የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ በእኔ እይታ
ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )
Tilahungesses@gmail.com
ለብሔራዊ ውይይት ይበጅ ይሆን በሚል ቀና መንፈስ የቀረበ
ክፍል ሶስት
የግል ማስታወሻ፡- እኛ በውስብስብ የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ የምንገኝበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አቅጣጫ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ይመስላል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ትልቋን የኢትዮጵያ ስእል አሻግሮ በማየት ሀገራችንን ለመገንባት አንድነታችንን ማጠንከር፣ መከፋፈልን ማስወገድ ይገባናል፡፡ አንድ ከሆን እንቆማለን፡፡ ከተለያየን እንወድቃለን፡፡ ››
<< We are amid a stream of political challenges. Looking at the big picture, let us unite to build our country and trample the divisions between us. If we stand we united and if we divide we fall dawn >>
አሁን ያለውን መንግስት ከምን አኳያ መተባበር ይቻል ይሆን ?
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ባቀረብኳቸው መጣጥፎች ላይ የመንግስትን ጥንካሬና ድክመቶች ያልኳቸውን ነጥቦች ለአንባቢው በወፍ በረር ለማስቃኘት ሞክሬአለሁ፡፡ ጸሁፉ ጠቃሚና ምክንያታዊ ሀሳቦችን እንደያዘ እገምታለሁ፡፡
አንድ ምክንያታዊ የሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅጣጫ በተመለከተ ያለው ግንዛቤ አስደንጋጭ እንደሚሆንበት ለመተንበይ አዳጋች አይመስለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ በአንድ ሳንቲም ላይ እንዳሉ ሁለት የተለያዩ ገጽታዎች የሚቆጠር ሲሆን፣ አንደኛው ገጽ አንድነት ሲሆን ለኢትዮጵያ ህይወትን የሚያድስ ነው፡፡ ሌላኛው ሁለተኛው የሳንቲሙ ገጽ ደግሞ መከፋፈልን የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ ግን ለኢትዮጵያ አይበጃትም፡፡
በአንድ የፖለቲካ መረጋጋት በሚገኝባት ሀገር፣ የሀገሪቱ ሰላም አስተማማኝ በሆነበት ሁኔታ፣ጠንካራ የፍትህ ተቋማት፣ የዲሞክራቲክ ተቋማት ባሉበት ሁኔታ ወዘተ ወዘተ መንግስትን መሞገት፣ በዲሞክራቲክ ምርጫ ላይ ተሳትፎ በሰለጠነ መንገድ የማእከላዊው መንግስትን ለመተካት የፖለቲካ ስራዎችን ማከናወን የዲሞክራቲክ መብት ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሀገር አደጋ ውስጥ ስትወድቅ፣ በየአካባቢው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በህገ ወጥ ታጣቂዎች ሲፈጸሙ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ከመንግስት ጎን በመቆም አጥፊዎች በፍትህ አደባባይ የሚቆሙበትን መንገድ መሻት አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ በሌላ አነጋገር የማእከላዊ መንግስትም ሆነ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በኢትዮጵያ ምድር እንዲከበሩ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው፡፡ ምንም እንኳን በአንድ ሀገር ላይ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ እንዳይጣሱ፣ ከተጣሱም በኋላ አጥፊዎችን በፍትህ አደባባይ ከማቅረብ አኳያ የአንበሳው ድርሻ የማእከላዊው መንግስት ሁነኛ ሃላፊነት ቢሆንም፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራርም ሆነ አባላቶች መብቶች ላለመጣስ መቆጠብ አለባቸው፣ ወይም በአንድ አካባቢ መብቶች ሲጣሱ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት አለባቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ህዝብ የተለያዩ የፖለቲካ አማራጮችን እንደሚሻ የፖለቲካ ሀይሎች ሁሉ በእውነት መሰረት ላይ ቆመው መገንዘብ አለባቸው፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም ከጎሳ ማንነት ውጪ በርእዮት አለም፣ በአላማ፣ በዜግነት፣ በሰውነት ደረጃ ላይ ሆነው ፕሮግራማቸውን በይፋ ለህዝብ ማሳወቅ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ለአብነት ያህል የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው የምርጫ ማኒፌስቶ አዘጋጅተው ለኢትዮጵያ ህዝብ ያሳወቁት ? እስቲ ህሊና የፈጠረባችሁ ጠይቁ፡፡ ለማናቸውም ሰላማዊና የሰለጠነ ፖለቲካዊ ፕሮግራም ማዘጋጀት የማእከላዊውን መንግስት በሰለጠነ መንገድ ለመገዳደር ከሚረዱ ዘዴዎች አንዱ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳቦች በሚስተናገዱበት ሀገር ለሀገር የሚጠቅሙ ሀሳቦች ሊንሸራሸሩ ይቸላቸዋል፡፡
ለሀገሪቱ አንድነት የሚበጀው ቁምነገር አማራጭ ሀሳቦችን መቀበል ነው፡፡ የአንድ ገዢ ቡድን ወይም የአንድ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ሃሳብና ፕሮራም ብቻ ለሀገሪቱ አንድነት የሚበጅ አይመስለኝም ፡፡ ስለሆነም መንግስትና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደመሃል መንገድ ድረስ በመምጣት፣ በተለይም የሀገሪቱን አንድነት በተመለከተ መነጋገራቸው የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ የሀገሪቱ አንድነት እና ሉአላዊነት ከፖለቲካ ይቀድማል፡፡ መጀመሪያ ኢትዮጵያ ተብላ ስለምትታወቅ ታሪካዊት ሀገር በተመለከተ መጨነቅ መጠበብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ባሻግር የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ምን እንደሆነ በቅጡ ማጥናት አለባቸው፡፡ እንደው ዝም ብሎ የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ህዝብ ላይ መጫን የትም የሚያደርስ አይመስለኝም፡፡The unity and sovereignty of the country come before politics.
በብሔራዊ ደረጃ ተደራጅተው የፖለቲካ ፓርቲ የመሰረቱት ድርጅቶች ምን ያህል ይሆናሉ? የትኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው ለሀገር መድህን የሚሆኑ ሀሳቦች በፖለቲካ ፕሮግራማቸው ላይ ያሰፈሩት ? የትኞቹ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው የምርጫ ማኒፌስቶ ያዘጋጁት ? የትኞቹ ናቸው ለኢትዮጵያ ሉአላዊነትና አንድነት የሚደማ ልብ ያላቸው ? መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ኢትዮጵያውያን ትቼዋለሁ፡፡ በእኔ አስተያየት አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች መሰረታቸው ጎሳ ላይ የቆመ ነው፡፡ እነኚህ ራእያቸው አላማቸው በክልላቸው ወይም ወክለነዋል የሚሉትን ጎሳ ጥቅም ለማሳካት ነው፡፡ እነርሱ በብሔራዊ ደረጃ ተጽእኖ ለመፍጠር አይቻላቸውም፡፡ የእነርሱ ዋነኛ አላማ የጎሳ እና የጎሳ ብሔርተኝነት ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ጎሰኞችም ሆኑ የጎሳ ብሔርተኞች በብሔራዊ ደረጃ ተጽእኖ መፍጠር አይቻላቸውም፡፡ ይገባኛል የጊዜው የኢትዮጵያ የፖለቲካ በአመዛኙ በዘር ወይም በጎሳ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በጎሳ ፖለቲካ አኳያ ከተደራጁት የፖለቲካ ድርጅቶች መሃከል ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉት ከሁለት የሚበልጡ ሀይሎች አይሆኑም፡፡ ሌሎቹ የሃይል ሚዛኑ ወዳደላበት የሚያጋድሉ ናቸው፡፡ ይህ ከትሮይ ፈረስነት ባሻግር የትም የሚያደርስ አይደለም፡፡ የጎሳ ፖለቲካ አረማጆች ሃሳብ የላቸውም፡፡ የእነርሱ መነሻ ብሶት ነው፡፡ ከብዙ አመታት በፊት በሁለት ማህበረሰቦች መሃከል የተከሰቱ ግጭቶችን በማጉላት ወይም ያልነበሩ በደሎችን በማጎን የሚመሰረቱ ናቸው፡፡ የዘር ፖለቲካ እኛ እና አነርሱ በማለት በህዝብ መሃከል ልዩነትን ያጎላሉ፡፡ ፖለቲካ በጎሳ መሰረት ላይ ሲሆን መዘዙ ዘመናት ተሻጋሪ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሰዎች በጎሳቸው ተደራጅተው ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውን ለማበልጸግ ቢሰሩ ክፋት የለውም፡፡ ሰዎች በጎሳ ተደራጅተው የአረንጓዴ ልማት ቢመሰርቱ ውጤት ያለው ይመስለኛል፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ኢትዮጵያውያን የተፎካካሪ የፖለቲካ ሀይሎች ከርእዮት አለም አኳያ ተደራጅተው ፣ የራሳቸውን አቋም በመያዝ( የሌላ ፖለቲካ ድርጅት ርእዮት አለም መሸከም አይጠቅማቸውም፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተፎካካሪዎች መከዳትም፣ መክዳትም( ከሃዲና፣ የተከዱ ) ባህሪያቸውን አሽቀንጥረው በመጣል ፣የትብብርና አንድነት መንፈስ ቢከተሉ ኢትዮጵያ ትጠቀማለች፡፡ ( ለአብነት ያህል አንዳንድ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ድርጅት አመራሮችን ታሪክ ለሚመረምር ግለሰብ እርስበርሳቸው ሳይቀር አሳዛኝ የርስበርስ ክሀደት ታሪክ አላቸው፡፡ ለመሆኑ የሞራል ልእናን የሚያከብሩ ምን ያህሉት ነበሩ መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋለሁ፡፡)
እውን አሁን ከገባንበት የፖለቲካ ማጥ ውስጥ ሊያወጣን የሚችል አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ በኢትዮጵያ ምድር ይገኝ ይሆን መልሱን ለኢትዮጵያ ህዝብ ትቼዋለሁ፡፡ በእኔ አስተያየት የምንኖረውና መወሰን የምንችለው በእጃችን ባለ ነገር ይመስለኛል፡፡ በመጪዎቹ ወራቶች በኢትዮጵያ በሚካሄደው የምርጫ ውጤት መጨረሻ ላይ ሁለት ነገሮች እውን ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
1.አሁን ያለው መንግስት ምርጫውን በማሸነፍ ሀገሪቱን ሊመራ ይቻለዋል የሚል ግምት አለኝ
- አሁን ያለው መንግስት ፣በጎሳ አኳያ የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በብሔራዊ ደረጃ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ከአገኙት የሕዝብ ድምጽ አኳያ የጥምር መንግስት ሊመሰረቱ የሚችሉ ይመስለኛል:: ሁለተኛው አማራጭ እንዴት እውን መሆን እንደሚችል ሲታሰብ ግራ ያጋባል፡፡ ለማናቸውም በሁለተኛው አማራጭ የሚከተሉት ሁኔታዎች ( ሁነቶች) ታሳቢ መሆን ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
– ሁሉንም ነገሮች ህጋዊ ለማድረግ ከባድ ይመስላል ፡፡ እንዲህ አይነት የስልጣን ክፍፍልን እውን ለማድረግ እንዴት እንደሚቻል ከወዲሁ ማወቅ ወይም መተንበይ አይቻልም፡፡ ይህ በጠላትነት የሚፈላለጉ ቡድኖችን በአንድ ጎጆ ውስጥ እንደማስቀመጥ ይቆጠራል፡፡ This is like keeping enemies in the same cage.
– የመከላከያ ሰራዊትና የመሳሰሉትን መንግስታዊ ተቋማት እንደገና ለማዋቀር ግዴታ ይጥላል፡፡
– በአሁኗ ኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስቱ ወኪሎች በመላው ሀገሪቱ ይገኛሉ፡፡ እነኚህ የገዢው ፓርቲ ወኪሎች ያለው ስርአት እንዲቀጥል የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ሥለሆነም እንዲህ አይነት የጥምር መንግስት ከእነርሱ አኳያ ተቀባይነት ያለው አይመስለኝም፡፡ የተለያዩ ሰናክሎችን ሊደቅኑ ይችላሉ፡፡
– ከላይ ካሰፈርኳቸው ባሻግር አንዳንድ አክራሪ የጎሳ ቡድን አባላት የጥምር መንግስቱን አንቀበልም የሚል ሀሳብ ይኖራቸዋል፡፡ እነርሱ ለኢትዮጵያ የሚደማ ልብ የላቸውም፡፡ የእነርሱ ህልምና ምኞት የራሳቸውን ጎጆ ቀልሰው ለመኖር ነው፡፡ ለአንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች ወይም አመራሮች የኢትዮጵያ አንድነትና የሀገር ግንባታ አጀንዳ አንጻራዊ ነው፡፡ በእነርሱ አረዳድ ወይም ፍላጎት የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈልጉት የሚመሩት የጎሳ ፖለቲካ ድርጅት በብሔራዊ ደረጃ የበላይነት በሚቀዳጅበት መልኩ ነው፡፡ እኛ እነርሱ ምን እንደሚፈልጉ ለመረዳት ያስቸግረናል፡፡
For some of them, the Ethiopian unity and nation-state building agenda are conditional. According to them, the idea can be ‘considered’ as they control their ethnic group and gain influence at the national level. We do not understand what they will do
- በጣም አንገብጋቢ የፖለቲካ ጉዳዮች በሀገሪቱ የፖለቲካ መልክዓምድር ላይ ይገኛሉ ፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሀ. ከኤርትራ ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በሞራልና እውነት መሰረት ላይ ሆኖ የድንበሩን ጉዳይ መጨረስ
ለ. ከትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ጋር የሚደረገው ጦርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት
ማግኘት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ( በሌላ አነጋገር በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሀገር ሀብት ዝርፊያ እጃቸው ያለበት ሁሉ ተይዘው በፍትህ አደባባይ መቆም አለባቸው፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩ ሀጢያቶችን( ወይም ችግሮቻችንን) ሁሉ ህውሃትን በመቅጣት ብቻ ማጥፋት አይቻልም፡፡ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የተከለብንን የዘውግ ፖለቲካ መርዝን በአዋጅ በአንድ ቀን ለመከልከል አዳጋች ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግን ቀና አመለካከት ካለ ለማምከን ኢትዮጵያውያን ምሁራን ሙሉ ቁጭ ብለው የሚወያዩበት መድረክ ቢከፈት መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡)
ሐ. የአዲስ አበባ ጉዳይ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል
መ. በትግራይና አማራ ክልሎች መሃከል ያለው ድንበር ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነት ወዘተ ባደረጉ እውነታዎች ላይ ተመስርቶ ህጋዊ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ሠ. ሕገመንግስቱ ስለሚሻሻልበት መንገድ የኢትዮጵያ መንግስት በዋነኛነት፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች የሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል እና የሙያ ማህበር መሪዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና የምሁራን ተወካዮች በተገኙበት አንድ ብሔራዊ መድረክ ላይ መወያየት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
- ከላይ የተቀሰኳቸው አንኳር አጀንዳዎችና ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች የጥምር መንግስት ለመመስረት በጣም የተወሳሰቡ እና ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እንዲህ አይነት ወሳኝ ችግሮችን ለመፍታት በተለይም የኢትዮጵያ መንግስትና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ሌሎች ከላይ የጠቀስኳቸው አካላት በቅንነትና እውነት መሰረት ላይ ሆነው መነጋገር አለባቸው፡፡
- ረግረጋማ ቦታውን የሚያቋርጡት ፈረሶች ትክክለኛ መሆን እንደሚገባቸው (“Swapping horses while crossing streams is not appropriate ) ሁሉ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ ተፎካካሪዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅንነት በመነጋገር ኢትዮጵያ ከገባችበት የፖለቲካ አጣብቂኝ እንድትወጣ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለሀገሪቱ ህልውና እና አንድነት የሚበጅ ነው፡፡
- እንደ መደምደሚያ
መንግስትን በምክንያት ሳይሆን ፣ በስሜት ብቻ ተነስቶ መደገፍ ወይም መቃወም፣ በሌላ የሳንቲሙ ግልባጭ የሚገኙትን የፖለቲካ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መደግፍ ወይም መቃወም ጊዜው ያለፈበት ይመስለኛል፡፡ ይህ የዋህነት ስሜት ነው፡፡ በስሜት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊ የነበረው አብዝሃው ህብረተሰብ ወደ ህሊናው የተመለሰ ይመስላል፡፡ ያ በብዙ ተስፋ ተሞልቶ የነበረው አብዝሃው ህዝብ ዛሬ ለህይወቱና ለሀገሩ ያለው ምልከታ በጭንቀትና ሃሳብ ላይ የተሞላ ይመስላል፡፡ የሕይወታችን አውድ በጨለማና ብርሃን መሃከል ያለ ነው፡፡ ( ልክ ቀኑ አልፎ ጸሃይ ስትጠልቅ እንደማለት ነው) ጥያቄው ይነጋል ወይንስ ይጨልማል ?የሚለው ነው፡፡ መጪው ግዜ የብርሃን ዘመን ይሆን ? ወይንስ መጪው ግዜ የጨለማ ዘመን ይሆናል ? የሚሏቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ የነሳቸው ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎች ናቸው፡፡
There is a twilight-like description of the state in which we live. The question is, is it dusk or dawn? It is the dawn of a better era for all beloved Ethiopians ?. It is dusk for all beloved Ethiopians ?
በሚያሳዝን መልኩ ለግዜው በኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ቸግርን ለመፍታት ትክክለኛ መፍትሔ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በተለይም የጎሳ ፖለቲካ ለማምከን አሁን ድረስ አልተቻለም፡፡ በእኔ በኩል ሲቪክ ማህበራት ፣ ነጻ መንፈስ ያላቸው ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖት ተቋማት ስለ ጎሳ ፖለቲካ መርዝነት በተመለከተ ህዝብን ማስተማር አለባቸው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ እንደተጠመደ ፈንጂ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያን የፖለቲካ አቅጣጫ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ የዶለውን የጎሳ ፖለቲካን መርዝ ለማምከን እውቀት ግድ ይላል፡፡
ላለፉት ሃያ ሰባትና ከዛ በላይ በነበሩት አመታት የወያኔ አገዛዝ ዜጎች በፖለቲካው አኳያ ንቁ ተሳታፊ እንዳይሆኑ ጭቆና ያካሂድ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ነጻ በሆኑ የሙያ ማህበራት እና ሲቪል ማህበራት ውስጥ መደራጀት ወይም አባል መሆን አደጋ ነበረው፡፡ ለአብነት ያህል በአንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፣ አቶ ዳዊ ኢብራሂም ይመራ በነበረው የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበር አባላት ላይ የደረሰውን ግፍ አይዘነጋም፡፡ ለነጻ ማህበር እውን መሆን ሲታገሉ ነበር መምህር አወቀ፣ መምህርና የሰብዓዊ መብት ታጋይ ጋሼ አሰፋ ማሩ፣ ጋዜጠኛ ተስፋዬ ታደሰ በወያኔ ሹምባሾች በአደባባይ የተገደሉት፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ነጻና ገለልተኛ ምርጫ ውድድር ለማየት አልታደልንም፡፡ ( ምናልባት የግንቦት 1997 ዓ.ም. ነጻና ገለልተኛ ቢሆንም ውጤቱ አላማረም ነበር፡፡) ከዚህ ባሻግር አብዝሃው የኢትዮጵያ ህዝብ አልተደራጀም ወይም በድርጅት አልታቀፈም፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ( ሂደት) ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መሆን አልተቻለውም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የፖለቲካው ሁኔታ ሰርአት የያዘ እና የሰለጠነ እንዲሆን በኢትዮጵያ የተለያዩ ግዛቶች የሰብዓዊ መብት የሚጥሱ ቡድኖችን በፍትህ አደባባይ በማቅረብ ሂደቱ ላይ መተባበር ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ወንጀሎች በብረት አንጋቾች ወይም ጉልበተኞች እየተፈጸሙ እያየን ዝም ለማለት ህሊናችን አይፈቅድልንም፡፡
ውስብስብ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት የሚፈልግ መንግስት፣ እንዲሁም የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በሞራልና እውነት መሰረት ላይ መቆም ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ በእኔ አስተያየት መሬት ላይ ያሉ የፖለቲካ ችግሮችን ምንም ሳይቀባቡ ከነቀሱ በኋላ ወደ መፍትሔው መሄዱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ያጋጠሙንን ችግሮች ለማስወገድ ሁልግዜ በራሳችን መንገድ ወይም ለራሳችን በሚጠቅመን መልኩ ብቻ መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ከተጨባጩ እውነታ በመነሳት ነው ለገጠመን ችግር መፍትሔ መፈለገን ያለብን፡፡ የተከሰተው ፖለቲካዊ ችግር ራሱ በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ ስትራቴጂክ እና መሰረታዊ የሆነ ውሳኔ ግድ ይላል፡፡
ለአብነት ያህል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2016 በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጭ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ አለማዎች የነበራቸው ቢሆንም ገዢውን የወያኔ አገዛዝ የሚቃወሙ ነበሩ፡፡ ዛሬ እ.ኤ.አ. 2020 የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጣኑን በያዘው የፖለቲካ ፓርቲ ያላቸው አቋም በእጅጉ የተለያየ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር በመሃላቸው ያለው ልዩነት በእጅጉ የተለያየ ነው፡፡
በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ እጃቸውን የሚዶሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አይጠፉም፡፡ ለአብነት ያህል ግብጽ በሀገራችን ሰላም እንዳይሰፍን የተወሳሰበ ሴራ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ከምእራባውያን ሀገራት ጋር፣ በተለይም ከምእራብ አውሮፓ አንዳንድ ሀገራት ጋር የነበረው የውጭ ግንኙነት እየተቀዛቀዘ ስለመሆኑ በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መነገሩ አሳሳቢ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያ በውጭ ዲፕሎማሲ የእውቀት ዘርፍ ልምድ ያላቸውን በሳል ዲፕሎማቶችን በምእራብ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ወይም ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች መመደብ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
ባለፉት ሁለት አስርተ አመታት ከነበሩ የፖለቲካ ችግሮች ባሻግር፣ ዛሬም ሆነ ነገ ተነገ ወዲያ የሚቀፈቀፉ ፖለቲካዊ ችግሮቻችን ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እንቅልፍ ሊነሳ ይገባል፡፡ መንግስት በኢትዮጵያ ምድር ለሚከሰቱ ፖለቲካዊ ችግሮች መሰረታዊ ምክንያቶች በተመለከተ ( ለአብነት ያህል የጎሳ ፌዴራሊዝም የሚፈቅደውን ህገመንግስቱ ስለመሻሻሉ ) ስለሰጠው ትኩረት የታወቀ ጉዳይ የለም፡፡ በእኔ ግምት መንግስት ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ እስኪገጥማት የሚጠብቅ አይመስለኝም፡፡
እውን መንግስት ኢትዮጵያ የምትገኝበትን አስጨናቂ የፖለቲካ ችግር ችላ በማለት ስልጣኑን ለማጠናከር ብቻ እየሰራ የሚገኝ ነውን ? መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋለሁ፡፡ በነገራችን አንድ ሀይሉ አደጋ ላይ የወደቀበት አካል ጭንቅላት ሳይሆን ጡንቻ ነው የሚጠቀመው፡፡ ጉልበት ያታልላል፡፡ በጡንቻ የሚያምን ግለሰብ ወይም ቡድን የሚሸነፍ አይመስለውም፡፡ ሆኖም ግን ትንሽ ቆይቶ ወደ ቅዠትነት ይቆጠራል፡፡ በጉልበት ወይም ጡንቻ የሚመኩ ግለሰብ ወይም ቡድን መጨረሻው አያምርም፣ መቼ እንደሚወድቅ ሳያውቀው ድንገት ይወደቃል፡፡ በነገራችን ላይ በጥቅጥቅ ጫካ የሚመሰለው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳይ ፣ በመንግስትፍላጎትና አቅም ብቻ የሚፈታ አይመስለኝም፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት መንግስትና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ላይ ሆነውም የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት ይቸግራቸዋል፡፡ የኢትዮጵያን ውስብስብ ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት ፍላጎቱ ካለ አንድነትና ትብብር ምትክ አይገኝለትም፡፡ እውን ሁሉም ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ሀይሎች ለአንድነት ዝግጁ ናቸውን ? መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋለሁ ፡፡ በእኔ በኩል ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከተበተባቸው የጎሳ ከረጢት ውስጥ በመውጣት ለኢትዮጵያ አንድነት ካልታገሉ የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ ሊወደቅ ይችላል ብዬ እሰጋለሁ፡፡ አንድነታችንን ለማጠንከር ከዘገየን ችግሮቻችን እየተወሳሰቡ ከመሄዳቸው ባሻግር ጸሎቱ ምላሽ እንዳላገኘለት የሃይማኖት ሰው እንቆጠራለን፡፡ እኛ በመጪዎቹ ጊዜያት ሊመጡ ከሚችሉ አደጋዎች ራሳችንን ለመከላከል ዝግጅታችን ምን ይሆን ? መልሳችን አዎን የሚል ከሆነ ፍጥነት ያስፈልገናል፡፡ በነገራችን ላይ ከፊታችን የተደቀኑ ችግሮችን ለመፍታት የአንበሳው ድርሻ የመንግስት ይሆናል፡፡ መንግስት ደግሞ ብቻውን ሳይሆን ከህዝቡ ጋር በመተባበር ችግሮቻችን ለመፍታት የሚችል ይመስለኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳላ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች ዋነኛ ምክንያት ውስጣዊ እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡ የውጭ ሀይሎች እንደ ሁለተኛ ምክንያቶች ይቆጠራሉ፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ችግሮች በቅንነትና በአንድነት መፍታት ካልቻልን ኢትዮጵያዊ ማንነታችን አደጋ ላይ ሊወድቅ ይቻለዋል፡፡ ይህ ጽሁፍ የማንቂያ ደውል አይደለም፡፡ እኔ የማነሳቸው ፖለቲካዊ ችግሮች አሁን በመሬት ላይ የሚታዩ ፣ የሚዳሰሱ ናቸው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሰከነና በሰለጠነ መንፈስ፣ በሰላማዊ መንገድ ለችግሮቻችን መፍትሔው ምን እንደሆነ በየአካባቢያችን እንወያይበት፡፡ መንግስትና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትም፣ ኢትዮጵያዊ ምሁራኖች ሁሉ የኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም እውን እንዲሆን በሰለጠነ መንገድ መነጋገር ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
ያለንበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ መጪው ጊዜ ብሩህ ተስፋ ይዞ ይማጣል ብሎ መደስኮር እራስን እንደማሞኘት ይቆጠራል፡፡ በአጭሩ ያለንበት የፖለቲካ ችግር እንቅልፍ የሚነሳ ነው፡፡ ስለሆነም የችግሩን እውነተኝነት በመቀበል ሁላችንም የችግሩ አካል መሆናችንን ተረድተን ለችግሮቻችን ተባብረን መፍትሔ መፈለግ የህለውና ጉዳይ መሆኑን በቅን ልቦና እንረዳ፡፡ እራሳችንን ማጭበርበር የለብንም፡፡ ላለፉት ሰላሳ አመታት ውሸት አፈር ድሜ እንዳስጋጠን ዛሬ ቢያንስ እንረዳ፡፡ በዋነኝነትና በፍጥነት የሀገራችንን አንድነት እናስጠብቅ፡፡ ሌሎች ነገሮች በብሔራዊ ውይይት የሚፈቱ ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻግር መንግስት፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በፍጥነት በእውነት እና ሞራል መሰረት ፤ላይ ቆመው እንዲወያዩ፣ እንዲነጋገሩ፣ እንዲተማመኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በሰለጠነ መንገድ መርዳት ያለበት ይመስለኛል፡፡
Our situation has no place for a foolish optimist. However, let us focus on the country’s unity, and we can fix the rest through dialogue. Knowing we are without an alternative, let us shape and force the government to act with our country’s peace and unity in its heart and action. In the end, we, the people, are the agents of our fate
የግል ማስታወሻ፡-
እኔ ከላይ በሶስት ክፍሎች አስተያየት ለማቀርብ መንፈሴ ያስገደደኝ መንግስትን ወይም የተፎካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ለመተቸት አይደለም፡፡ ውዳሴ ከንቱም ለማቅረብም አይደለም፡፡ እኔ ለማንሳት የሞከርኩት በመሬት ላይ በገሃድ በግልጽ ስለሚታየው የኢትዮጵያ መሰረታዊ የፖለቲካ ችግሮቻችን ላይ ነው፡፡
በእኔ አስተሳሰብ የኢትዮጵያን ችግሮች ሁሉ መንግስት ብቻውን የሚፈታው አይመስለኝም፡፡ ከችግሮች ጋር ለብዙ አመታት ኖረናል ብዬም አስባለሁ፡፡ ምንም እንኳን ህገመንግስቱ እንዲሻሻል የተለያዩ ምሁራን አስተያየት ቢሰጡም ሰሚ ጆሮ አላጋኙም፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያው ህገ መንግስት የዲምክራሲና ሰብዓዊ መብቶች በተመለከተ ጠቃሚ አንቀጾችን የያዘ ስለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ሊሻሻል የሚገባው ግን መሻሻል አለበት፡፡ በተለይም የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርዓት የሚፈቅደው አንቀጽ ሊሻሻል ይገባዋል፡፡
በመጨረሻም በድጋሚ የኢትዮጵያ አንድነት ትኩርት እንዲሰጠው ሳስታውስ በአክብሮት ነው፡፡ ይህ የፌዝ ወይም የለበጣ መልእክት አይደለም፡፡ መልእክቱ ከልብ የመነጨ፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ ከነሳቸው ኢትዮጵያውያን የተላከ ነው፡፡ ይገባኛል ጥቂቶች ወይም ብዙዎች በዚህ መልእክት ልትቆጡ ወይም ጸረ ፌዴራሊዝም በማለት እምቡር እምቡር ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ አንዳንዶች የቀድሞ ስርዓት ናፋቂ የሚሉ አይጠፉም፡፡ አንዳንዶች የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞችን ሁሉ ትኩረት የማይሰጥ የሚል ድምዳሜ ላይ ልትደርሱ ትችላላችሁ፡፡ እኔ ከማናችሁም ጋር አይደለሁም፡፡ ወይም የተጠቀሱት መላ ምቶች እኔን የሚመለከቱ አይደሉም፡፡ እኔ የማናቸውም የፖለቲካ ድርጅቶች ነቃፊም ሆነ አሸርጋጅ አይደለሁም፡፡ የእኔ እራስ ምታት የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ችግር ወይም አሳሳቢው የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ በእኔ አመለካከት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች ሁሉ ሰራሄ መፍትሔ የሚጋኙት በሰውነት ደረጃ ላይ ስንቆም ነው የሚል ነው፡፡
Our situation has no place for a foolish optimist. However, let us focus on the country’s unity, and we can fix the rest through dialogue. Knowing we are without an alternative, let us shape and force the government to act with our country’s peace and unity in its heart and action. In the end, we, the people, are the agents of our fate.
እንደ መደምደሚያ
በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ ሴይጣናዊ ችግሮች ሁሉ ስረመሰረቱ ወይም ምክንያቱ የኢትዮጵያ ህገመንግስት ነው ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታም ዝግጁ ነኝ፡፡ ይህ ህገመንግስት በኢትዮጵያ የጎሳ ፌዴሬሽን ግዛት እውን እንዲሆን የፈቀደ ነው፡፡ በአለም ላይ ካሉት ሀገራት ሁሉ የጎሳ ፌዴሬሽን ግዛት እውን እንዲሆን የፈቀደው የኢትዮጵያ ህገመንግስት ብቻ ነው፡፡ በአለም ላይ ከሚገኙትት ሀገራት ውስጥ( በተባበሩት መንግስታት እውቅና ያለቸውን ሀገራት ማለቴ ነው፡፡) ከኢትዮጵያው ህገ መንግስት በቀር የጎሳ ፌዴሬሽን እውን እንዲሆን የሚፈቅድ የለም፡፡ ( ወይም በአሁኑ ዘመን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡) የኢትዮጵያው ህገ መንግስት በጎሳ ላይ የተመሰረቱ ድንብሮችን የሚፈቅድም ነው፡፡ አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች መሰረታቸው በጎሳ ላይ የተመሰረተው በዚሁ ህገመንግስት ፈቃጅነት ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ከአፍሪካ ሀገራት ሁሉ በመታወቂያ ካርድ ላይ የጎሳን ማንነት እንዲገለጽ የሚፈቅደው ይሄው ህገመንግስት ነው፡፡ በመኪናዎች ታርጋ ላይ ሳይቀር የጎሳ ማንነት መጻፉ ሲታይ ህሊናን ያደማል፣ ሆድን ይበጠብጣል፡፡ ባለፉት ሰላሳ አመታት የጸደቀውን የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ማሻሻል ወይም መቀየር ከባድ እንደሆነ ይገባኛል ፡፡ የጥቂት ጊዜያት ስራም አይዶለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና መንግሰት በቀና መንፈስ ከተነሳ ማሻሻል ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የጎሳ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ይበጃል የሚሉ ምሁራንን በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ አይ የጎሳ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም የሚሉ ምሁራንን ጥናታዊ ጽሁፎቻቸውን፣ ለኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች፣ ለተፎካካሪ የፖለቲካ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሢቪል ማህበር ተወካዮች፣ ወዘተ በተገኙበት እንዲያቀርቡ በመጋበዝ ውሳኔውን ለህዝብ የህሊና ፍርድ እንዲተው ሳስታውስ በአክብሮት ነው፡፡ ነጻነቱን የተጎናጸፈ ህዝብ፣ የሚበጀውን የሚያውቀው ህዝብ በነጻ መንፈስ የህሊና ውሳኔ ቢሰጥ ከመሰረታዊ የፖለቲካ ችግሮቻችን የምንገላገል ይመስለኛል፡፡
በእኔ በኩል የኢትዮጵያ መሰረታዊ የፖለቲካ ችግሮች ሁሉ በዲሞክራቲክ ፌዴራሊዝም ስርዓት ስር ይፈታሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በዲሞክራቲክ ፌዴራሊዝም ስርዓት በኢትዮጵያ የሚገኙት ከ100 በላይ ጎሳዎች ሁሉ ኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በማድረግ የኢትዮጵያን አንድነት አስተማማኝ ማድረግ ይቻላል፡፡
Our situation has no place for a foolish optimist. However, let us focus on the country’s unity, and we can fix the rest through dialogue. Knowing we are without an alternative, let us shape and force the government to act with our country’s peace and unity in its heart and action. In the end, we, the people, are the agents of our fate.
በመጨረሻም የጎሳ ፖለቲካ ይበጃታል የሚል የአንድ በአካል የማላውቀውን ኢትዮጵያዊ ወንድሜን ተምሳሌት አድርጌ ላቅርብና ጽሁፌን ልቋጭ፡፡ ( የጎሳ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ይበጃታል የሚሉ ወንድሞች፣እህቶች፣ አባቶች ሞለተው ተርፈዋል፡፡)
የጎሳ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ይበጃታል የምትል ወንድሜ ሆይ ስለ ጎሣ ፖለቲካ አደገኛነት እስከዛሬ ስትዋኝበት ከርመህ በራስህ ተመክሮ ያልተማርከውን ካንተ ጋራ እንኪያ ሠላምታና ጉንጭ የሚያለፋ ያለም አይመስለኝም ።
አንተ ሥልጣን ላይ ለመክረም ወይም በቀቢጸ ተስፋ ነገ ተነገወዲያ ስልጣን ላይ ቁጢጥ ለማለት ድርጅትህ የሰጠህን ተልዕኮ ጊዜ መፍጃ አጀንዳ እየበላህ ነው ።
ድርጅትህም ሆነ አንተ ዝንተ ዓለማችሁን የጎሣ መሣፍንቶች ሆናችሁ መዝለቅ የመረጣችሁ ሟቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ያበጇችሁ ወይም በእርሳቸው መንገድ ለመጓዝ የመረጣችሁ ፖለቲከኛ ናችሁ ብዬ አስባለሁ።
አገራችን ኢትዮጵያና ሕዝቧ ግን ሰፊና ትልቅ ናቸው ።
የእናንተ አይነት ደካማና ለአገር የማይጠቅም የፖለቲካ ቅኝት አይመጥናትም ።
ትናንት ታላቋ ትግራይ ለመመሥረት ብለው ሲዋትቱ የነበሩ ቅዠታቸው መክኖ እያየህ ዛሬ ደግሞ ያንኑ ታላቋ ክልሌ ብለህ ለመንደርደር ታቆበቁባለህ ይህ ለሰሚው ግራ ነው ።
የሚበለፅገው አገርና ሕዝብ እንጂ አንድ ጎሣ አይደለም ።
አሁን ለናንተ ይሄ ነው ያ ነው ብሎ ለማስተማር ጊዜን ማጥፋት ነው ።
ፖለቲካ ዕውቀትና ጥበብ እንጂ የቆዳ ልፊያ አይደለም ። ቆዳ ማልፋትና ካንተ ጋር እሰጥ እገባ ልዩነት የለውም ። ብትታሽ ብትታሽ ….
ሠላሣ ዓመት መማርና ርዕዮትህን ማስተካከል ካቃተህ መቼም አትማርም ።
አንተ ለማስቀጠል ከምትፈልገው የማይጠቅም የፖለቲካ ሥርዓት በላይ ዐዋቂዎቹ ቀድመውህ ከታች የተጠቀሰውን መፈክር ካነሱ ዓመታት አስቆጥረዋል ።
የጎሣ ፖለቲካ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ስለማይበጃት የኢትዮጵያ መንግስት፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ የሲቪልና የሙያ ማህበራት ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የሓይማኖት ተወካዮች፣ ኢትዮጵያዊ ምሁራን በተገኙበት እጅግ በሰለጠነ፣ ዲሞክራቲክ መንገድ እና በጥናት ላይ በመሰረተ፣ የዒትዮጵያ ህዝብ ይሁንታ ተሰጥቶት በህግ እንዲታገድ ኢትዮጵያውያን ሲማጸኑ አመታት ተቆጥሯል ።
አራት ነጥብ ።
በነገራችን ላይ የብሔርተኝነት ጥያቄው ማቆሚያ የለውም፡፡ ስለሆነም በቅድሚያ የጋራ መግባባት አለብን፡፡ ቁጭ ብለን ስለ የጋራ ሀገራችን ጉዳይ ቁጭ ብለን ወደ አንድ ብሔራዊ መግባባት መድረስ አለብን፡፡ አንዱ ወንድማችን ድንገት ተነስቶ የራሴን ክልል ብቻ ካለ ፡፡ አደጋው ለሁላችንም ነው፡፡ እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ለሀገር የሚበጅ አይደለም፡፡ ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያ ከጎሳ አስተሳሰብ ውጪ ትገኛለች ብዬ አስባለሁ፡፡ ብሔር ወይም የጎሳ አስተሳሰብ ከአምክንዮ ይልቅ ወደ ስሜት እንደሚያጋድል ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሰከነ መንፈስ ተነጋገሩበት፣ መፍትሔም ፈልጉ፡፡ ይህ የእኔ ሀሳብ ነው፡፡ ሃሳቤን ደግሞ በሌሎች ላይ ለመጫን በፍጹም አልፈልግም፡፡ ለሀገር መድህን ሊሆን ይችላል የሚል ሀሳብ ማቅረብ ወይም መሰንዘር ተፈጥሮአዊ መብቴ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የሚጥመውን የሚያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ወሳኝ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን የጎሳ ፖለቲካ ይጠቅመናል የምትሉ መብታችሁ መሆኑን ባውቅም፣ ሃሳብችሁ ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም በማለት እሟገታለሁ፡፡
በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ የምትገኙት አንተና መሰል የጎሳ ፖለቲካ ደጋፊዎች፣ የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ እውን እንዳይሆን፣ ታስወግዱታላችሁ ብሎ የሚጠብቅ የለም ።
ተፈጥሯችሁ ድዊነት፣ወይም በራስ ወዳድነት ላይ ተመስርቷልና አይታሰብም ።
በፖለቲካ አስተሳሰብ ልትዘምኑ ከቶውን አይቻላችሁም ተብሎ ቢጻፍ ስህተት የሚል ይኖር ይሆን ካላም ምንታደርጊዋለሽ የሚለውን የጋሼ ጥላሁንን ዘመን አይሽሬ ዜማ ከመጋበዝ ውጪ ለግዜው የምለው የለኝም ።
በነገራችን ላይ በጎሣ ካባ ተከልላቹህ ታላቋን ስእል ኢትዮጵያን ረስታችኋልና መርሳታችሁ ወይም ሆነ ብላችሁ ችላ ማለታችሁ የመጨረሻ ምርጫችሁ ነው ።
ለኢትዮጵያ የሚበጃትን የፖለቲካ እሳቤ በሕዝብ ይሁንታ፣ ነጻነት፣ ፍላጎት ኃያልነት፣ በዲሞክራክ ፌዴራላዊ ስርዓት ግን ይፈፀማል ።
ከተሻለህ ጤና ይስጥልኝ !
ፌዴራሊዝም አንድ ብቻ ነው
‹‹ ዴሞክራሲያዊ››
‹‹ ሀቀኛ ፌዴራሊዝም ››
ፌዝ በጎሰኞች ሚስጥር ኪስ ውስጥ ብቻ ትገኛለች፡፡
ዴሞክራሲ መሰረቱ ሰው እንጂ የጎሳ አጥር ክልል አይደለም፡፡
ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም.