>

ገና አልባነንም፤ የአገዛዙ አለቃ ኦሮሙማ የሚባለው ፀረ-ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ባለቤት ወይስ በወጥመዱ ተጠላፊ? (ከይኄይስ እውነቱ)

ገና አልባነንም፤ 

የአገዛዙ አለቃ ኦሮሙማ የሚባለው ፀረ-ኢትዮጵያ ፕሮጀክት 

ባለቤት ወይስ በወጥመዱ ተጠላፊ?

ከይኄይስ እውነቱ


እ.አ.አ. ዲሴምበር 27/2020 ‹‹ደውሉ ለማን ነው የሚደውለው! በህይወት የመኖር መብት የሌላቸው ዜጎች ምርጫ ሌላ መታረጃቸው ነው!›› በሚል ርእስ ጽዮን ዘማርያም በተባሉ ሰው የተጻፈ ረዘም ያለ አስተያየት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ገጽ አነበብሁ፡፡

ጽሑፉ ወቅታዊውን አገራችን የምትገኝበትን ሁናቴ፣ ነባሩንና ቀጣዩን ሥጋት እንዲሁም ከገባንበት ዐዘቅት መውጫ መንገድ እና ነጋችን ብሩህ እንዲሆን ማድረግ ይገባናል ያሉትን ሃሳብ  የሠነዘሩበት ነው፡፡ በርእሱም ሆነ በአብዛኛው ይዘቱ የምስማማበት ሆኖ፣ ወደ ጽሑፉ ውስጥ ስዘልቅ አንድ የተሰነቀረ አስተያየት ገጠመኝ፡፡ ይኸውም ከዚህ በታች በቀይ ቀለም አድምቄ ያቀረብሁት ነው፡፡

‹‹በአንድ በኩል ለዶክተር አብይ መንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ በሌላ በኩል ዶክተር አብይ በኦሮሙማ ዘረኛና ተረኛ አመለካከት ወጥመድ ውስጥ እንዳይገባ ድጋፋዊ ሂስ በመስጠት ትግሉን መቀጠል የታሪክ ግዴታ ነው፡፡››

የጽሑፉን ርእስና ይዘት ላስተዋለ ሰው ከፍ ብሎ የተገለጸው አስተያየት በስህተት የገባ ወይም ያለ ቦታው የተሰነቀረ ይመስላል፡፡ የጸሐፊውን ፍላጎት ወይም ዓላማ (intention) የመገመት ወይም የመመርመር ፍላጎት የለኝም፡፡ ተገቢም አልመሰለኝም፡፡ አስተያየቱን እንደወረደ በቅንነት ተቀብዬና የጸሐፊውንም ሃሳብ በማክበር በግሌ የምለይበትን ጥቂት ሃሳቦችን ለመሠንዘር ግን ወደድሁ፡፡

የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ዐቢይ በተለመደው የአገዛዞች መንገድ ወደ ሥልጣን ሲመጣ (የኢትዮጵያ ጠላት ከሆነ እና ኢሕአዴግ ከሚባል የወያኔ የእጁ ፍጥረት ከሆነ የዘረኞችና የወንጀለኞች ድርጅቶቸ ስብስብ እንደመጣ እያወቅኹ) ስለምንወዳትና ስለምንሳሳላት ኢትዮጵያ የተናገራቸው አማላይ ቃላትና የሰጣቸው ተስፋዎች ባያሰክረኝም ይህ ሰው (ሕዝብ የቸረውን ከፍተኛ ድጋፍ ተጠቅሞ) የአገራችን ህልውና አደጋ ላይ የወደቀበትን – የጐሣ ፖለቲካውን፣ የጐሣ ፌዴራሊዝሙን፣ ‹ክልል› የሚባለውንና ዜጋውን በአገሩ ባይተዋር ያደረገውን አጥር እና ለዚህም የጐሣ ሥርዓት ሕጋዊ ሽፋን የሰጠውን አገር አጥፊ የወያኔ ‹ሕገ መንግሥት› በመሻር አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል፤  ለምንመኘውም መንግሥተ ሕዝብ መንገድ ጠራጊ ሊሆን ይችላል በሚል ግምት ጥርጣሬ ያልተለየው ድጋፍ ነበረኝ፡፡ ምኞቴም ሆነ ግምቴም ከመጀመሪያዎቹ ሦስት/አራት ወራት በላይ ሊዘልቅ አልቻለም፡፡ ቃልና ተግባር በጭራሽ ሳይሰናኙ ቀሩ፡፡ እኔ ተሳስቼ እሱ ትክክል እንዲሆን አጥብቄ ተመኝቼ ነበር፡፡ ብዙዎችም በሱ ተገብተው ያልፈጠሩት ሰበብ አልነበረም፡፡ አሁንም የቀጠሉ አሉ፡፡ እነሱ የፈጠሩለትን ሰበብ የማይጋራውን ሁሉ ያወግዙ ነበር፡፡ አሁንም ከገቡበት ጥልቅ እንቅልፍ/ሰመመን/ቅዠት ያልባነኑ አሉ፡፡ ግን መሬት ላይ ያለው ጽድቅ የሚናገረው በተቃራኒው ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ተዳፋቱን ተያይዞት አሁን የምንገኝበት ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ላይ ደርሰናል፡፡ የዐቢይ አፓርታይዳዊ አገዛዝ የወያኔን የጥፋት ሬከርድ በቊጥር በማይገለጽበት ሁናቴ ሰብሮታል፡፡ ጆሮን ጭው የሚያደርገው የዕለት ተዕለት አሰቃቂ ድርጊት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሠቱትን ፋሺዝምና ናዚዝምን እያስናቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት መክሸፉን እና የለም የሚያሰኙ መገለጫዎቹ ደጋግመው የተነሱ ቢሆንም ለአብነት ያህል የምንጠቅሳቸው ድርጊቶች ወይም ዳተኝነቶች በዐቢይ ፈቃድና የሚያስደነግጥ ዝምታ መፈጸማቸው እሱ ራሱ ኦሮሙማ የሚባለው ፀረ-ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ባለቤት እንጂ በፕሮጀክቱ ተጠላፊ አለመሆኑን በእጅጉ ያመለክታሉ፡፡

1/ ኢትዮጵያ በታሪኳ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ነገድንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ዘግናኝና አረመኔያዊ የጅምላ እልቂት ወይም የዘር ፍጅት (ጄኖሳይድ) የሚፈጸምባት ምድር ሆናለች (የቡራዩው ጭፍጨፋና እሱን ተከትሎ በአ.አ. ወጣቶች ላይ የተፈጸመው ግድያና የበርሃ እሥር እስከ ኦነግ የልጃገረዶቹ ዕገታ፤ በአሸባሪው ጀዋር ተከበብኩ ምክንያት በሽመልስ አሸባሪ ቄሮዎች ከተፈጸመ ጭፍጨፋ እነ እስክንድርን በየጊዜው በመተናኮል የተፈጸመ ዛቻ/ማስፈራሪያ፤ የሃጫሉን ግድያ ሰበበ በማድረግ በሻሸመኔ፣ በዝዋይ በአርሲ ከተደረጉ ጭፍጨፋዎችና የንብረት ውድመቶች እስከ ጉራፈርዳው እልቂት፤ በሲዳሞ ኤጄቶዎች ከተፈጸሙ ግድያዎችና አብያተክርስቲያናት ቃጠሎ እስከ ወለጋው ጉሊሶ ጭፍጨፋ፤ የአረመኔነቱ ጣራ ማሳያ ከሆነው የመተከሉ የዘር ፍጅት እስከ ኮንሶው የንጹሐን ጭፍጨፋ ወዘተ.)፡፡ ባጠቃላይ ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዝናት በዚህ ሦስት ዓመታት ገደማ ሰላም ውላ ሰላም ያደረችበት ቅጽበት የለም፡፡ የወንበዶች መፈንጫ ሆናለች፡፡ በነዚህ ሁሉ እልቂቶች ማን ኃላፊነቱን ይውሰድ? የአገር መሪ ነኝ ከሚል ግለሰብ በዝቅተኛ ደረጃ የሚጠበቀው የተፈጸመውን ድርጊት በስሙ ጠርቶ ከማውገዝ ጀምሮ በግፍ ለተገደሉ ዜጎች ክብር ካለው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ ብሔራዊ ሐዘን ማወጅ ነበር፤ የተጎዱትን በየቦታው በአካል ተገኝቶ ከማጽናናትና ጀምሮ አቅም በፈቀደው ደረጃ መልሶ ማቋቋም፡፡ ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ በድርጊቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉትን ለፍርድ ማቅረብና ተመሳሳይ ድርጊት ዳግም እንዳይፈጸም አስፈላጊውን ሕግና ሥርዓትን የማስፈን ተከታታይ ርምጃ መውሰድ፡፡ ይህንን ለማድረግ የማይፈልግ/የማይችልና የሕዝብን ሐዘን የማይጋራ መሪ ለኢትዮጵያ ምኗ ነው? እሱን ማንቆሻበሉና መደገፉ በተፈጸሙት ድርጊቶች ግብረ አበር ከመሆን ምን የተለየ ትርጕም አለው? 

2/ ተረኞች ጐሠኞች (የዐቢይ ድርጅት በየደረጃው ያስቀመጣቸው አመራሮችና ወዶ ፈቅዶ ባማካሪነት ጭምር ባስጠጋቸው ኦነጎች ምክንያት) በመላው አገራችን በሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

3/ የአገር መከላከያ፣ የፖሊስ እና የአገርና የሕዝብ ደኅንነት ተቋምን በጐሣ በማደራጀት የአገዛዙ ፓርቲ ጠባቂ ኃይል ከማድረግ ባለፈ በሁሉም የመንግሥት ተቋማት ውስጥ (የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖችን ጨምሮ) ከአመራሮች ሹመት እስከ ተራው ሠራተኛ እሱ እውክለዋለሁ በሚለው ጐሣ ሰዎች እንዲሞላ በማድረግ አብዛኛውን ዜጋ ባገሩ ባይተዋር ማድረጉ፤ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

4/ በሱ ዕውቅናና ፈቃድ በየክፍለተ ሃገራቱ በተለይም እሱ እመራዋለሁ በሚለውና ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በፈጠረው የኢትዮጵያ ግዛት ከአገር መከላከያ በላይ ብዛት ያለው ‹ልዩ ኃይል› የሚባል ለአሸባሪነት የተጋለጠ ሕገ ወጥ ሠራዊት በማደራጀት የአገር ህልውና ሥጋት ላይ ከመውደቁ በተጨማሪ ከፍተኛ የሕዝብ ሀብት እየባከነ ይገኛል፡፡ ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

5/ የርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ምእመናን ለዘመናት በነፃነት ሲያከብሩ የቆዩትን ሃይማኖታዊ በዓላት በነፃነት እንዳያከብሩ ምእመናን እና ካህናትን ከመግደልና አብያተ ክርስቲያናትን በማቃጠል ሳይወሰን በሽመልስ የሚመሩ አሸባሪ ቄሮዎችን እንዲሁም በዘር የተደራጀውን የፖሊስ ኃይልና ሕገወጡን ‹ልዩ ኃይል› በማሠማራት የተቀደሱ በዓላትን ክብር መድፈርና ዜጎች በደስታቸውም ሆነ በሐዘናቸው ወቅት በልዩ ልዩ መልኩ የሚይዙትንና የሚያጌጡበትን ዓርማ የለሹን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ መቀማት፣ ማቃጠልና በዚህም ምክንያት በየጊዜው እንግልት በመፈጸም የተለመደው አስነዋሪ ተግባር ለማስቆም አለመፈለግና በተቃራኒው ኦነጋውያኑ የሱ ዘመዶች የሚይዙት የአንድ ቡድን ዓርማ (እንደ ሰንደቅ ዓላማ ተቈጥሮ) እና ከጐሣው ጥቂቶችን ብቻ የሚወክል ‹ፖለቲካዊ በዓል› በነፃነት እንዲከበር በማድረግ ያሳየው አድልዎ፡፡ ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

6/ በአዲስ አበባ በተለይ፣ በሌሎቹም የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገራት ባጠቃላይ ዐቢይ በሚወክለው የኦሮሞ ጎሠኛ ፖለቲከኞች አማካይነት የኦነግ አሸባሪ ኃይልና ‹ልዩ ኃይል› የተባለውን ሠራዊት በመጠቀም ሕዝብን በማፈናቀል ከፍተኛ የሆነ የመሬት፣ ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ወረራ እና የሕዝብን ስብጥር የመቀየር ፖለቲካዊ ነውር እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ ይህ ሕዝብን እየገደሉና እያፈናቀሉ በኃይል የታገዘ የውስጥ ግዛት መስፋፋት ኦሮሙማዎች ከኢትዮጵያ የተለየ አገር ለመፍጠር ካላቸው ፍላጎት ይሁን ወይም የዐቢይ ቊልፍ ሹመኛ ሽመልስ እንደነገረን ታሪካዊቷን ኢትዮጵያ ከእነ ዕሤቶቿ በማጥፋት ኦሮሞን የምትመስል ኢትዮጵያ የመገንባት ኅልም አካል እንደሆነ የእንቅስቃሴው ባለቤቶች የሚያውቁት ሲሆን፣  ‹ብልጽግና› የተባለውን ዳግማዊ ኢሕአዴግ የሚመራው ዐቢይ በተግባርና በዝምታ ጭምር ዕውቅና የሰጠው አገርን የማጥፋት የክህደት ተግባር ነው፡፡ ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

7/ በሚከተለው የለየለት አፓርታይዳዊ (የጐሣ መድልዎ) ሥርዓትና የተሳሳተ የውጭ ፖሊሲ ምክንያት የውስጥ ሰላምና ጸጥታ ማስከበር አቅቶት አገርን ደካማ በማድረግ ለውጭ ወራሪ ኃይል ማጋለጡና ማስደፈሩ፤ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

8/ ቀዳሚ ዓላማው የአገዛዙን ሥልጣን (አገር አጥፊውን የወያኔ ‹ሕገ መንግሥት›) ለማስጠበቅ ያለመ፣ ቊጥራቸው እስካሁን በውል የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን ያለቁበትና እጅግ ከፍተኛ የሀገር መከላከያ መሣሪያ የወደመበት ጦርነት ተካሂዶ ወያኔ ተደምስሷል ቢባልም (አመራሮቹ በቊጥጥር ሥር ስለመዋላቸው ወይም ስለመደምሰሳቸው በይፋ ባልተነገረበት) ጦርነቱ ገና እልባት አላገኘም፡፡ ይህን የአገር ጠንቅ አሸባሪ ቡድን ከዓላማ አጋሩ ኦነግ ጋር ሕገ ወጥ በማድረግ በአሸባሪነት ለመፈረጅ አለመፈለግ ባንድ በኩል ከሕወሓት ጋር የአስተሳሰብና የዓላማ ልዩነት አለመኖርን ሲያመለክት፣ በሌላ ወገን ኦነጋውያን የዐቢይ አማካሪ በመሆን÷ በመንግሥታዊ ሹመት (መከላከያውን ጨምሮ) እና ሽመልስ በሚመራው ‹ልዩ ኃይል› ውስጥ የተደባለቁ በመሆኑ ከኦሕዴድ ጋር (ምናልባት የሥልጣን ሽኩቻ ካልሆነ በቀር) አንድ አካል አንድ አምሳል መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ከዚህም አልፎ የማይካድራውን ዘር ፍጅትና በሰሜን እዝ ሠራዊት ላይ የጦር ወንጀል የፈጸመውን ሕወሓት የትግራይ ብልጽግና በሚል ሽፋን ለማስቀጠል እየሠራ ይገኛል፡፡ ታዲያ ከዚህ አገዛዝ ምን እንጠብቅ? ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

9/ እንደ ኤፈርት፣ ዲንሾ፣ ጉና የመሳሰሉ በሕገወጥ መንገድ የፖለቲካ ድርጅት ንብረት የተደረጉና ከሕዝብ የተዘረፉ የወንጀል ፍሬዎች ለባለቤቱ ሕዝብ እንዲመለሱ፣ በተለይም በኢሕአዴግ ድርጅቶች ግፍና በደል የተፈጸመባቸው ዜጎች የሚካሡበት እንዲሆን ለመወሰን አለመፈለግ ዳግማዊው ኢሕአዴግ ከቀዳማዊው ኢሕአዴግ አለመለየቱን ከሚያስረዳም በላይ ይህ ወያኔ የፈጠረው ኢሕአዴግ (አሁን ‹ብልጽግና›) የተባለው ስብስብ መቼም ቢሆን በፈጸመው አገራዊ በደል የማይጸጸትና ሕዝብን ለመካሥ ዝግጁ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ አገዛዝ ምን እንጠብቅ? ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

10/ በግብር ከፋዩ ሕዝብ የሚተዳደሩት የመንግሥት አስተዳደር መ/ቤቶች (ቢሮክራሲ)  ከማዕከል እስከ ክፍለ ሀገር ተረኛ ነን ለሚሉ ኃይሎችና ቡድኖች መሣሪያ መሆናቸው፤ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

11/ ዐቢይ በደምና ባጥንነት የተገኘ ነው የሚለው የወያኔ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› ሳይሻሻል ሲዳሞ እና ደቡብ ምዕራብ የሚባሉ ሕጋዊ ዕውቅና የሌላቸው ግዛቶች በመፍጠር የደቡቡን የኢትዮጵያ ክፍል በተረኞችና ከእነ አባይ ፀሐዬ እኩል ወንጀለኛ በሆነው አባ ዱላ አማካይነት የሚፈጸመው አገር የማፍረስ የኦሮሙማ ፕሮጀክት አካል ምን ትርጕም እንስጠው፡፡ ሽመልስ አገርን የሚያምስበት የቋንቋውስ ጉዳይ ምን ሕጋዊ መሠረት አለው? ባለፉት 30 ዓመታት በሰፈነው የጐሣ አገዛዝ ሥርዓት ሕግ አውጪው የሕዝብ ተወካዮች ያልሆነው ም/ቤት ሳይሆን ሕግ አስፈጻሚው አካል መሆኑ በሚገባ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ የሚኒስትሮች ም/ቤት የኛ የሚሉትን ‹ሕገ መንግሥት› ተፃርሮ (ካላሻሻለው በቀር) 5 ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ብሎ በተራ ሕግም በተግባርም መፍቀድ አይችልም፡፡ ምን ታመጣላችሁ የሚል ትእቢትና ሕዝብን ንቀት ካልሆነ በቀር፡፡ ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

12/ በአመዛኙ ክፍላተ ሀገራት በአስተዳዳሪነት የተሰየሙት የጎሣ አለቆች በማዕከላዊው መንግሥት የተሰየሙ ሞግዚት ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ሕገ ወጥ የመንደር ወሮበሎችን በማደራጀትና መዋቅራዊ ድጋፍ በመስጠት የሕዝብን የዕለት ተዕለት ኑሮ ሲያውኩ ያለአንዳች ተጠያቂነት መታለፋቸውና አሁንም ድርጊቱ መቀጠሉ፤ በተለይም ወያኔ ‹አማራ ክልል› ባለው ግዛት ዐቢይ ከአንዴም ሁለቴ የፈለገውን ታማኝ ሎሌ እያሰቀመጠ የሚቆጣጠረው መሆኑ እና ፍትሕ የሚጠይቁና የሚገዳደሩ ርእሰ መስተዳድሮችና ባለሥልጣናት ሲታዩ የተፈጸመውን የሰኔ ሁነት ሁላችን የምናስታውሰው ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ አገዛዝ ምን እንጠብቅ? ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

13/ በአገዛዙ ድጋፍና ዕውቅና በተረኝነት መንፈስ በሚንቀሳቀሱ ጐሠኛ ባለሥልጣናት፣ ግለሰብ ነጋዴዎች፣ አድርባዮችና ዘረኛ የፖለቲካ ቡድኖች ብሔራዊ ምልክት የሆኑ ተቋማትን (ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ) በተጠና መልኩ የማፍረስ ተግባራት ታይተዋል፡፡ ታዲያ ከዚህ አገዛዝ ምን እንጠብቅ? ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

14/ ወያኔ ትግሬ ባህል ያደረገውን ገዢ ‹ፓርቲ› እና ‹መንግሥት› አንድ አካል አንድ አምሳል ሆኖ በመሥራት የሕዝብን ሀብት አገራዊ ላልሆነ የፖለቲካ ቡድን ዓላማና ፍላጎት በማዋል የሚታይ ሥር የሰደደ ንቅዘትና በሥልጣን መባለግ እና ተጠያቂነት ያለመኖር ባህል (culture of impunity) ባዲሶቹ ተረኞች ተጠናክሮ መቀጠሉ፡፡ ታዲያ ከዚህ አገዛዝ ምን እንጠብቅ? ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

15/ የፍትሕ ሥርዓቱ ባጠቃላይ ዳኝነቱ በተለይ እንደ ዘመነ ወያኔ ከቤተመንግሥት የሚታዘዝ የአገዛዙ ደንገጡር መሆኑ እና ዜጎች በሕግ የበላይነት እምነት እንዲያጡ መደረጉ ሌላው ዝቅጠት ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ አገዛዝ ምን እንጠብቅ? ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

16/ የባንኮቹን ዘረፋ ምን ስም እንስጠው? የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግፍ የተሞላበት ዕደላ ምን እንበለው? በሕዝብ/መንግሥት ሀብት ለሥልጣን የሚደረግ የምርጫ ቅስቀሳ ንቅዘት ብቻውን ይገልጸዋል ወይ? ሲሰርቁ አለመገኘትና ሲያሰርቁ መገኘት ልዩነቱ ምንድን ነው? ስልቻ ቀልቀሎ እንደማለት አይደለም? ታዲያ ከዚህ አገዛዝ ምን እንጠብቅ? ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ?

17/ ከወያኔ በተማረው መሠረት ተቃዋሚ ተብዬዎችን በሕዝብ ሀብት ድርጎ (ሹመት፣ ቤት፣ መኪና ወዘተ.) እየሰጠ በማምከን፣ እውነተኛዎቹን ደግሞ ያለምክንያት እያሰረ በማሽመድመድና ‹ምርጫ ቦርድን› ተቈጣጥሮ በሕገ ወጥ ‹ልዩ ኃይል› በመታገዘ የውሸት ምርጫ ለማድረግ መሯሯጥ የት ያደርሰናል? ታዲያ ከዚህ አገዛዝ ምን እንጠብቅ? ለዚህ ማን ይጠየቅ ወይም ኃላፊነቱን ይውስድ? ጸሐፊው እንዳሉት እላይ በዘረዘርናቸውና በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚታየውን ጽድቅ ለተረዳ አእምሮና ላስተዋ ኅሊና በአሁኑ ጊዜ ምርጫ ማድረግ ዜጎችን ለከፍተኛ እልቂት የሚጋብዝ÷ ኃላፊነት የጎደለውና በታሪክ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው፡፡

እንቀጥል ካልን ዝርዝሩ ማለቂያ የለውም፡፡ ውዳሴ ከንቱን እንጂ ገንቢ ትችትን መስማት ከማይፈልግ፣ በበሳሎች ምክርና ጥበብ ሳይሆን በሠራዊት ብዛት ከሚመካ፣ እውነትን ከመጋፈጥ ይልቅ ልማዳዊ ቅጥፈትን ገንዘቡ ካደረገ ፣ ሕዝብ የሰጠውን ዕድሎች ሁሉ ካመከነ ጐሠኛ መምዕላይ (dictator) ምን እንጠብቅ?

ባጭሩ የአገርን ጥቅምና የሕዝብን ደኅንነት የማያስቀድም ‹መሪ› (በተግባርም፣ በዝምታም፣ በዳተኝነትም፣ ቈራጥነት በማጣትም፣ ከሁሉም በላይ ከወያኔ በወረሰው ጐሠኛነት) በየትኛውም መመዘኛ የምንደግፍበት ምክንያት የለም፡፡ አሁን ካልባነንን ጊዜው እየረፈደ ይመስላል፡፡ 

በፈሪና ጨካኝ አረመኔዎች እጅ ወድቀናል፡፡

ኢትዮጵያንና ሕዝቧን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በምሕረቱ ይጎብኝ፡፡ 

እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!! 

ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡

ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡

Filed in: Amharic