>

ሱዳን የያዛችው መሬት ብቻ አይደለም! (ጌታቸው ሽፈራው)

ሱዳን የያዛችው መሬት ብቻ አይደለም!

ጌታቸው ሽፈራው

 

የትህነግና የኦነግ ደጋፊዎችና ትርፍራፊዎች ሱዳን “የአማራን መሬት ያዘች” ብለው አብረው ክብ እየዞሩ እየጨፈሩ ነው። “ኢትዮጵያን ወጋች ብለው” እየተደሰቱ ነው። ሱዳን የያዛቸው የአማራን መሬት ብቻ አይደለም። ለኢትዮጵያን መሬት ብቻ አይደለም። ሉአላዊ ግዛት ነው!
መሬት ተደርጎ ከተወሰደማ አማራው ሱዳን ከያዘችው የበለጠ እጥፍ ድርብርብ ርስቱን  ከትህነግ አስመልሷል። በመሬት ከሆነማ ትህነግ ከ30 አመት በፊት በግድ የከለላቸው ወልቃይት ጠገዴ ጠለምትና ራያ ሱዳን ከያዘችው አንፃር ሲታይ ምንም ነው።  ግን ሱዳን የያዘችው ከመሬትም ከፍ ያለ ነው። ሉአላዊነት ነው።
በእርግጥ ሱዳን የበርካታ ገበሬ ንብረት ወስዳለች፣ አቃጥላለች፣ አበላሽታለች። ይህ እጅግ አሳዛኝ  ነው። ግን አማራም ኢትዮጵያም ካገኙት ድልና ካለባቸው የቤት ስራ አንፃር የሱዳንን ወረራም ስሜታዊ አልሆኑበትም። የገበሬዎቻችን መፈናቀልና ንብረት ውድመት ስለማያሳስበን አይደለም። እጅግ አሳሳቢ ነው። እጅግ። ግን  ደግሞ ኢትዮጵያና አማራ የጎረሱት ድል አለ። አሁን የትህነግና የኦነግ ትርፍራፊ ደስታውን ስለገለፀ ኢትዮጵያም አማራውም የጎረሱትን ተፍተው አሳዛኝ ተሸናፊ መሆን የለባቸውም። ኢትዮጵያም አማራም ትህነግን ጎርሰውታል። ሱዳን ጋር እንግጠም ብለው ትህነግን እንዲተፉላቸው ነው የኦነግና የትህነግ ደጋፊዎች ይህ ሁሉ ጩኸታቸው። አይሆንም። መጀመርያ በደንብ ያኝኩታል። ድቅቅቅቅ ማለት አለበት! ይዋጣል!
በቤንሻንጉልና በወለጋም ሌላ ችግር ገጥሞናል። በአንዴ ሶስት አራት ቦታ ባክነን የያዝነውን ሁሉ አንጥልም። ሱዳን እያወደመ ያለው ይታወቃል። ግን ስሜታዊ አንሆንም።  ቀሚስ አስለብሰን ያሸነፍናቸው ስሜታዊ ይሁኑ! ይለፍልፉ! እኛ ጎርሰናል መለፍለፍ አንችልም! የፊት የፊቱን እያጣጣምን እንቀጥላለን!
አሁን ኢትዮጵያም አማራም ትህነግን አንኮታኩተውታል። አማራው በመተከልና በወለጋ እየተወጋ ነው። ሌላ ግንባር ሆኗል። ይህኛው የትህነግ ውላጅ ጋር ያለው ግንባር በድል እስኪጠናቀቅ የሱዳኑን እንችለዋለን።  ቅደም ተከተል አለው። ጊዜ እንጠብቃለን!
ሱዳን የያዘችው መሬት ተብሎ የሚቃለል አይደለም። ሉአላዊ ግዛት ነው። በእርግጥ በመሬትም ብንወስደው ቀላል አይደለም።  በመሬት ደረጃ አናቀልለውም እንጅ ወደ መሬት እናውርደው ካልን ካስመለስናቸው ርስቶች ጋር ስናወዳድረው “ችግር የለውም ያለው ይበቃናል።” ብለን መተው እንችል ነበር።  አንከስርም። በንብረት ደረጃ አናወርደውም እንጅ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ንብረት ወድሟል።  በንብረት ደረጃ ካወረድነው ግን ትህነግ በአመት  ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያተርፍበትን ወልቃይት ጠገዴን ለባለርስቱ፣ ለጥንተ ነዋሪው ማስመለሳችን በቂ ነው ብለን እናቃልለው ነበር። ጠለምትና ራያን ጨምረን ምንም ነው ይቅርብን ብለን የባሰ እናቃልለው ነበር። ብናቃልለው ደምረን ቀንሰን አንከስርም ነበር። ግን አናቃልለውም። የሉአላዊነት ጉዳይ ነው። መሬትም፣ ንብረትም ብቻ አይደለም።
 አማራንም፣ የፌደራል መንግስቱንም ኤርትራንም አንዴ እገጥማለሁ እያለ ሲንጠራራ እንደፈነዳው ትህነግ አሳዛኝ ተሸናፊ አንሆንም። ከጠላቶች፣ ከከሃዲዎች ሳይቀር እንማራለን። በሉአላዊ ግዛታችን አንደራደርም። ሉአላዊነትም ቢሆን ግን ትርፍና ኪሳራ እናሰላለን። በሉአላዊነት አንደራደርም ማለት በመጣው ሁሉ ሳንዘጋጅ፣ ትንፋሽ ሳንወስድ፣ ተንደርድረን እንገባለን ማለት አይደለም።
አማራውም ኢትዮጵያም በትህነግ ስር የነበሩትን እያረጋጉ መሬት ላይ እየሰሩ ነው። ሱዳን ይህን ሲያረጋጉ ነው ከኋላ የወጋው። የጨበጡትን ሁሉ የትም ጥለው አይመለሱለትም። ወረራው አውዳሚ ቢሆንም እንኳ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ የግዳችን ሰክነንም እንወጣዋለን። ሌሎች ድሎችን ሜዳ ላይ በትኖ ተሸናፊ ላለመሆን እየተጎዳን ጠብቀናል።  ሲቻል በዲፕሎማሲ እንሞክራለን። ካልተቻለ የያዝናቸውን ቦታ ቦታ አስይዘን፣ የጎረስነውን ውጠን እንመለስበታለን!  ጊዜ እንኳን ቢወስድ የያዝነውን ላለመጣል እንጠብቃለን። እንደ ትህነግ በዚህም በዛም ጠላቴ ብለን፣ ሁሉንም ካልገጠምን ብለን፣ በስሜት ደንፍተን የያዝነውን ጥለን በድል ርሃብ አናፏሽግም። በቅደም ተከተል የጎረስነውን እያኘክን እንቀጥላለን። እንደ አማራም እንደ ኢትዮጵያም የሚያዋጣን ይሄ ነው። ድል የራበው፣ ያልጎረሰው ይጩህ፣ ባዶ ነው። እኛ የጎረስነውን  ጎርሰናል። የደከምንበትን የያዝነውን አንተፋም! ቀስ እያልን ሌላ እንጨምራለን እንጅ!
ትህነግ ለሱዳን እንድትወስደው ቃል የገባው ቀርቶ ትህነግ የወሰደውን ጊዜ ጠብቀን፣ አቅም አሰባስበን፣ ሰክነን ወደነበረበት አስመልሰናል። የሚያለቅሱት እንባም ሲጨርሱ እኛ የድል ስንቅ እናጠራቅማለን። ኢትዮጵያ ተወረረች ብለው በባዶ ተስፋ የሚፈነጥዙት ከንቱ ሲደክሙ እኛ የያዝነውን ይዘን አቅም እናሰባስባለን!
Filed in: Amharic