>

አብደአመቱ...!!! (በእውቀቱ ስዩም)

አብደአመቱ…!!!

(በእውቀቱ ስዩም)

* “ ጄንዎሪ ሲመሻሽ፤ ርችት ሲፈነዳ
እንኩዋን ሰው ዘመዱን ፤ ያስከትባል ባዳ “
እንሆ በጎርጉራውያን ዘመን አቆጣጠር 2021 ገባ!
 በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ግን ገና  2013  ነው ፤
 እንዲህ አይነት ልዩነት  እንዴት ሊፈጠር ቻለ?   ከሁለቱ የካሌንደር ቀማሪዎች አንዱ ሂሳብ ይፎርፍ እንደነበር በመገመት እንለፈው ፤  ዘመን መለወጫ ድሮ ቀረ ! ማለቴ ኢትዮጵያ ቀረ!  እኔ ጋ  ያለ በረዶ ይወርዳል ፤  እዚህ ገና በረፋድ ላይ  ይጨልማል ፤  እኔም በጊዜ ተጠቅልየ እተኛለሁ፤
 ቅድም፤ አንሶላየ ውስጥ ጋደም ብየ በትልቅ ሚዶ  ሳበጥር የቤቴ በር መጥርያ እሪሪሪሪ አለ፤ በሶስት ቋንቋ   እየተራገምኩ በሩን ከፈትኩ፤
በር ላይ ጎረቤታችን ሴትዮ ቆማለች፤ እጆቿን  ወደ ሁዋላ ደብቃቸዋለች
“ ሚስተር ስዩም”
“ አቤት ! “
 ፈገግ ብላ አየችኝ ፤ ፈገግታየን እንደ እንጀራ ፊቴ ላይ አስፍቼ  ለሰርፕራይዝ ተዘጋጀሁ፤ ዝም ብላ ፈገግ እንዳለች ቀረች፤  ትግስቴን ስለጨረስኩ እጇን ጠምዝዤ ስጦታውን መንጠቅ ሁሉ አማረኝ !
“ እንኳን አደረሰህ! በረንዳ ላይ ተከምሮ መተላለፍያ ያሳጣንን  በረዶ የምትዝቅበት ይሄንን  አካፋ አበርክቸልሀለሁ”
“ አካፋ ለኔ?’ አልሁኝ  ሆድ ብሶኝ !
“ በረዶው በዚህ ከቀጠለ ከከተማው አስተዳደር  ጋር በመተባበር  ቡል ዶዘር እናበረክትልሀለን”
 በሬን ዘግቼ  ቲቪ ከፈትኩ፤ የፈረንጆች ደመረ ለገሰ ፤  የክት(ባት)  ልብሱን እንደለበሰ
“ Happy happy new year
happy new year “
እያለ ይዘፍናል ::
አዛማጅ ትርጉም
“ ጄንዎሪ ሲመሻሽ፤ ርችት ሲፈነዳ
እንኩዋን ሰው ዘመዱን ፤ያስከትባል ባዳ “
በነገራችን ላይ  ኢትዮጵያ ውስጥ  ህዝቡ ኮረና መፍራት ማቆሙን ራሴው አረጋግጫለሁ ፤ዶክተር ሊያ በገጿ ላይ የሞተውና የቆሰለውን ስትዘረዝር ፌስቡከኛው  የሳቅ ምልክት ይጎዘጉዝላታል ፤ ይሄንን ስታይ፤  ተስፋ ቆርጣ ወደ ግብርና ሚንስትር አዛውሩኝ አለማለቷ እምደንቅ ነው!
መልካሙ ዜና ክትባት ተጀምሯል፤ መጥፎው ዜና በቀላሉ እሚደርሰኝ አይመስለኝም፤ መጀመርያ ነርሶችና ሀኪሞች ፤ቀጥሎ ከሰባ አመት በላይ የሆናቸው አዛውንቶች- ቀጥሎ ሰፊው ህዝብ- በመጨረሻ የኔ አይነቱ ይደርሰዋል፤
ይህንን ለበየነ ደውየ  ስነግረው ምን አለኝ ፤
“ ትክክለኛ እድሜህን ብትነግራቸው እኮ ቅድሚያ ይሰጡህ ነበር’
“ሰው እኮ እህህህ ! “ አለ የማሸንበቆ  ቤት ግድግዳ ጥቅስ!
በደምሳሳው ካየነው ይሄ አመት ብሽቅ አመት ነበር፤ የሆነ ጊዜማ የምር ምርር ብሎኝ ኑዛዜየን ፅፌ፤ በከተማው ዳር በቆመው  ህንፃ  ስምንተኛ ፎቅ ላይ ወጣሁ፤
 እዛ ተከራይቼ መኖር ከጀመርሁ ይሄው ሶስት ወር ሞላኝ!
Filed in: Amharic