>

የፖለቲካ ማኅበር እንቅስቃሴ ከግለሰብ መሪዎች ጋር መቈራኘት (ከይኄይስ እውነቱ)

የፖለቲካ ማኅበር እንቅስቃሴ ከግለሰብ መሪዎች ጋር መቈራኘት

ከይኄይስ እውነቱ


በባህላዊው የኢትዮጵያ ዘውዳዊ አስተዳደር ነገሥታቱ የውጭ ወራሪ ሲመጣም ሆነ የአገር ውስጥ ውጊያ ሲኖር ሠራዊትን መርተው መዝመት የተለመደ ነው፡፡ ታዲያ አልፎ አልፎ የጦሩ ራስ የሆነው ንጉሠ ነገሥት ወይም እንደሁናቴው ንጉሥ በዐውደ ውጊያ ላይ ከተገደለ ወይም ከቆሰለ ወይም ከተማረከ ሠራዊቱ እንደሚፈታ ተስተውሏል፡፡ ንጽጽሩ ጎደሎም ቢሆን በ‹ተቃዋሚ የፖለቲካ ማኅበራትም› በተወሰነ መልኩ እየታየ ይመስላል፡፡ መሪዎቹ በአገዛዙ ሲታሠሩ የፖለቲካ ድርጅቱ እንቅስቃሴም ሲገደብ ይስተዋላል፡፡ በርግጥ በቅንነታቸው÷ በተአማኒነታቸው÷ በዓላማ ጽናታቸው÷ በቈራጥነታቸው÷ የሞራል ከፍታን በተላበሰ ሰብእናቸው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኙ የፖለቲካ ማኅበራት መሪዎች በማኅበሩ ውስጥ የሚኖራቸው ቊልፍ ሚና ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ነው፡፡ ባንፃሩም መሪዎቹ በሌሉበት ሌሎች አመራሮችና አባላት የየድርሻቸውን አይወጡም ማለት አይደለም፡፡ ባሳለፍነው ሦስት ዐሥርት ዓመታት ባገር ውስጥ የተደራጁ የፖለቲካ ማኅበራት ባገዛዞች የሚደርስባቸው ተጽእኖና ውክቢያ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በራሳቸው ውስጣዊ ድክመትና አድርባይነት ምክንያት የከሸፉት ያመዝናሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ክሽፈቱ ለሕዝብ ታማኝ የመሆንና የማገልገል ስሜት ካለመኖር፣ ከዘላቂው አገራዊ ርእይ ይልቅ ጊዜያዊ ሥልጣንና ጥቅምን የማስቀደም፣ ሕዝብን በዓላማ ዙሪያ ከማሰባሰብ ይልቅ ርስ በርስ መጠላለፍ (በአንድ ድርጅትም ውስጥ ሆነ ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ሌሎች ድርጅቶች ጋር) እና መከፋፈል፣ ዝርዝር የዓላማና የርዕዮት ጥራት አለመኖር፣ መከዳዳት ወዘተ. ይገለጻል፡፡ ይህንን የማነሳው በጐሣ ስለተደራጁት ቡድኖች አይደለም፡፡ ከመነሻው እነዚህ የፖለቲካ ማኅበራት ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ አለመታደል ሆኖ ወያኔና ኦነግ በተከሉት የጐሣ ፖለቲካና ይህንን ፍላጎታቸውን ሕጋዊ ቅርፅ የሰጡበት ሰነድ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን፣ ጐሠኛነትንና ደካማ የመንደር ‹አገዛዞችን› ወይም ቁርጥራጭ ‹አገሮችን› የሚያበረታታ በመሆኑ እንጂ፡፡ ዛሬ አንድ/ሁለት ብለን ከምንጠራቸው ውጪ ዜግነትንና አገራዊ አንድነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ እንከተላለን የሚሉት ድርጅቶች ከጐሠኞቹ የሚለዩበትን መሠረታዊ አላባዎች ከስም በስተቀር ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም፡፡

ረዘም ባለ መግቢያ የጀመርኩት ጽሑፍ ዛሬ ከውግዘትና መግለጫ ያላለፉ በስም ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ብሔራዊ ጥቅሞችና ለሕዝባችን የአገር ባለቤትነት እንታገላለን ለሚሉ፣ መሠረታቸው ጐሣ ላልሆነ እውነተኛ ተቃዋሚዎች አንዳንድ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ስላላቸው አቋም ጥያቄ ለማንሳት እና ምርጫ ከሚባለው ታንቲራ ርቀው ሕዝባቸውን ለሥርዓታዊ ለውጥ አስተባብረው እንዲያንቀሳቅሱ ጥሪ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

በቅድሚያ ሕዝብ ተስፋ የጣለበትንና በምንወደውና በምናከብረው ወንድማችን ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ስለሚመራው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጥቂት ቃል ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ እስክንድርና ባልደረቦቹ በወያኔ ወራሹ የዐቢይ አፓርታይድ አገዛዝ በግፍ ከታሰሩ እነሆ መንፈቅ ሊሞላቸው ነው፡፡ እስክንድር ኢትዮጵያ በምትባለው ግልጽ እስር ቤት በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ከጓዶቹ ጋር በጋራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ባጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ላይ የዘረኞቹ የአፓርታይድ አገዛዝ በተረኝነት መንፈስ በዜጎች ላይ የሚያደርገውን ጭፍጨፋ፣ በአገራዊ ሀብት ላይ የሚፈጸመውን ዝርፊያ፣ በሥልጣን መባለግ፣ ባጠቃላይ ሕገ ወጥ ድርጊቶች/ውንብድና ከሥር ከሥር እየተከታተለ ከማጋለጥ በተጨማሪ ለዘለቄታው መፍትሄ በሚሆኑ ሕጋዊ፣ ሥርዓታዊና መዋቅራዊ ለውጦች ላይ ሲንቀሳቀስ በጉልህ ይታይ ነበር፡፡ እሱና ጓዶቹ ነፃነታቸው በተገደበበት ጊዜ (የታሠሩ ባልደረቦቻቸውን ጉዳይ ከመከታተሉ ጎን ለጎን) ድርጅቱ የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሆነ ብገምትም፣ ፓርቲው ከተቋቋመም አጭር ጊዜ ቢሆንም ጎልቶ የወጣ ክንዋኔ (የአቋም መግለጫ፣ ውግዘት እንደተጠበቀ ሆኖ) አላስተዋልኹም፡፡ እስክንድር አገዛዙን በመገዳደር የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ለምን ተቋረጡ? በእኔ ምልከታ ባልደራስን ከሌሎች እውነተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለየት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች አንዱ ዓላማውን ለማሳካት የሚያደርገው የፖለቲካና ማኅበራዊ ቀስቃሽነት (political and social activism) ተግባሩ ይመስለኛል፡፡

ተቃዋሚዎች ዓላማቸውን፣ ርዕያቸውንና ፕሮግራማቸውን መሠረት አድርገው የራሳቸውን አጅንዳ ቀርፀው ሲንቀሳቀሱ አይስተዋልም፡፡ በአመዛኙ አገዛዙ ከዋና ጉዳይ ለማናጠብ በየጊዜው በሚወረውራቸው አጀንዳዎች ላይ ተጠምደው እናገኛቸዋለን፡፡ የኃይል ሚዛኑ የት እንዳለ በግልጽ ቢታወቅም፣ በመርህ ደረጃ አገዛዙ የሚመራው የዘር ‹ፓርቲ› (ዳግማዊ ኢሕአዴግ) ከመቶ በላይ እንደሆኑ ከሚነገርላቸው (በርካታዎቹ አገዛዙ በሚሠፍርላቸው ድርጎ አዳሪ ቢሆኑም) የጐሣ ቡድኖችና የፖለቲካ ማኅበራት (ሕግ የሚሠራበት አገር ከሆነ) አንዱና ከእነሱም እኩል ነው፡፡ ይሁን እንጂ በምድር ላይ ያለው ጽድቅ የሚነግረን ዳግማዊው ኢሕአዴግ ባሻው ጊዜ የአገዛዝ ቆቡን እያጠለቀ አጀንዳ ቀራፂ እና ለተቃዋሚዎች አዳይ፣ እሱ ሰብሳቢ፣ ፈቃጅና ከልካይ፣ በዘር ያደራጃቸውንና የሚቆጣጠራቸውን የጸጥታ ኃይሎች እያሠማረ አዋካቢና አሳሪ፣ እሱ ተለማኝ ተቃዋሚዎች ለማኝ የሆኑበትን አሠራር ነው፡፡ ይህ በሰፈነበት ስለምርጫ ማውራት አገራዊ ቧልት ካልሆነ ለኔ ትርጕም የለውም፡፡ ለዚህም ነው እውነተኛ ተቃዋሚዎች ካሉ መሥራት ያለባቸው ለእውነተኛ ምርጫ መደላድል የሚሆኑ አንኳር ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ እነዚህም ደጋግሞ እንደሚነገረው የጐሣ ፖለቲካን፣ የጐሣ ፌደራሊዝሙን፣ ዜጋውን ባገሩ ባይተዋር ያደረገውን ‹ክልል› የሚባል መዋቅርና አፓርታይዳዊ ለሆነው የጐሣ አገዛዝ ሥርዓቱ የሕግ ሽፋን የሰጠውን የወያኔ አገር አፍራሽ ‹ሕገ መንግሥት› ለመቀየር ሕዝብን የማንቀሳቀስ ግዙፍ ሥራ ነው፡፡ 

ከፍ ብለን ያነሳናቸውን የወያኔን ቅራቅንቦዎች እንደተሸከምን የምን ምርጫ ነው? ኦሮሙማ በአዲስ አበባም ሆነ በመላው አገሪቱ እያካሄድ የሚገኘውን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አኮስምኖ ዘረኝነትን የሚያደልብ ፕሮጀክት ይዞ የምን ምርጫ ነው? ስለሆነም ጥያቄው ዐቢይና ዘመዶቹ ሊያካሂዱት ስለሚያስቡት ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ 

በዚህ ረገድ ዜግነትን መሠረት ላደረገ ፖለቲካ፣ ላንድ አገርና ላንድ ሕዝብ ሉዐላዊነትና አንድነት፣ ለብሔራዊ ጥቅም፣ ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ለእኩልነት እንሠራለን፣ የሕግ የበላይነት ለሚሰፍንበት መንግሥተ ሕዝብ፣ ባጠቃላይ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ዕሤቶች ቆመናል የሚሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ማኅበራት በተናጥልም ሆነ በኅብረት እነዚህ የአብዛኛው ሕዝባችን ፍላጎት የሆኑትን ቁም ነገሮች በዝርዝር፣ ወጥነት ባለውና የአገላለጽ ጥራት ባለው ሁናቴ ከማስተላለፍ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊሠሩ ይችላሉ የምንላቸውን ሰላማዊ የትግል ዘዴዎችን ወይም እምቢተኝነት ተግባራዊ ለማድረግ አልቻሉም፡፡ አልፎ አልፎ ሰላማዊ ሰልፍ ከመጥራት እና እሱም ባገዛዙ ሲከለከል ‹አልተፈቀደም› ብሎ አኩርፎ ከመቀመጥ ያለፈ እንቅስቃሴ አላየንም፡፡ የተቃውሞ ፖለቲካ  ፓርቲዎች ሕዝብን አደራጅተው ለጋራ ዓላማ ማንቀሳቀስ ካልቻሉ የመኖራቸው ፋይዳ ምንድን ነው? በድርጎ እንደሚያድሩት ቡድኖች ባንኩንም ታንኩንም ለተቈጣጠረው አጃቢ በመሆን የሥልጣንና የሀብት ፍርፋሪ ጥበቃ ከሆነ በሕዝብ ስም መነገድ አያስፈልግም፡፡

በሌላ በኩል ብሔራዊና የጋራ የሚባሉ ፓርቲ-ዘለል አጀንዳዎች ሲነሱም ለአገዛዙ ጭፍን ድጋፍ ለመስጠትና ሕጋዊነትን ለማላበስ ሳይሆን ጥናትና ምርምርን መሠረት ባደረገ ሁናቴ ግራ ቀኙን አበጥሮና አንጠርጥሮ በማየት ብሔራዊ ጥቅምንና የአገር ሉዐላዊነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን ማረጋገጥ ያሻል፡፡ ሕዝብ የማንንም ፈቃድ የማያሻውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብት የሚያፍን አገዛዝ እሱ የሚያተርፍበት ሆኖ ሲያገኘው ወጥታችሁ ዝለሉ ጨፍሩ ብሎ ሲፈቅድ ወጥቶ መዝለልና መጨፈር ከፓርቲዎችም ሆነ ከሕዝብ አይጠበቅም፡፡ 

ሌላው ዜጎች በነገድ ማንነታቸውና በሚከተሉት ሃይማኖት ምክንያት በየዕለቱ በዘግናኝ ሁናቴ በሚጨፈጨፉበት አገር የእውነተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና ምን ድረስ ነው? ድርጊቱን በትክክለኛ ስሙ ጠርቶ ለማውገዝ እንኳን ወጥነት አለ? ከማውገዝስ ባለፈ የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተባብሮ በሀገር-አቀፍ እምቢተኝነት አገዛዙ ላይ የተደረገ ጫና አለ? በቅርቡ የአገዛዙ አለቃ የአማራ ሕዝብ ‹ቄራ› የሆነው መተከል ተገኝቶ የአመራር ለውጥ እንደሚደረግ ተናግሯል፡፡ ችግሩ ሥርዓታዊ በመሆኑ የተባለው ርምጃ ቢወሰድ እንኳን ከጊዜያዊ ማስታገሻነት የሚያልፍ አይደለም፡፡ ‹ሰውየው› በስፍራው በአማራውና በአገው ሕዝብ የሚፈጸመውን የዘር ፍጅት አሁንም ‹ግጭት› ነው የሚለው፡፡ ፈጻሚዎቹንም በስማቸው ለመጥራት አልደፈረም፡፡ በሌላ አነጋገር ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ፍላጎት እንደሌለው ያሳያል፡፡ የሄደውም የሕዝብ ጩኸት ሲበዛ ልገላገል በሚል መንፈስ ይመስላል፡፡ የማይካድራውን የዘር ፍጅት (ጄኖሳይድ) በመተከል፣ በወለጋ እና በኮንሶ ላይ ከሚፈጸም ጋር አነፃፅራችሁ እዩት፡፡ ምን ሥዕል ይሰጣችኋል? በአሸባሪው የታገቱት ልጃገረዶችስ ጉዳይ መንግሥት ያለበት አገር የሚፈጸም ነው? ከአብራካችሁ የተከፈሉ ልጆች ቢሆኑ ልታደርጉ የምትችሉትን ሁሉ ለነዚህ በነገድ ማንነታቸው ለታፈኑ ልጆች አድርጋችኋል? 

አንድ ተጨማሪ ነጥብ ላንሳ፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በተዘረፈ ሀብት የወንጀል ፍሬ ሆኖ የተቋቋመው ኤፈርት (ወጋገን ባንክን ጨምሮ – በጦርነቱ ሰሞን በወጣው የድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ ለምን እንዳልተካተተ አልገባኝም) ሕወሓት ለአመራሩና ቤተሰባቸው መምነሽነሻ፣ ለደጋፊዎቹ የሥራ ምንጭ እና ከሁሉም በላይ በመላው ኢትዮጵያ በጅምላ ሲያከፋፍል ለነበረው ሽብር የገንዘብ ምንጭ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ይህ አሸበሪ ድርጅትና ሕገ ወጥ የገቢ ምንጩ የነበረው ኤፈርት ጦርነቱ ተጠናቅቋል ከተባለ በኋላ ዕጣ ፈንታቸውን በሚመለከት ልጆቹን ልኮ ሕይወቱን የከፈለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአገዛዙ ብዙ ይጠብቅ ነበር፡፡ እውነተኛ ተቃዋሚዎች ካላችሁ ሕዝብን የምታስተባብሩበት የእናንተ አቋም ምንድን ነው? ሕወሓት የትግራይ ብልጽግና ተብሎ በዳግማዊ ኢሕአዴግ ጥላ ሥር በምርጫ የሚሳተፍ ድርጅት ሊሆን ነው? ላለፉት 27 ዓመታት አገር በማፍረስና በአገራዊ ሀብት ዝርፊያ ተሰማርቶ የቆየ ነውረኛ ድርጅት (ሌሎቹ 3ቱና ‹አጋር› የተባሉት ወንጀለኛ ግብረ አበር ድርጅቶች ሳይዘነጉ)፣ አሁን በጦርነቱ ደግሞ የዘር ፍጅትና የጦር ወንጀል የፈጸመ ድርጅት ስሙንም ቀይሮ እንዲሳተፍ ከተፈቀደለት ‹ብልጽግና› የሚባለው ዳግማዊ ኢሕአዴግ ለላቀ ምክንያት የወንጀለኛ ድርጅቶች ስብስብ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የምርጫ ቦርድ የዳግማዊ ኢሕአዴግ ቅጥያ ካልሆነ በቀር የትግራይ ብልጽግናም (ሕወሓት) ሆነ ዳግማዊ ኢሕአዴግ የተባለው የዐቢይ ‹ብልጽግና›ን ከፖለቲካ ማኅበርነት መሠረዝ ሊኖርበት ይገደዳል፡፡ በኦሕዴድ የሚመራው ዳግማዊ ኢሕአዴግ ምን ላይ ተቀምጠሽ ማንን ታሚያለሽ ሆኖበት ይሁን በሌላ ምክንያት ወያኔን እና ኦነግን ሕገ ወጥ አድርጎ በሽብርተኝነት ለመፈረጅ እንዲሁም የወንጀል ፍሬ የሆነውን ኤፈርት ለሕዝብ ጥቅም ወርሶ በአሸባሪው ሕወሓት ግፍና በደል ለተፈጸመባቸው ዜጎች መቋቋሚያ እንዲሆን ለማድረግ ፍላጎት የለውም፡፡ ታዲያ እውነተኛ ተቃዋሚዎች ወያኔን እና ኦነግን ሕገ ወጥ ድርጅቶች አድርጎ በሽብርተኝነትም መፈረጁ ላይ ያላችሁ አቋም ምንድን ነው?

የውጭ ወራሪ ኃይል ድንበር ጥሶ ዜጎቻችንን ሲዘርፍ፣ የደረሰ ሰብላቸውን ሲያቃጥል መንግሥት ባለበት አገር ‹ተዉአቸው÷አትንኳቸው› የሚል ነውር እንዴት ይነገራል? ለመሆኑ ኢትዮጵያ ጠረፍ/ድንበር ጠበቂ ጦር የላትም ወይ? የአንድ አገር መከላከያ ኃይል ዋና ተግባሩስ ይህ አይደለም ወይ? አሁን ከወያኔ ጋር በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የኃይል መሳሳት ቢኖር እንኳን በየቦታው ልዩ ኃይል (ሕገ ወጥ በመሆኑ እስኪበትን ወይም በአገር መከላከያ ኃይል ውስጥ ሥርዓት እንዲይዝ እስኪደረግ) በሚል በአገር ሀብት የሠለጠነውን ኃይል ማሠማራት አይቻልም? ነገር ግን የተፈለገ አይመስልም፡፡ የትኛው መንግሥት ነው ዜጎቹን (የአካባቢውን አርሶ አደር) ለውጭ ወራሪ አጋልጦና ድንበሩን አስደፍሮ ፍጹም ኃላፊነት በጎደለው ሁናቴ የሚቀመጥ? ይህ በወያኔና በወራሹ የዐቢይ አገዛዝ ካልሆነ በታሪካዊቷ ኢትዮጵያ የሚታሰብ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ እውነተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን እያደረጉ ነው? አገዛዙን ተጠያቂ ለማድረግና ዜጎቻችንን ለመታደግ የግድ ሥልጣን መያዝ ይጠበቅባቸዋል?

የአገዛዙን ነውር በትጋት በማጋለጣቸውና ለሥልጣኔ ሥጋት ይሆኑኛል በሚል በወኅኒ ቤት የተወረወሩትን እንደ እነ እስክንድር ያሉ የኅሊና እስረኞችን በሚመለከት እውነተኛ ተቃዋሚዎች ካላችሁ አቋማችሁ ምንድን ነው? መርህ ላይ በመቆምና ነግ በኔን በማሰብ ጭምር ወጥነትና ተከታታይናት ባለው መልኩ እየጮኻችሁ ነው? ለእነዚህና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ አናገኝም፡፡ የጥፋት ኃይሎች እንደ ግብር አባታቸው ዲያቢሎስ 24/7 ሲሠሩ ለአገር ህልውናና ለሕዝብ ደኅንነት ቆመናል የምንል 8/2ስ እንሠራለን? የአገር ህልውናና ዜጎች በሕይወት የመኖር መብት በተነፈጉበት አገር ለምርጫ ዝግጅት እያደርግን ነው? ይካሄዳል የሚባለው ምርጫ ጉልበተኞችንና ጐሠኞችን በሥልጣን እንዲደላደሉ ከሚያደርግ በቀር የተለየ ፋይዳ ይኖረዋል ብሎ የሚያስብ የዋህ ይኖር ይሆን? ጎበዝ! ታዲያ ተአምር እየጠበቅን ነው ያለነው?

እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!! 

ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡

ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡

Filed in: Amharic