>
5:33 pm - Friday December 5, 1394

ኦሕዴድ/ብልፅግና አዲስ አበባን የኦሮሞ ንብረት ለማድረግ የጀመረውን  ዘመቻ ያቁም...!!! (ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ)

ኦሕዴድ/ብልፅግና አዲስ አበባን የኦሮሞ ንብረት ለማድረግ የጀመረውን  ዘመቻ ያቁም…!!!

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ

ኦህዴድ ብልፅግና ቤተ-መንግሥት ከገባ ጀምሮ የመላ ኢትዮጵያውያን ብሎም የአፍሪካ መዲና የሆነቺውን አዲስ አበባን በኦሮማዊነት መንፈስ ለመቆጣጠር እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡
ከሰሞኑ ከተማዋን የኦሮሞ ብቻ መዲና ለማድረግ እና ኦሮማዊ ስነ-ልቦናን ለማላበስ ኦሕዴድ/ብልፅግና የሕንፃዎች ግንባታ ዘመቻን ጀምሯል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በ1.8 ቢሊዮን ብር ወጭ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንፃን፣ በ1.5 ቢሊዮን ብር ወጭ የኦሮሚያ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ሕንፃን፣ በ1 ቢሊዮን ብር የኦሮሞ ታጋዮች ፋውንዴሽን ሕንፃን እንዲሁም በ7 መቶ ሚሊዮን ብር ወጭ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ሕንፃን በአዲስ አበባ ለመገንባት ሥራዎች ጀምሯል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ህወሃት ሲያደርግ እንደ ነበርው የህዝብ ሃብት እየተዘረፈ ለነገድ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ለሚመሯቸው የፖለቲካ ኤሊቶች ጥቅም ማስገኛ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ እውነታ ነው፡፡ በህገ-መንግስቱ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንደሆነች ባልተፈቀደበት ሁኔታ ይህ የተወሰደው እርምጃ አዲስ አበባን በኦሮሞ ስነ ልቦና ለመሥራት በሚል ሽፋን የኦሮሞ የነገድ ፓለቲካ ኤሊቶች ጥቅም ማጋበሻ እንዲሆኑ የታለሙ መሆናቸውን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ያምናል፡፡
ይህም በ16እና በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመናት ተቋርጦ የነበረውን የገዳ ስርዓት ወረራ ለማስቀጠል እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴም አካል ነው፡፡
አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት ይህ ወረራ አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ለመዋጥ ወይም ለማጥፋት ያለመ ነው፡፡ ‹በረራ› በመባል ትታወቅ የነበረችው ጥንታዊቷ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ እንደ ገና የዛሬዋን አዲስ አበባ እስከቆረቆሩበት ጊዜ ድረስ ፈርሳ የቆየችው በገዳ ወረራ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡ በ16ኛው እና በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመናት በተካሄደው የገዳ ስርዓት ወረራ ከ28 በላይ ነባር የኢትዮጵያ ነገዶች መጥፋታቸው በታሪክ የተመዘገበ ነው፡፡
በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ከመላ ኢትዮጵያ የተሰበሰቡ ነዋሪዎች ከሚገብሩት ግብር ለክልሎች ፈሰስ ከሚደረገው ድጎማ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣኖች ለነገድ የፖለቲካ ማራመጃነት እና ለግል ጥቅም ማካበቻ በማን አለብንነት የሚያባክኑት የሀገር ሃብት ተጠያቂ የሚሆኑበት ስርዓት እንዲፈጠር መላው የከተማዋ ነዋሪ በሰላማዊ ትግል አድሏዊ ከሆነ የኪራይ ሰብሳቢ አካሄድ እንቅስቃሴያቸው እንዲታቀቡ ባልደራስ በአፅንኦት ያሳስባል፡፡
ታህሳስ 14 ቀን 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
ድል ለዲሞክራሲ!
Filed in: Amharic