ያባከንናቸው ትልቅ የሀገር በረከት…!!!
መስከረም አበራ
ኢትዮጵያ ወንዝ ታቅፋ የምትጠማ፣ለም መሬት ይዛ የምትራብ ሆና አታበቃም-አዋቂ ሞልቷት እውቀት ያጠራትም ጭምር ነች፨ የእኛ ሃገር እውቀት ይመራት ዘንድ እድሏ አልቀናም፨ አዋቂዎች ዳር ተቀምጠው ለአላዋቂ ከበሮ ይደለቃል፨ ካቢኔው፣ ኮሚቴው ፣ኮሚሽኑ ሁሉ በአላዋቂ ይታጀላል፨ መሾሙ እውቀት የሚሆን የሚመስለው ብዙ ነው፨
አውቆ መሾም አልሆን ካለ ከተሾሙ በሃላ እውቀትን መሻትም ያባት ነው፨ ይህ እንዲሆን ልምድ ከእውቀት ያጣመሩ ሰዎችን ማቅረብ ፣ከእነሱ መስማት ደግ ነው፨
እውቀት ከልምድ ካሰናሰሉ፣ ሊሰሙ ከሚገባቸው ሰዎች አንዱ የሃገር ሰው ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊወርጊስ አንዱ ናቸው፨ በውትድርናው ዘውግ ሻለቃ ሲሆኑ በአሜሪካ ሃገር ከሚገኘው ታዋቂው የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ በህግ የማስተርስ ዲግሪ አላቸው፨በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ሶስት መፅሃፍት ፅፈዋል፨ “Red Tears” የሚለው መፅሃፍ እኔ ካነበብኳቸው ምርጥ መፅሃፍቶቼ አንዱ ነው፨ በሃገራዊ እና አህጉራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በእንግሊዝኛ የሚ ፅፏቸው ፖለቲካዊ፣ ጅኦ-ፖለቲካዊ እና የፀጥታ ጉዳዮችን ያጣመሩ ፅሁፎች ብዙ ተምሬያለሁ፨
ሻለቃ ዳዊት የውትድርና እና ጸጥታ ሳይንስ እውቀታቸው ለሃገር ቀርቶ ለአህጉር የሚተርፍ ነው፨ ስለ ሰላም ፀጥታቸው መላ ፍለጋ ሻለቃ ዳዊትን ያላማከረ የአፍሪካ ሃገር የለም፨ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግራ ላጋባው የአፍሪካ ጉዳይ ሻለቃ ዳዊትን በአማካሪነት ይዞ የተጓዘበት አጋጣሚ ብዙ ነው፨ ሃገራቸውን የሚወዱበት ሃያል ፍቅር ልዩ ነው፨ ሁልቀን በዋናነት ሊያስጨንቀን የሚገባው የኢትዮጵያ እንደ ሃገር መቀጠል እንደሆነ አጥብቀው ይናገራሉ፨
ከታላላቆች መስማት የምወድ እኔ በዙከንበርግ ግዛት መስመር ላይ ባየሁዋቸው ቁጥር ወሬ እጀምራለሁ፨ ብዙ እናወራለን፨ ጓደኛን እንደማዋራት ባለ ምቹ ስሜት የተሰማኝን በተሰማኝ ሁኔታ ስናገር በደንብ አድምጠውኝ ግራቀኝ እንዳስተውል የሚያደርገኝን ሃሳብ ያጋሩኛል፨ አሁን ፈጣሪ ብሎ ለቪዥን ኢትዮጵያ የጥናት ወረቀት ሊያቀርቡ በመጡበት በአካል አገኘሁዋቸው፨ ጥናታቸውን ሊያቀርቡ በቆሙበት መድረክ ላይ ሃገራቸው ከረዥም ዘመን በሃላ ስለመመለሳቸው ለመናገር ሲጀምሩ እንባ ቀደማቸው፨ አዳራሹ ውስጥ ያለው ሰው ሴት ወንዱ በእንባ አጀባቸው፨ የሃገር ፍቅሩ አይሎባቸው እንጅ ዝም ብለው የሚያለቅሱ ሰው ሆነው አይመስለኝም፨
የሚያለቅሱላት ሃገራቸው ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ ፀጥታዋ በተናጋበት ወቅት ስለሰላሟ መላ እንዲሉ የእሳቸውን እርዳታ የምትሻበት ነው፨ የመንግስት የፀጥታ እና ደህነት ሹመኞች ይህን ትልቅ ሰው አግኝተው ማነጋገር ቢችሉ ጥቅሙ ለሃገር ነው፨ ሻለቃ ዳዊት ቀርቦ የሚጠይቃቸው ቢኖር ለሃገራቸው ነፍሳቸውን ሳይቀር ለመስጠት የማያመነቱ ሰው ናቸው፨