>

ላልተመረጡበት የስልጣን ዘመን እቅድ ማዘጋጀት ጸረ ዲሞክራሲያዊነት ነው!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ላልተመረጡበት የስልጣን ዘመን እቅድ ማዘጋጀት ጸረ ዲሞክራሲያዊነት ነው! 

አቻምየለህ ታምሩ

በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የመንግሥት ሥልጣን በሚያዝባቸው አገራት ሁሉ  አገራዊ  እቅድ የሚዘጋጀው በመንግሥትነት የተሰየመው  አካል ወይም  መንግሥት ለመሆን የሚፎካከር ወገን  በተመረጠበት ወይም በሚመረጥበት [አራት ወይም አምስት ዓመታት] የስልጣን  ዘመን ብቻ ለሚከውናቸው ተግባራት ብቻ ነው።  በምርጫ የመንግሥት ስልጣን በሚያዝበት አገር አንድ መንግሥት ላልተመረጠበት የስልጣን ዘመን እቅድ አያዘጋጅም። የዐቢይ አሕመድ የኦሮሙማ የአፓርታይድ አገዛዝ ግን  ላልተመረጠበት የስልጣን  ዘመን የአስር ዓመት የልማት እቅድ ማዘጋጀቱን ከሰሞኑ እየነገረን ይገኛል። ይህ የአገዛዙ እርምጃ የበሬው እንትን ይወድቅልኛ ብላ ስትከተል እንደዋለችው ቀበሮ  ዐቢይ  ወደ ዲሞክራሲ ያሻግረናል ብለው  በተስፋ ለኖሩ  ተደጋፊ ተደማሪዎች  መርዶ ነው።
በየትም አለም ብንሄድ  በምርጫ መንግሥት በሚሰየምበት ሥርዓት አንድ መንግሥት የሚያቅደው በስልጣን ዘመኑ ወይም በሚመረጥበት የስልጣን  ዘመን [term] የሚመራትን አገር  ከየት አንስቼ የት አደርሳታለሁ የሚለውን ብቻ ነው።  ለምሳሌ ባለፉት ጥቂት ወራት  በቀጣይ አራት ዓመታት የአሜሪካ ርዕሰ ብሔር ለመሆን የዲሞክራቱ እጩ ም/ፕሬዝደንት ጆይ ባይደንና የወቅቱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ትንቅንቅ ላይ ነበሩ፡፡ ሁለቱም እጩ ርዕሳነ ብሔሮች ሲቀሰቅሱ  የሰነባበቱት ቢመረጡ ለሚቀጥሉት 4 የዋይት ሐውስ ዓመታት ምን ሊሰሩ እንዳሰቡ ያላቸውን እቅድ ለመራጮቻቸው  በማስረዳት ነበር። ጆይ ባይደንም ሆነ ዶናልድ ትራምፕ ንጉሦች አይደሉምና  ከአራት ዓመታት በኋላ ማለትም እ.ኤ.አ. ከ2024 ዓ.ም. በኋላ  ለአንድ ቀንም ቢሆን የማቀድ መብት [mandate] የላቸውም።
“ወደ ዲሞክራሲ እኔ አሻግራችኋላሁ”፤  “የስልጣን ምንጭ የመራጭ ድምፅ ነው” ፤  “ተፎካካሪ ፓርቲ ቢያሸንፍ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሥልጣን እናስረክባለን”  ወዘተ ሲለን  የከረመው ዐቢይ አሕመድ የሚገዛት  ኢትዮጵያም  እንደ  ጂን ቤዴል ቦካሳ “ምን ታመጣላችሁ ንጉሥ ሆኛለሁ” ብሎ ዘውድ እስካልደፋ ድረስ  ለተመረጠበት እንጅ ገና ላልተመረጠበት የአስር ዓመታት የስልጣን ዘመን የልማት እቅድ የማውጣት ስልጣን [mandate] የለውም።
የዐቢይ አሕመድ  የአስር ዓመት  እቅድ ለሚቀጥሉት አስትርና በላይ አመታትም ገዥው  እኔ ነን ከሚል እርግጠኝነት የመጣ ነው። እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ ለውጥ በሚባለው ነገር ተስፋ ላላቸው በተስፋ የሚጠብቁት  ዲሞክራሲ የማይመጣ መሆኑን፤ በዐቢይ ዘመንም  ብቸኛው ትሩፋት ሞትና ሞት ብቻ  መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡  ከፍ ሲል እንዳልሁት በዲሞከራሲያዊ አስተሳሰብ፣ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሉበት ሀገር፣ የሚታቀደው እቅድ በአንድ የስልጣን ዘመን ሊተገበር የታሰበ እቅድ ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡ ስለዚህ የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ  ገና ላልተመረጠበት 10 ዓመታት እንካችሁ ያለን የ2022ቱ እቅዱ የልማታዊነት  ሳይሆን  የፍጹም አምባገነንነቱ ማረጋገጫ ነው። ዐቢይ አቀድሁ የሚለውን የ2022ቱን እቅድ ብመረጥ የማሳካው ነው እንዳይለን፤ ኢሕአዴግ የሚባለው የብልጽግና አባት  አቀድሁት ሲለን የኖረውን ከፊሉን እንኳን  እንዳላሳካው እሙን ነው፡፡ አይ እስከ 2022  በሚደረጉ ምርጫዎች ብሸነፍና ባቅድ ምን ችግር አለው፤  ሌላ የሚያሸንፍ ፓርቲ ካለ ያ ዳር ያደርሰው የለም ወይ?  እንዳይባል ያልተሳተፈበትን፣ ያልተመረጠበትና ያላረቀቀውን እቅድ አሳካለሁ ብሎ ምረጡኝ  የሚል የምር  የፖለቲካ ፓርቲ  ሊኖር አይችልም።
ባጭሩ መንግሥት ላልተመረጠበት የስልጣን  ዘመን የልማት እቅድ አያዘጋጅም! አንድ በመንግሥትነት የተሰየመ አካል ያልተመረጠበትን የስልጣን ዘመን የሚያቅድ ከሆነ  አዘጋጀሁት የሚለው የአስርም ይሁን የአስራ አምስት ዓመታት እቅድ  የልማታዊነቱ ሳይሆን የጸረ ዲሞክራሲያዊነቱ እና ፍጹም አምባገነንነቱ ማሳያ ነው ። በልማትና ዲሞክራሲ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ሁሉ የሚያሳዩት ላልተመረጠበት፤ ለማይወዳደርበትና ሊተገበር እንደሚችል እርግጠኛ ያልሆኑበትን እቅድ ማቀድ  የልማትና ዲሞክራሲ ምልክት ሳይሆን የአምባገነንነት ዋና ማሳያ መሆኑን ነው።
በተጨማሪም እጅግ ተለዋዋጭ በሆነ አለም ውስጥ እየኖርን አንድ መንግሥት ለመሆን የሚፎካከር አካል እንኳን ያልተመረጠበትን የእድሜ ዘመን ይቅርና  የተመረጠበትን አራትና አምስት ዓመታትም በርግጠኝነት ማቀድ አይቻለውም። ራዕይ ከማስቀመጥ በስተቀር  ላልተመረጠበት የእድሜ ዘመን እያቀደ ወደ ዲሞክራሲ አሻግራችኋለሁ የሚል ቢኖር እመራዋለሁ ብሎ የሚያስበውን ሕዝብ እንደሚንቀውና አያስብም፤  ደንቆሮ ነው  ብሎ እንደሚሰድበው ብቻ ነው የሚያሳየው።
Filed in: Amharic