>

የመተከሉ ጭፍጨፋ እና ያደረሰው የመንፈስ ስብራት.. !!! (በጋዜጠኛ መስከረም ጌታቸው)

የመተከሉ ጭፍጨፋ እና ያደረሰው የመንፈስ ስብራት.. !!!

(በጋዜጠኛ መስከረም ጌታቸው)

ሰሞኑን ለአገልግሎት ወደ እንጅባራና ባህር ዳር ነበርኩ ።
ሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ እንጅባራም ሆነ ባ/ዳር ማስክ አያደርጉም አስቀድሜ ብሰማም ሳያቸው ግን በጣም ገረመኝ ። ባሕር ዳር ወደ ቤት የሚወስደኝን የባጃጅ ሹፌር ለምን ማስክ እንደማያረጉ ጠየኩት ። “ለምን እናረጋለን መልሶ ጠየቀኝ” ከመታበይ ቆጥሬው ነው መሰል አናደደኝ። መልሽልኝ እንጅ አለኝ።
ግራ በመጋባት ኮሮና እዚህ አልደረሰም እንዴ አልኩት። ይችን እንድለው እንደፈለገ የገባኝ ይህን ሲመልስልኝ ነው” እኛን የገደለን ኮሮና አይደለም ሰው ነው ᎐᎐᎐ሰው ነው ሰው᎐᎐᎐” ዝም አልኩት።  የባጃጇ መጋረጃ በምሽቱ የባሕር ዳር ንፋስ አበሳውን ያያል ።ቀዝቃዛው አየር ደስ ቢለኝም ይህ የእሱ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ስሜት እንደሆነ በመረዳቴ ውስጤ የናፈቀውን አየር እየሳበ ራሱን ማደስ አቃተው።መንገድ ስለዋልኩ ስለቀኑ ውሎ መረጃ አልነበረኝምና ዛሬ ምን አዲስ ነገር አለ አልኩት። “ምን አለ ብለሽ ነው ያው እየሞትን ነው አሉ ለመርዶ ማን ብሎን” ሲያወራ እኛ እያለ ነው ። ሞቱ ሳይሆን ሞትን ተገደሉ ሳይሆን ተገደልን ᎐᎐
እንጅባራ የነበረንን ቆይታ አጠናቀን ወደ ባህር ዳር እየተመለስኩ ነው ። አነሳሴ ከመሼ ነበርና መኪና አጥቼ በሞላ “ኮስትር” ውስጥ ገባሁ። አዲስ ቅዳምን እንዳለፍን ተጠግቼ ከነበርኩበት ወደ መጨረሻ ወንበር ተዛወርኩ።ከጎኔ ገራገር ወጣት አለ-ለምጠይቀው ሁሉ በቅንነት የሚመልስ።መንገድ ላይ ወሬ ባልወድም እሱ ጋ ግን አወራሁ።በዚህ ሁሉ መሀል ግን ከፊቴ የተቀመጠችው  16 ወይ17 አመት እድሜ የምገምታት ወጣት ትኩረቴን ሳበችው።
ሰው ድምጹን ከፍ አድርጎ ሲናገርም መኪናው ፍጥነት ሲጨምር ሲቀንስም ብቻ በሁሉ ነገር ንቁ ናት ቶሎ ቶሎ ዙሩያዋን ትቃኛለች ።በኋላ እንደገባኝ ደግሞ ስጋት እና መረበሽ ስሜት ውስጥ ናት።ወሬውን እንዴት እንደጀመሩት ባላውቅም አጠገቤ ካለው ወጣት ጋር ስታወራ “በፊቴ ነው የገደሏቸው” ስትል ከመተከል አካባቢ እንደመጣች ገባኝ። እኔም ወሬውን ተቀላቅዬ ጥያቄ አስከተልኩ መለሰችልኝ። “ሆቴል እና ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ነበረን ከዚያ ውጡ ብለው አስወጡን ቢያንስ እቃ እንያዝ ስንል አይሆንም ብለው የተወሰነ እቃ ጭነው ቤተሰቦቼ ወደ ቡለን ሄዱ እኔ ወደ አዴት አያቶቼ ጋ እየሄድኩ ነው። እንቅልፍ ከተኛን ዘመን የለንም ኑሮ አይበለው ደሞ  ምሄድበትን አላወቀውም᎐᎐መኪና አገኝ ይሆን ᎐᎐አሁንስ ምርር አለኝ”አለችና ቀጭን አንገቷን ደረቷ ላይ ደፋችው᎐᎐᎐እኔን!!
የጀመረችውን ወሬ አትጨርሰውም᎐᎐᎐በየመሀሉ ብቻዋን ታወራለች ግን ለማንም አይሰማም። ፈጣሪ ከሰማት ይበቃል።ውስጧ ከማየው በላይ እንደተሰበረ የበለጠ የገባኝ ግን ዳንግላ ስንደርስ ነው። ከመኪናው ውጭ አንዲት ሴት ትጮሃለች ።መንገድ ያለው ተረበሸ።መኪናችን መሄድ እስኪቸገር ሰው ይሯሯጥ ነበር። እኛም  ሌላ መኪና ሰው ገጭቶ ይሆን እያልን ግምታችንን ሰጠን።
የዛች ወጣት ግምት ግን ሌላ ነበር “ወይኔ ጉዴ እዚህም አሉ እንዴ? ደሞ እዚህ ሁሉም ቀዮች ናቸው በቃ ይጨርሷቸዋል እረ አሁንስ የት ሂደን እንኑር ᎐᎐᎐”ቀጥታ ያገናኘችው ተወልዳ ባደገችበት አካባቢ ካየችው መከራና በቃላት ከማይገለጸው ጭፍጨፋ ጋር ነበር። ይቺ ወጣት ካየችው እልቂት ብትተርፍም እንዲህ ውስጧን ከሰበረው ትእይንት ግን አእምሮዋ ነጻ ሊሆን አልቻለም-ሕጻናቱማ እንዴት ላለ ስነ ልቦናዊ ቀውስ ተዳርገው ይሆን? አረጋዊያኑ ምን ይህል ዘመናቸውን ረግመውት ይሆን?
እግዚእብሔር ሆይ መልካም ቀናትን መልስልን!!
(በጋዜጠኛ መስከረም ጌታቸው)
Filed in: Amharic