>
5:13 pm - Thursday April 19, 9556

“ኦሮሞን አትመስልም!” ስትባል የኖረችው የአባቶቻችን ኢትዮጵያ...!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

“ኦሮሞን አትመስልም!” ስትባል የኖረችው የአባቶቻችን ኢትዮጵያ…!!!

አቻምየለህ ታምሩ

የአንድ አገር የገንዘብ ኖቶች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደተጠበቀ ሆኖ በኖቶቹ ላይ የሚታተሙ ምስሎች የአገርን ታሪክ፣ ብሔራዊ አሻራ፣ ታላላቅ ሰዎች፣ ወዘተ የሚያሳዩና መላ ሕዝቡ ወይም የሕዝቡ ክፍል የሚገለገልባቸውን ምልክቶች የሚወክሉ ናቸው። በመሆኑም የገንዘብ ኖቶች ላይ የሚታተሙ ምስሎች ልክ በቴምብር ላይ እንደሚታተሙ ምስሎች አገር ምን እንደምትመስል ገጽታዋን ለዓለምና ለአገሬው የሚያስተዋውቁ ናቸው።
“ኦሮሞን አትመስልም” የተባለቸው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመኗ ኢትዮጵያ አገልግሎት ካዋለቻቸው አምስት የኢትዮጵያ የገንዘብ ኖቶች መካከል በብዛት ይታተም በነበረው በአሥር ብር የፊት ገጽ ላይ “ኦዳ” የተሰኘውንና የኦሮሞ ሕዝብ ምልክት ተደርጎ የሚቆጠረውን  ዛፍ አትማ ታወጣ ነበር።
ልብ በሉ! አነግና ኦሕዴድ ባዘጋጇቸው ድርጅታዊ አርማዎች መካከል የኦዳ ዛፍ ከማስቀመጣቸው ከብዙ አሥርት ዓመታት በፊት “ኦሮሞን አትመስልም” እየተባለች ስትወገዝ የምትውለው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመኗ ኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ ባዋላችውና በሚሊዮኖች ታትመው በነበረችው የአሥር ብር ኖት የፊት ገጽ ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ምልክት ተደርጎ የሚቆጠረውን የኦዳ ዛፍን ታሳትም መገበያያ ታደርግ ነበር።
ይህንን የኢትዮጵያ የትናንት እውነት “ኦሮሞን አትመስልም!” እየተባለ ሲነገረው ለኖረው፣  የኦነግን  ፕሮፓጋንዳ ለማጣራትና በራሱ አስቦ ምርምሩ ወደሚወስደው ድምዳሜ ለመድረስ ፈቃደኛ ላልሆነው ትውልድ  የኦሮሞ ሕዝብ ምልክት ተደርጎ የሚቆጠረውን የኦዳ ዛፍ በኦነግና ኦሕዴድ አርማዎች መካከል ከመቀመጡ ከዘመናት በፊት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ  ዘመኗ ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች ታሳትማቸው ከነበሩት የገንዘብ ኖቶች መካከል በቁጥር ቀዳሚ በነበረው የአሥር ብር ኖት የፊት ገጽ ላይ ታትሞ እንዲወጣ በማድረግ  የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የኦሮሞን እሴት ለያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና ለመላው ዓለም ያስተዋውቅ እንደነበር ቢነግሩት ሊሰማ አይፈልግም።
የሆነው ሆኖ ከታች የታተመው ታሪካዊ ፎቶ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያሳትማቸው ከነበሩት የብር ኖቶች መካከል በብዛት ይታተም በነበረው አሥር ብር የፊት ገጽ ላይ የታተሙትን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ገጽታና የኦሮሞ ሕዝብ ምልክት ተደርጎ የሚቆጠረውን የኦዳ ዛፍ ምስል የሚያሳይ ነው። ይቺን ኢትዮጵያ ነው ኦሮሞን አትመስልም ሲሉን የኖሩት!
Filed in: Amharic