>

የዘር ማጥፋትን (ጄኖሳይድን) በሽምግልና ለመሸፈን?! (ከይኄይስ እውነቱ)

የዘር ማጥፋትን (ጄኖሳይድን) በሽምግልና ለመሸፈን?!

ከይኄይስ እውነቱ


ነውር ገንዘቡ የሆነው የዐቢይ አገዛዝ ነውረኛና ቋሚ ሎሌው በሆነችው ሙፈሪያት አማካይነት በጎጃሙ መተከል እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) ለመሸፈን እና በፍጅቱ ግንባር ቀደም ተሳታፊ የሆኑ የአገዛዙን ባለሟሎች ከተጠያቂነት ለማዳን አለቃዋ በሰጣት ትእዛዝ መሠረት ለሃይማኖት ተቋማት የሽምግልና ጥሪ እንዳቀረበችና እነሱም በሃሳቡ እንደተስማሙ ሰማን፡፡ እንደተነገረው የሃይማኖት ተቋማት የተባሉትም በሽምግልናው ተስማምተው ከሆነ ማፈሪያዎች ከመሆናቸውም በላይ በዚህ የአገዛዙ ሴራ ተካፋይና ተባባሪ በመሆን ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ በሰማይም እንዲሁ፡፡ ሽምግልና መልካም ተቋምና ተግባር ነው? አዎ! ወንጀልና ወንጀለኛን ለመሸፈን ሳይሆን ለእውነትና ለቅን ዓላማ ሲውል፡፡ 

በርግጥ በአገዛዝ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነትም ሆነ በውስጣዊ ችግር – በሩቁ ከዛሬ 50 ዓመታት ገደማ በቅርቡ ደግሞ ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ – ኢትዮጵያ በሃይማኖት ተቋማት ደረጃ መንፈሳዊነት ወይም የሞራል ልዕልና ያላቸው የሃይማኖት መሪዎች የሏትም ለማለት ያስደፍራል፡፡ ተቋማቱም በባለጌ አገዛዞችና ባለሟሎቻቸው ተደፍረው ቀለዋል፡፡ የሽምግልና ተቋምም እንዲቀል እንዲዋረድ ተደርጓል፡፡ በጥቅል አነጋገር እውነተኛ ሽማግሎችም ተመናምነዋል (በመለስ ተላላኪዎች በእነ ‹ፕ/ር› ኤፍሬም ይስሐቅ ታይቷል)፡፡  ኢትዮጵያ ከምትኮራባቸውና ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ትስስር መሠረት ከጣሉት አገራዊ (ሃይማኖታዊና ባህላዊ) እሤቶች መካከል ፈሪሃ እግዚአብሔር እና ሽምግልና በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የወያኔ/ኢሕአዴግ እና የኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ባለጌ አገዛዞች ባስከተሉት ግዙፍ ማኅበራዊ ድቀት/ልሽቀት ምክንያት ሁለቱም ተቋማት (ሃይማኖት እና ሽምግልና) በእጅጉ ተዳክመው ተአማኒነት ያጡበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ 

ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና እ.አ.አ. 1948 ዓ.ም. የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቅጣት በወጣው ዓለም አቀፍ ስምምነት አንቀጽ 3 መሠረት የዘር ማጥፋት መፈጸሙን መካድ፣ ድርጊቱን በተለያየ መንገድ ለመሸፈን መሞከር የዘር ማጥፋት ግብር አበርነት (complicity in genocide) በሚል የወንጀሉ ብያኔ ውስጥ ተመልክቷል፡፡ ሙፈሪያትና አገዛዙ እየፈጸሙ ያሉት ይሄንን ነው፡፡ ለዘር ማጥፋት ግብር አበርነቱ ተባባሪ ለመሆን ፈቃደኛ የሆኑት የሃይማኖት ተቋማትም ውሳኔያቸውን ቆም ብለው ካላጤኑት በንጹሐን ፍጅት እጃቸውን እያስገቡ እንደሆነ ቢረዱት መልካም ነው፡፡ በአማራ ወገኖቻችንና በርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እየተፈጸሙ ያሉት የዘር ፍጅቶች መካከል ልዩነት ባይኖርም የመተከሉ የአረመኔነቱ ጫፍ ማሳያ ነው፡፡ የወገኖቻችን አስከሬን በክብር ሳያርፍ (ክቡሩ የሰው ልጅ እንደ ‹ቆሻሻ› በግሬደር ተሰቅስቆ ባንድ ጉድጓድ ውስጥ የተወረወረበት ሁናቴ) በነውር ላይ ነውር መጨመር ምን የሚሉት ነው?  በቀደም ወያኔ ‹ክልል› በሚል ባዋቀራቸው የ‹ባንቱስታን› ግዛቶች ለሽብር፣ ሥልጣን ማስጠበቂያ እና ዜጎችን ለማንገላታት በሕገ ወጥ መልኩ ያደራጃቸው ‹ልዩ ኃይሎች› (የየግዛቱ ሕገ ወጥ ሠራዊት) መፍረስ አለበት ስትዪ አድምጠናል፡፡ ሃሳቡ ለረጅም ጊዜ ስንጮኽለትና እንደ ሌሎቹ አንኳር አገራዊ ጉዳዮች ሰሚ ጆሮ አጥተው ነጥረው ከተመለሱት መካከል አንዱ ነው፡፡ በቅንነት ቢነሳ መልካም ነበር፡፡ ግን ኅሊና ካለሽ አንቺም ታውቂዋለሽ፡፡ እኛም በሚገባ እናውቀዋለን፡፡ ዐቢይ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ባካሄደው ጦርነት ወያኔ አማራ ብሎ የሰየመው ግዛት ‹ልዩ ኃይል› አንፀባርቆ በመውጣቱ ዐቢይና ተረኞቹ እነ ሽመልስ ሥጋት ስለገባቸው በአለቃሽ ትእዛዝ የተሠነዘረ ሃሳብ መሆኑ አገሩ ሁሉ ያወቀው ጉድ ነው፡፡ ከመቼ ወዲህ ነው ሎሌ በራሱ ማሰብ የጀመረው?

ሙፈሪያት! ይህ ከሰው በታች መውረድ ነው፡፡ የሎሌነት ጥግ ነው፡፡ ቀድሞ ለሕወሓት አሁን ደግሞ ለተረኞቹ ኦሕዴድ፡፡ ለቤተሰቦቻችሁ ማፈሪያ አትሁኑ፡፡ ቀን ሳለ ሳይጨልም በእውነተኛ ንስሓ ተመለሱ፡፡ መዋቲ ሰው የሠራው ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ አገርና ሕዝብ እያጠፋ ያለን የጐሣ ፖለቲካ፣ የጐሣ ፌዴራሊዝም፣ ‹ክልል› የተባለና ዜጎችን በገዛ አገራቸው መጻተኛ ያደረገ መዋቅር፣ ለነዚህና የሕዝብን አንድነት ላናጋ የፈጠራ ትርክቶች ሕጋዊ ሽፋን የሰጠው የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት›ን ቀዳዶ ጥሎ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጐሣና በሃይማኖት ማንነታቸው ልዩነት ሳይደረግባቸው ለእኩልነት፣ ለአንድነትና ለአብሮነት ሥርዓት አዲስ ምዕራፍ መክፈት ይቻላል፡፡ ይህ ምዕራፍ እናንተ በተንኰል በምታስቡት የውሸት ምርጫ ግን በጭራሽ አይመጣም፡፡ በጭራሽ! በጭራሽ! 

ሥልጣን በአረመኔነትና በጉልበት አደላድሎ ተጨማሪ ግፎችን ለመፈጸም ሳይሆን የተበደሉትን አእላፋት ለማካሥ፣ በግፍ የተጨፈጨፉትን በክብር ለማሳረፍና መታሰቢያ ለማቆም፣ የፈረሰውን ለመገንባት፣ የጎደለውን ለመሙላት፣ የጠመመውን ለማቅናት፣ የደፈረሰውን ለማጥራትና ከመንደር ወደ አገር ለመውጣት የኢትዮጵያ ሕዝብ የመጨረሻ ዕድል የሰጣችሁ ይመስለኛል፡፡ ዕድሉ ካመለጣችሁ በኋላ የምታደርጉት ጩኸትና ጸጸት እንደ ግብር አባታችሁ ወያኔ/ሕወሓት የማይጠቅምና ከንቱ ይሆናል፡፡

እናንተ የሃይማኖት ተቋማትን እንመራለን የምትሉ ‹አባቶች› በቅድሚያ ከራሳችሁ፣ ቀጥሎም በእረኝነት እንጠብቃቸዋለን ከምትሏቸውና ባዝነው ከቀሩት ምእመናን ሳትታረቁና ከአድርባይነት ወጥታችሁ ቤታችሁን ሥርዓት ሳታስይዙ ለሽምግልና አትበቁም፡፡ ለአማኙ ሕዝብ እውነትንና መንፈሳዊነትን ይዛችሁ አርዓያ ሳትሆኑ ያውም በሽምግልና ስም ከዘር ማጥፋት ወንጀለኞችና ግብረ አበሮቻቸው ጋር ተባባሪ ለመሆን መዘጋጀት ምን የሚሉት ነውር ነው? ይህንን ከአገዛዝ ሥር መንከባለል አቁማችሁ የሰማያዊ መንግሥት እንደራሴነታችሁን በቃልም በተግባርም አሳዩን፡፡ ወያኔ ያስቀመጣቸውን ካድሬዎች ከየቤተእምነታችሁ አውጡ፡፡ ራሳችሁን አስከብራችሁ እኛንም አስከብሩን፡፡ የአገዛዝ ሹመኞች በመሆናችሁ ሳይገባችሁ ቦታው ላይ የምትገኙ ቦታውን ለቃችሁ (የየሃይማኖቱ ሰዎች ከሆናችሁ) ራሳችሁን ፈትሹ፡፡ ለአብነት ያህል በየደረጃው ያላችሁ የርትዕት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አመራሮችን ብንወስድ ሌላውን ሁሉ ትተን በመተከል የተዋሕዶ ተከታይና አማራ በመሆናቸው ስለተጨፈጨፉት ወገኖቻችን ምን አላችሁ? ሲቻል መንግሥትን ተገዳድሮ ቦታው ድረስ በመሄድና ምእመናንን በማስተባበር ለጊዜው ከሞት ተርፈው በሥጋትና በሰቀቀን ከነቤተሰቦቻቸው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በሜዳ ላይ ጦማቸውን እያደሩ ያሉ ወገኖቻችን ማጽናናትና አስቸኳይ ርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ፣ አስከሬናቸው እንደ አልባሌ ዕቃ በግሬደር እየተሰበሰበ የተወረወሩትን ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎላቸው የክብር ቀብር (decent burial) እንዲያገኙ ማድረግ አይጠበቅባችሁም? አገዛዙን በመለመን የሚገኝ ነገር አለ? ሕፃናት፣ እናቶችና አረጋውያን እየተጨፈጨፉ ባለበት ምድር ፣ ምዉት ነን ላላችሁት ለዚህ ዓለም ምን አለበት አንድ ጊዜ እንኳን የሃይማኖት ጥብዐትን ብታሳዩን? የሌሎችም ቤተ እምነቶች አመራሮች ዜጎች ባገራቸው፣ አይደለም ለማየት ለመስማት የሚሰቅቅ ግፍ ሲፈጸምባቸው ምን እያደረጋችሁ ነው? ጭራሽ ይሄንን አረመኔነት በሽምግልና ስም ለመሸፈን ከሚሯሯጥ አገዛዝ ጋር ኅብረት ታሳያላችሁ? እውነት እናንተ የምድራዊ ገዢዎች ሎሌ ወይስ የሰማያዊ መንግሥት እንደራሴ ናችሁ? የሃይማኖት ተቋማት ከየእምነቱ ተከታዮች ውጪ ህልውናችሁ ምንድን ነው? ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ክቡሩ የእግዚአብሔር ‹ቤተመቅደስ/ሕንፃ እግዚአብሔር› (የሰው ልጅ) በየቦታው በአረመኔዎች እጅ እየፈረሰ ነው፡፡ 

ስለሆነም ‹ሽምግልና› ከሚለው የአገዛዙ ዋዛ ፈዘዛ ትርኢት ራሳችሁን አርቁ!!! ጊዜው አጉል ሆኖ ውኃ ሽቅብ መፍሰስ ስለጀመረ አንድ ኃጢአተኛና ታናሻችሁ ወደላይ አንጋጦ ገሠፀን፣ ተናገረን በሚል መልእክቴን እንዳታቃልሉት፡፡ ኅሊናችሁን ተከትላችሁ ተገቢውን አድርጉ፡፡

በቀል የኔ ነው ያለ እግዚአብሔር አምላክ በግፍ የተጨፈጨፉ የወገኖቻችንን ደም ከንቱ አያስቀርብን፡፡ 

 

እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!! 

ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡

ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡

Filed in: Amharic