዙን ያሟሸው፡፡ በመሀል የፈጸመውና አንድ ትውልድ የበላው የቀይ ሽብር/ነጭ ሸብር እልቂት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አገዛዙ የተደመደመው አሁንም አገራችን ልትተካቸው የማትችላቸውን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ባለ ከፍተኛ ማዕርግ ወታደራዊ መኮንኖችን በመረሸን ነው፡፡ በዚህም ከሕወሓት አስቀድሞ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ንቀቱን ያሳየውና ሠራዊቱ ለደረሰበት የሞራል ውድቀት፣ ውርደትና እንግልት የመጀመሪያ ተጠያቂው ራሱ ደርግ ነው፡፡

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት  አገርን ሰው አልባ፣ ሃይማኖት አልባ፣ ዕሤት አልባ፣ ወዘተ. ከማድረግ ምን የተለየ ምን ትርጕም አለው? ደርግ ይህንን ፈጽሞታል፡፡ ከዛም አልመከር አልሰማ ብሎ ከሱ ለከፉ የጐሣ አረመኔዎች ነው አሳልፎ የሰጠን፡፡ ወንድሜ አቻምየለህ ታምሩ እንዳነሳው ሟቹ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ በዓፄ ኃይለሥላሴና በኢኦተቤክ ፓትርያርኮች ግድያ የነበረው ድርሻ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በግፍ ለተገደሉት ለ60ዎቹ ታላላቅ ኢትዮጵያውያንና በደም ተጀምሮ በደም ለተደመደመው አገዛዝ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንባር ቀደም ተጠያቂዎች አንዱ መሆኑ እሙን ነው፡፡ የቤተመንግሥቱንና ቤተክህነቱን ራሶች በግፍ በመግደል በፈሪሃ እግዚአብሔር የተቃኘውን የሕዝብ ሞራል እንዲንኮታኮት ያደረገ፣ ሕዝባችን ለእነዚህ ለአገር አዕማድ የሆኑ ሀገር-በቀል ተቋማት የነበረውን ክብርና ዋጋ ያዋረደና ዛሬ ኅብረተሰባችን ለደረሰበት አስደንጋጭ የሞራልና ማኅበራዊ ድቀት የቁልቁለቱን መንገድ የጀመረ ጨካኝ አገዛዝ ነው – ደርግ፡፡ ለክፋቱ  አርኪቴክት ከሆኑት ዋናዎቹ አንዱ ደግሞ ሟቹ ሻምበል መሆኑ አይካድም፡፡

ሟቹ ፍርድ ተቀብሎ በመጨረሻም በምሕረት የወጣም ቢሆንም፣ ባንፃሩም በሞት በተለየ ሰው ላይ መጨከን ቢመስልም ከሻምበሉ ዕረፍት በኋላ ባንድ የግል ሜዲያ በማስታወሻነት ያየሁት አጭር መልእክትና መልካም ሠርተው ላለፉ በማጀቢያነት የሚቀርበውን የጋሽ ጥላሁንን ‹‹ሞት እንኳን ጨክኖ›› (ምናለ ደጋጉን ዳግመኛ ቢፈጥረው) የሚለውን ሙዚቃ መስማቴ በየትኛውም መመዘኛ ትክክል ካለመሆኑ በተጨማሪ በአገዛዙና በባለሥልጣናቱ ጭካኔ ተነግሮ የማያልቅ ግፍ የተፈጸመባቸውን አእላፍ ኢትዮጵያውያንን መሳደብ ይሆናል፡፡ በግፍ ላይ ግፍ እየተደራረበበት የመጣ ወገናችን ይረሳል ማለት አይደለም፡፡

እባካችሁ ይህንን በ‹አጋንንት› መካከል ከንቱ ንጽጽር የምታደርጉ ሰዎች ደጋግማችሁ ብታስቡበት መልካም ነው፡፡ በሰው ቁስል እንጨት አትስደዱ፡፡ ደርግ አረመኔያዊ አገዛዝ ነው፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት ገደማ ለተነሱትም ፋሺስታዊ/አፓርታይዳዊ አገዛዞች (የሕወሓት እና ወራሹ የሆነው የኦነጋውያኑ አገዛዝ) ወይም የጐሣ ጁንታዎች (ethno juntas) መንገዱን የጠረገና መሠረቱን የጣለ የአገዛዝ ሥርዓት መሆኑን ለአፍታም መርሳት የለብንም፡፡ ከበቂ በላይ ሕያው ምስክሮች መኖራቸውን አትዘንጉ፡፡ የአረመኔነት ሬከርዱን ያሻሻሉ ሰይጣናዊ አገዛዞች በመነሳታቸው ብቻ የደርግን ዲያቢሎሳዊነት ለማለዘብ መሞከር ለኢትዮጵያውያን ፍትሕ እንደመሥራት አድርገን አንቊጠረው፡፡

 

እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!! 

ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡

ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡

Filed in: Amharic