>

የትግራይ ህዝብና የአማራ ህዝብ ከአንድነት በላይ ናቸው...!!! (አብርሃም አለህኝ)

የትግራይ ህዝብና የአማራ ህዝብ ከአንድነት በላይ ናቸው…!!!

አብርሃም አለህኝ

 

በሎጥ ዘመን ከደረሰው መከራ በቃል ኪዳኑ ድነናል። የአብርሃምን የእንባ መአዛ አሽትተን ከመምሬ አድባሬ ዛፍ ስር ተገኝተን ጥበብ ምድር ወሰማይ ተቀብለናል። በፈሪሀ እግዚአብሄር ተኮትኩተን አድገናል። ወደግብጽ ብንሰደድም ዘራችን ባቦካው እጡብ ግሩም ድንቅ ሀውልት አንጸን ለአለም አስረክበናል።  ከመልከጼዴቅ ጻህል መንፈሳዊ ህብስት ተጋርተናል። በሙሴና በአሮን እግር ስር ቁጭ ብለን ስርአተ ክህነትን ከስርአተ መንግስት ጋር አስተባብረን የፈርኦንን የአመራር ጥበብ ከዮቶር የክህነት ምስጢር ጋር አሰናስለን የአክሱምን ጥበበ ምድርነት ከስነህንጻ ጀምሮ እስከ ስነ ፍጥረት ወመለኮት አሻራችንን አስቀምጠናል።
በቀዳማዊ ምኒልክም ሆነ ከዚያበፊት እንደአሁኑ አማራ ትግሬ ሳንባባል አብረን ኖረናል። ከቀዳማዊ ይስሀቅ የወረደውን የንጉስ ዳዊትን የዘር ቋጠሮ ፈትተን በጋራ ገምደናል።  ከይስማኤል የዘር አንጓ ክፋዩን ተዋህደን በፍቅርና በአንድነት የሰላም እልልታችንን አቅልጠነዋል።  በንግስት ህንዳኬ በኩል ጠቢቡ ሰለሞንን አግኝተን ማህልይ ማህልይ ዘሰለሞንን ዘምረናል። በወይኑ አትክልት እርሻ ላይ ተገናኝተን አኩኩሉ አልጠባም የእምቦቃቅላ ንጹህ ልብ ጨዋታ እየተጫወትን ቦርቀናል። ተዋደንና ተፋቅረን፣ ተጋብተን ተዋልደናል። የአብርሀ ወአጽብሀ የኢዛናና ሳይዛና መንበረ መንግስትን አጽንተናል።  የነብዩ መሀመድን መልዕክተኞች በፍቅር ተቀብለን የክርስትና እምነት አቻ ወዳጂ፣ የብዝሀ እምነትን አፅመ ሀውልት መስርተናል። ከዚያም ክርስትናን ከእስልምና ክርስቲያን ማህበረሰባችንን ከሙስሊም ማህበረሰባችን ጋር አቀራርበን አዋህደን አኑረናል። አልፎ አልፎም በጋብቻ ተጣምረው በቤተሰብ ደረጃ የሃይማኖት ብዝሀነትን አክብሮ በፍቅርና በትብብር የሚኖር የማህበረሰብ ስብጥር ፈጥረናል። አልነጃሽ ገብተን ኢዛና ስናደርስ አክሱም ፣ ተድባበ ማርያምና መርጦለማርያም ላይ ከምኩራብ እስከ ቤተመቅደስ አገልግሎት የደረሰ መንፈሳዊ ቃልኪዳን ፈጽመናል።
የተሰአቱ ቅዱሳን መናገሻ ሆነንም አገልግለናል። የአባቶቻችንን እግር አጥበን ጽዋዕ በረከት ተጎንጭተን ጨልጠናል። ቡራኬ አበውንና በረከተ እመውን ተቀብለን ሽህ አመታት በፍቅር ዘልቀናል።
እንደዛሬው አማራና ትግሬ ሳንባባል በንጉሰ ነገስት አፄ ካሌብ ስር ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን በአክሱም ጉበን ላይ አትመናል።
እንደዛሬው አማራና ትግሬ ሳንባባል በአጼ ነአኩቶ ለአብ ስር  ምጡቅና ድንቅ ቃልኪዳን አስረናል።
በእነቅዱስ ያሬድ ወንበር ስር ቁጭ ብለን ድጓ ፣ ፆመድጓ ዜማን ተምረናል። የግዕዝ ማር ልሰን ጣዕመ ምስጢርን በእጅጉ ቀስመናል። በእዝል መንኮራኩር በአራራይ ደመና ወደላይ በረናል።
የአማራ ህዝብና የትግራይ ህዝብ ከአንድነት በላይ ነው የምንለው በምክንያት ነው።
ምድራዊና ሰማያዊ ማዕድ በጋራ እየተካፈለ እዚህ ለደረሰ ህዝብ አንድነት ምኑ ነው ? ትግራይ ክልል ያለ አማራ ክልል የሌለ ምን አለ ? አማራ ክልል ያለ ትግራይ ክልል የሌለስ ምን አለ ? ሁሉም በሁሉ የሁሉ የሆነው ሁሉ የሁሉም ነው። የአማራም የትግሬም ነው። የአማራ የሆነው ሁሉ የትግሬ ነው። የትግሬ የሆነው ሁሉ የአማራ ነው። ሁሉም አንድና ያው ናቸው። ከአንድነት በላይ የሆነ አንድነት። ከአዳም እስከ ኖህ ፣ ከኖህ እስከ ሄኖክ ፣ ከሄኖክ እስከ መልከጼዴቅ ፣ ከመልከጼዴቅ እስከ ቀዳማዊ ምኒልክ ፣ ከቀዳማዊ ምኒልክ እስከ አፄ ካሌብ ፣ ከአጼ ካሌብ እስከ አጼ ገብረመስቀል ፣ ከአፄ ገብረመስቀል እስከ ዛሬ  የዘለቀ ውሁድ ማንነት።
ይኸን ከአንድነት በላይ የሆነ ህዝብ ሊነጣጥለው የሚችል ማንም የለም። አክሱም ፣ አድዋ ፣ አዲግራት ሽሬና መቀሌ የአማራ ህዝብ መናገሻ ከተሞች ናቸው። ባህርዳር ፣ ደብረብርሃን ፣ ደሴና  ጎንደር የትግሬ መዳረሻና መናገሻ ከተሞች ናቸው።  ሁሉም በሁሉ የሁሉ የሆነውም ሁሉ በሁሉ ነው የምንለው መሬት ላይ ያለ ሀቅ ስለሆነ ነው።
በሽታው ፖለቲካውና ፖለቲከኞች ናቸው። እኛ ፖለቲከኞች ከህዝቡ ስንነጠል ህዝቡ በቤተመስጊድ ኢዛና ሲያደርስ ፣ በቤተመቅደስ ደግሞ ሰአታት ይቆማል። ህዝቡ ከአንድነት በላይ ነው የምንለው በምክንያት ነው።
ችግሩ ከምንከተለው ነጣጣይና ከፋፋይ ፖለቲካችን ነው። ፖለቲካችንን ከህዝቡ ጫንቃ ስናንሳ የህዝቡ ትክክለኛ ገጽታ ይገለጣል። የአማራና የትግራይ ህዝብ ከአንድነት በላይ ነው የምንለው ከአንድነት በላይ ስለሆነ ብቻ ነው።
እኛ ፖለቲከኞች የፈጠርነው ችግር ሳያንስ ችግሩን ሁሉ ምንም ለማያውቀው ህዝብ ለማሸከም ጥረናል። በየትኛውም የአለም ታሪክ የፖለቲካ ፓርቲና ህዝብ አንድና ያው ሊሆን አይችልም። የአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ፍልስፍናና የህዝብ የህይወት ፍልስፍና በፍጹም አንድ አይደለም። አንድ የሆነበት የታሪክ አጋጣሚም የለም።
ትህነግና የትግራይ ህዝብ በፍጹም አንድ አይደለም። አንድ ሊሆንም ከቶ  አይችልም። ትህነግና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው ማለት ብርሀንና ጨለማ አንድ ነው እንደማለት ነው። የትግራይ ህዝብ ብርሃን ነው። ትህነግ ደግሞ ጨለማ፣ ከጨለማም ጨለማ ድቅድቅ ጨለማ። ስለሆነም ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ህብረት አለው ብለን እንጠይቃለን።
የአማራ ህዝብና የትግራይ ህዝብ ከአንድነት በላይ ነው የምንለውም ብርሀናዊ ማንነታቸውን የሚፈታተን ጨለማ በፍጹም ሊያደበዝዘው የማይችል የብርሀን ውጤቶች ስለሆኑ ነው።
ችግሩ ያለው ከጨለማው ያውም ከድቅድቅ ጨለማው ነው።
ተፈጥሮ ፣ ታሪክ ፣ ሃይማኖትና ባህል አንድ ያደረገውን ህዝብ ማንም ሊነጣጥለው አይችልም።
Filed in: Amharic