>

የጎንደር ከንቲባ ገብሩ ደስታ  ...!!! (ሳሚ ዮሴፍ)

የጎንደር ከንቲባ ገብሩ ደስታ  …!!!

ሳሚ ዮሴፍ

ከንቲባ ገብሩ ተብለው ከመጠራታቸው በፊት ጎባው ደስታ በመባል ይታወቁ ነበር። ጎባው ከአቶ ደስታ ወልደእሴይና ከወይዘሮ ትርንጎ ተክሌ በጎንደር ክፍለ ሀገር በአለፋ ወረዳ  በ1848 ዓ.ም ተወለዱ።
ጎባው ከወላጆቻቸው ጋር እያሉ ትምህርት ያላገኙ በመሆናቸው በአጤ ቴዎድሮስ ሥር ወደ ነበሩት አጎታቸው ወደ ሻቃ ውቤ ዘንድ ትምህርትና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በቤተሰቦቻቸው ፈቃድ ሄዱ። አጎታቸው ቤት ሁሉም ነገር እንዳሰቡት ሆነው ስላላገኙት አሁንም ለተሻለ ህይወት ወደ ቴዎድሮስ ከተማ ወደ ደብረ ታቦር ከሌሎች መንገደኞች ጋር በመሆን ጉዟቸውን አቀኑ በአስራ አንድ ዓመታቸው። እዚያ እንደደረሱ የአጤ ቴዎድሮስ የቅርብ አማካሪ የነበሩት የሊቀ መኳስ ዮሐንስ ቤል (ጆን ቤል) ልጅ ዮሴፍ ቤል ያገኛቸዋል። ዮሴፍ ቤል ከወይዘሮ ወርቅናሽ ይልማና ከጆን ቤል የተወለደ ሲሆን እህቱ ሳራ (ሱዛን የውብዳር) ደግሞ ሚሲዮናዊውን የስዊዝ ተወላጅ ቴዎፍሎስ ዋልድሜይርን አግብታ ትኖር ነበር። ዮሴፍ ቤል የንጉሥ ሳዖል ልጅ ዮናታን ዳዊትን እንደወደደው ሁሉ ጎባው ላይ ቀልቡ አረፈ ወደዳቸው። ስለሆነም ወደ ሳራና ቴዎፍሎስ ዋልድሜየር ቤት ይወስድና ያስተዋውቃቸዋል። የጎባው አዲስ ህይወት ‘ሀ’ ብሎ እዚህ ላይ ጀመረ። ጎባው በጥሩ ሁኔታ በአካልም በእውቀትም እያደጉ ሄዱ።
በጊዜው አጤ ቴዎድሮስ በዙሪያቸው የነበሩትን የውጭ ሀገር ዜጎች ባሰሩበት ወቅት የእንግሊዝ ጦር መጥቶ እስረኞቹን ባስፈታበት ሰዓት እንግሊዞች…
* ዓለማየሁ ቴዎድሮስን እና ወርቅነህ እሸቴን (ሀኪም) ሲወስዱ…
* ኃይሉ ወሰን፣ ሰንበቱ ዳንኤልንና ጎባው ደስታን ሚስዮናዊው ቴዎፍሎስ ዋልድሜየር ከኢትዮጵያ ይዘው ወጡ። ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ወደ እንግሊዝ፣ ወርቅነህ እሸቴ ወደ በርማ፣ ጎባው ደስታና ሌሎቹ ወደ እየሩሳሌም ተወሰዱ።
ጎባው እየሩሳሌም በነበረው በዮሐናን ሉድዊግ ሽኔለር
(Johanan Ludwig Scheneller) የሚሲዮን አዳሪ ትምህርት ቤት በቢሾፕ ሳሙኤል ጎባት አማካኝነት ገብተው ለሶስት ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታተሉ።
ቴዎፍሎስ ዋልድሜየር “የሚሲዮናዊነት ሥራ አስር ዓመት በኢትዮጵያና ስልሳ ዓመት በሶሪያ” በሚለው የህይወት ታሪካቸው መጽሐፍ እንደጻፉት
“ጥቂት የተማሩ ሰዎችን ከኢትዮጵያ ወደ እየሩሳሌም ወስደን በቢሾፕ ሳሙኤል ጎባትና በሚስተር ሽኔለር ወላጅ የሌላቸው ልጆች በሚማሩበት አዳሪ ትምህርት ቤት አስገብተናቸው ሲማሩ ከቆዩ በኋላ ስዊዝ በሚገኘው ቅዱስ ክሪሾና መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሄደው እንዲማሩ አድርገናል”
ጎባው በ1872 ዓ.ም ወደ ስዊዘርላንድ ተልከው ከእነሱ ቀድመው ከሄዱት ከቤተ እስራኤሎቹ ሚካኤል አረጋዊ፣ ሰማኒ ዳንኤልና አጋዤ ሳክሉ ጋር በቅዱስ ክሪሾና መንፈሳዊ ኮሌጅ ለአራት ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል። ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንኽረስት እንደ ገለጹት ከጎባው ደስታ በስተቀር ሌሎቹ በሙሉ ከጎንደር አካባቢ ወደ ክርስትና የገቡ ቤተ እስራኤሎች ናቸው።
(History of Education printing and literacy in Ethiopia- prof- Richard Pankhurst).
ጎባው ደስታ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ቢፈልጉም በጊዜው ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር በነበራት ግጭት መንገድ አመች ባለመሆኑ ሃሳባቸውን ቀይረው ወደ ጀርመን ወርትንበርግ በመሄድ ከሚሲዮናዊው ሉድዊግ ክራፕ (Ludwig Krapf) ጋር በመሆን ከፊል የሀዲስ ኪዳን መጻሕፍትንና ቀደም ብሎ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ የነበረውን መጽሐፍ ቅዱስ በማረም ሲረዱ ቆይተው ከሀገራቸው ከወጡ ከ15 ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።
ጎባው ኢትዮጵያ እንደገቡ ቀጥታ ወደ ጎንደር በመሄድ በጎንደር ክፍለ ሀገር አዘዞ ከተማ ትምህርት ቤት ከፍተው ማስተማር ጀመሩ። ነገር ግን የአካባቢው ካህናት ሊያሠሯቸው ስላልቻሉ ትምህርት ቤቱን ዘግተው ወደ ወለጋ ክፍለ ሀገር በመሄድ ልዩ ስሙ “ጉድሩ” በሚባል ቦታ ትምህርት ቤት ከፍተው ሲያስተምሩ ከቆዩ በኋላ 1887 እ.ኤ.አ. እንደገና ወደ እየሩሳሌም ተመለሱ። ከእየሩሳሌም ወደ ሶሪያ ተልከው በጀርመን የሚሲዮን ትምህርት ቤት ሲያስተምሩ ቆዩ። ከዚያም በታንጋኒካ (ታንዛኒያ) ዳሬሰላም ከተማ አዲስ የተከፈተውን የሚሲዮን ትምህርት ቤት ለማጠናከር ወደዚያ ተላኩ። ከዳሬሰላም ቆይታቸው በኋላ በኤደን በኩል ወደ እየሩሳሌም ጉዞ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ከኢትዮጵያ ተጠልፈው ለባርነት ሊሸጡ ሲሉ በእንግሊዝ የባህር ኃይል ኮማንደር (በቻርለስ ኢ. ጊሲኒማ) ነፃ የወጡ የኦሮሞ ወጣት ወንድና ሴት ልጆችን ኤደን ላይ አገኙ።
ጎባው ደስታ እነዚህን ወጣቶች በኦሮምኛ አነጋግረው ካጽኗኗቸው በኋላ እነሱን በማስተማር እዛው ኤደን ሥራ ጀመሩ። የጎባውን የኤደን ጉዞና ቆይታ ከዓመቱ ምህረቱ ጋር ሲገናዘብ በB.B.C. በእንግሊዝ የዜና ማሰራጫ ድህረ ገጽ ላይ ወጥቶ ለንባብ ከበቃው ታሪክ ጋር አንድ ሆኖ ይገኛል።
ታሪኩ በአጭሩ እንዲህ ነበር…
በ1888 እ.ኤ.አ. የወጣቶቹን አመጣጥና ነፃ አወጣጥ ካተተ በኋላ ከፊሎች የእስልምና እምነት ተከታይ የነበሩት ወጣቶች ኤደን ውስጥ ኗሪ በሆኑ የእምነቱ ተከታዮች በማደጎነት የተወሰዱ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ለጊዜው ኤደን በሚገኘው የስኮትላንድ ሚሲዮናውያን ቤተ ክርስቲያን ከቆዩ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ልዩ ስሙ ላቭዴል ወደሚባል ቦታ ለሚሲዮናዊያን በአደራነት ይሰጣሉ። በዚህ ቦታ የክርስትና እምነትን ተቀብለው በአካልና በዘመናዊ ትምህርት እያደጉ ለመምህርነትና ለተለያዩ ሥራዎች ራሳቸውን እንዳዘጋጁና ከመካከላቸው አንዷ ቢሾ ጃርሳ ስልጠናዋን ጨርሳ መምህርት እንደሆነችና የቤተ ክርስቲያን መጋቢ (መሪ) አግብታ ዲምቢቲ የምትባል ልጅ እንደወለደች ያትታል።
አፍሪካ ከተወሰዱት መካከል አስራ ስምንቱ እስከ 1903 እ.ኤ.አ. ድረስ በሞት የተለዩ ሲሆን አስራ ሰባት ፈቃደኛ ወጣቶች ደግሞ በአጤ ምኒልክና በጀርመን አማካሪዎቻቸው
(ከንቲባ ገብሩ አብረዋቸው ይሠሩ የነበሩ) ብርታት ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ እንደተመለሱ ይገልጻል።
ዲምቢቲ ዳቪድ አሌክሳንደር የሚባል ሰው አግባታ ይህን ታሪክ የጻፈውን ባንድ ወቅት ብሔራዊ ነፃ አውጭ ድርጅት በመባል የሚታወቀውን የፖለቲካ ድርጅት ካቋቋሙትና በዚህም ምክንያት ከነፃነት ታጋዩ ከፕሬዚዳንት  ከኔልሰን ማንዴላ ጋር አብሮ ታስሮ የነበረው (ሮቢንስ ደሴት) ታዋቂው ምሁርና መምህር የሺሾ ጃርሶ የልጅ ልጅ ዶክተር ኔቬል አሌክሳንደር ይገልጻል። ኔቬል አሌክሳንደር ከዚህ በተጨማሪ የአስራ ሰባት (ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ) ሰዎችን ስም ዝርዝር በማውጣት እነዚህን ሰዎች የሚያውቁ ወይም ቤተሰብ የሆኑ ሰዎችን በማፈላለግ ላይ እንደሆነ ብሎም የአያቱን
የቢሾ ጃርሳን ዘመዶች ማወቅ እንደሚፈልግ ጠቁሟል።
BBC “How an Ethiopian Slave become a south African Teacher” 25 August 2011.
እነዚህ ወጣቶች ላቭዴል ከተወሰዱና ጎባው ደስታ ስማቸውን ገብሩ ብለው ከቀየሩናFreedom,የከንቲባነት ማዕረግ ካገኙ በኋላ ነገሮ ጫሊ የተባለ ወጣት ላቭዴል ሶስት ዓመታት ቆይቶ በመምህርነት በሰርተፊኬት ተመርቆ በኤደን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ እዚያው ኤደን ውስጥ እነሱን
(ነጻ የወጡትን) መጀመሪያ ተቀብሎ ባስተናገዳቸው ሚሲዮን ትምህርት ቤት ውስጥ በማስተማር ላይ እያለ በንጉሥ ኤድዋርድ ክብረ ንግሥና ላይ ለመገኘት በራስ መኮንን መሪነት የሄደውን የኢትዮጵያ መልእክተኛ ቡድንን እንዳገኘ ከነሱ መካከል በ1889 ኤደን በሚገኘው እሱ እያስተማረ ባለበት ትምህርት ቤት የሼክ ኦትማን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ያስተማሩትን ከንቲባ ገብሩን እንዳገኛቸው እንዲህ በማለት ገልጾታል።
“የተከበሩ ከንቲባ ገብሩ ሲያዩኝ በደስታ ከመቀመጫቸው ብድግ በማለት ሰላም አሉኝ። ከጧቱ ሁለት ሰዓት እስከ ቀኑ ስምንት ሰዓት አብሬያቸው ቆየሁ። ላቭዴል ከቀሩት መካከል ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ካሉ ከአጤ ምኒልክ ጋር በመነጋገር እንዲመለሱ የሚጥሩ መሆናቸውን ነግረውኛል”
(Lovedale News Christian Express 1 January 1901-4)
የእነዚህ ወጣት ወንድና ሴት ኦሮሞ ተጠላፊዎች ታሪክ
“From Slavery to Freedom, The Oromo Children of Lovedale” Sandra Rowoldt Shell…Thesis for phd (Acadamia edu) በሰፊው ተጠቅሷል።
እነዚህን ከጠላፊ እጅ ነፃ የወጡ ወጣቶች ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ጎባው ከኤደን ወደ እየሩሳሌም ጉዞአቸውን በመቀጠል የሚሲዮናዊውን የክርስቲያን ቬንደርን ልጅ ማርታን አግብተው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በራስ መኮንን ግዛት ሐረር ከተማ ኑሯቸውን መሠረቱ። ሆኖም ወጣቷና የስድስት ወር ነፍስ ጡር የነበረችው ባለቤታቸው ማርታ በኮሌራ በሽታ በሞት ተለየቻቸው። ማርታ ቬንደር የተወለደችው ከአባቷ ከሚሲዮናዊው ከክርስቲያን ቬንደር እና ከእናቷ ከወይዘሮ የሺመቤት ሸምፐር ነበር። ወይዘሮ የሺመቤት ሸምፐር ደግሞ የታዋቂው ጀርመናዊ ዕፅዋት ተመራማሪ የሄንሪ ሸምፐር እና የአድዋ ተወላጅ የሆኑት የወይዘሮ ምርጺት ልጅ ናቸው። ( A Princess in the Family by Annie and Tony Betts published by Domtom Publishing Ltd, Burgess Hill UK 2010.)
የመጀመሪያዋ የሴት ጋዜጠኛና ተወዳጅ የነበረውን የምግብ አሠራር ትምህርት በኢትዮጵያ ራዲዮ በ1950ዎቹ ያቀርቡ የነበሩት የወይዘሮ ሮማን ወርቅ ካሳሁን አያት (ካሳሁን ሻምፐር) እንዲሁም ባዘል ከተማሩት ወጣቶች አንዱ የነበረው እንግዳሸት ሻምፐር የሄነሪ ሻምፐር ልጆች መሆናቸውን ኮሎኔል ዳዊት በመጽሐፋቸው ገልጸውታል።
(ከንቲባ ገብሩ የኢትዮጵያ ቅርስ)
ጎባው በራስ መኮንን ስር የሐረር ከተማ ሹም ሆነው ሠርተዋል። በዚህ ጊዜ በእየሩሳሌም የኢትዮጵያ ንብረት ጉዳይን በሚመለከት ለመነጋገር ከመምህር ወልደ ሰማያት፣ ከፊታውራሪ ኃይለስላሴ (የራስ እምሩ አባት) እና ከጸሐፌ ትእዛዝ ወልደ ሩፌ ጋር በመሆን ኢየሩሳሌም በመሄድ ተልዕኳቸውን ተወጥተዋል። ሲመለሱም ሶስት ባለ ልዩ ጥራዝ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለአጤ ምኒልክ አምጥተው ሰጥተዋል።
በ1895 ዓ.ም ጎባው ደስታ አጤ ምኒልክ ዘንድ በመቅረብ ሁለት ጥያቄዎችን አቀረቡ።
1ኛ/ ስማቸው ገብሩ ደስታ ተብሎ እንዲቀየርና
2ኛ/ በትውልድ ሀገራቸው በጎንደር ከንቲባ አድርገው እንዲሾሟቸው።
ሹመቱና ስም መቀየሩ ጸድቆላቸው ከንቲባ ገብሩ ደስታ ተብለው የጎንደር ከንቲባ ሆኑ።
ከንቲባ ገብሩ ደስታ አጤ ዮሐንስ መተማ ላይ ከሱዳን ጋር በተዋጉበት ጊዜ በምርኮ የተወሰዱትን ሰዎች ለማስፈታት መልእክተኛ በመሆን ወደ ሱዳን ተጉዘው ለሀገሪቱ መሪ (ለከሊፋው) በጠራ አርብኛ ቋንቋ አቤቱታቸውን አሰምተዋል። ንግግራቸውም በጊዜው በሀገሪቷ ጋዜጣ ተጽፎ እንደነበር ይታወሳል። እንዲሁም የንግሥት ቪክቶሪያ ልጅ ኤድዋርድ ሰባተኛ የታላቋ ብሪታንያ ንጉሥ በዓለ ንግሥና በስነ ስርዓቱ ላይ ከልዑል ራስ መኮንን ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ወክለው ተገኝተዋል፤(1901 እ.ኤ.አ.)…ከዚህ በተጨማሪ የንግሥት ቪክቶሪያ የልጅ ልጅ የጆርጅ አምስተኛ ክብረ ንግሥና ላይ
ከቀኛዝማች ብስራት፣ ከነጋድራስ አበቤ፣ ከብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ስላሴና ከደጃዝማች ካሳ ኃይሉ (በኋላ ራስ) ጋር በመሆን በበዓሉ ተገኝተው ተመልሰዋል።
በ1911 እኤአ ጣልያንን፣ ፈረንሳይን፣ ቱርክንና ጀርመንን ጎብኝተው ከእነዚህ ሀገሮች መንግሥታት የኒሻን ሽልማቶችን ተቀብለው ተመልሰዋል።
በተጨማሪ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደሌሎቹ አፍሮ አሜሪካውያን ሁሉ የዘር ልዩነት እየተደረገባቸው ይቸገሩ ስለነበርና የባለ ቃልኪዳን ሀገሮች የአንደኛው የዓለም ጦርነት በድል መወጣትን አስመልክቶ የደስታ መግለጫ ለማቅረብ እንዲሁም በሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ጉዳዮች ላይ ለመነጋገርና ውይይት ለማድረግ
ከደጃዝማች ተሰማ ናደው (በኋላ ራስ ቢትወደድ)፣ ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ስላሴ፣ አቶ ስንቄ (የደጃዝማች ተሰማ ጸሐፊ) ጋር በመሆን መጀመሪያ ወደ እንግሊዝ ቀጥሎም ወደ ኒውዮርክ በንግሥት ዘውዲቱና በአልጋ ወራሽ ተፈሪ ፈቃድ ተጉዘው ተልዕኳቸውን ተወጥተዋል።
ይህ የልዑካን ቡድን እንግሊዝ ሲገባ በታዋቂው ሳቮይ ሆቴል እንዳረፈና በቆይታቸው የሚያስተናግዳቸው አንድ መኮንን እንደተመደበላቸው ተገልጿል። በአሜሪካ መንግሥት ከጥቁሮች በተለየ መልኩ ሲስተናገዱ እንደቆዩ ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ ኮሎኔል ዳዊትን እና አንድ የቺካጎ ጋዜጣን በመጥቀስ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል።
ይቀጥላል
Filed in: Amharic