>

“ ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት/አእምሮ/ ሰይፍና____” (አሰፋ ታረቀኝ)

“ ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት/አእምሮ/ ሰይፍና____”

አሰፋ ታረቀኝ

የህዋህቱ ቁንጮ አቦይ ስብሐት ከጉድጓድ ተስበው ወጥተውና እጃቸው በካቴና ሲታሰር እንዳየሁ የታወሰኝ የመንፈስ ልጃቸው አቶ ስየ አብረሐ መጋቢት 6 ቀን 2020 በትግራይ ቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርቦ የሰጠው ማብራሪያ ነበር፡፡ “  እዚህ አካባቢ የሚቀሰቀስ ጦርነት ድንበሩ አይታወቅም፣ የአድስ አበባ መንግሥት የትግራይን ሕዝብ አታውቅም ሊለው አይችልም፡፡” አቶ ስየ ይቀጥላል፣ “ አብይ ስለፍቅር ስለሰላም ሲናገር ሰምተነዋል፡፡ መደረግ ያለበትን በወቅቱ ባለማድረግ ሥህተት እየሠራ ነው፡፡” ባካበተው የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ሳይሆን በትግራይ ወጣቶችና በትዮጵያ ሕዝብ ደም ላይ ተሸጋግሮ የ UN ባለሥልጣን የሆነው ስየ አብረሐ፣ ህዋህት በትረ መንግሥቱን እንደጨበጠ ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ ጀግናውን የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት “ምን ልብ አለው” ማለቱን አንዘነጋውም፡፡ ከላይ በተጠቀሰውም ቀን ሲጠየቅ፣ “እዚህ አካባቢ የሚቀሰቀስ ጦርነት መቆሚያው አይታወቅም” ሲለን ቢያንስ “አፍሪካን ይለበልባል” ማለቱ ይመስላል፡፡ “የጃሂል መፎከሪያ አታድርገኝ” ይላሉ ወሎየዎች፣ /ጃሂል ማለት ከህይወትም ከትምህርት ቤትም በቂ ዕውቀት ያልገበየ/ ማለት ነው፡፡ አቶ ስዬ ማቆሚያው አይታወቅም ያለው ጦርነት፣ በሁለት ሳምንት ሲጠናቀቅ ቢያንስ በሩቅ ሆኖ አይቶታል፡፡ አቶ ስዬ ምንም እንኳ አምነዋቸው የተኙ ጓደኞቻቸውን እያረዱ በመጣል ተክኖ ያደገ ቢሆንም፣ ወደ ባህር ማዶ ወጣ በማለቱ፣ እሱና ጓደኞቹ እንደ እግዚያብሔር ከሚያመልኳቸው ፈረንጆች ትንሽ ሰብአዊነት ይገበያል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ከድንበር ጥበቃ በተጨማሪ፣ በማንኛውም ማህበራዊ ክንዋኔ ላይ ተሳታፊ በመሆን የትግራይን ህዝብ እያገለገለ ያለን የመከላከያ ሠራዊት እተኛበት ላይ እንደቅጠል ሲያረግፉት፣ በአደባባይ ወጥቶ ያወግዛል ብየ ጠብቄ ነበር፡፡ አቶ ስዬ፣ መንግሥቱም የአድስ አበባ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አሁንም ስለ ፍቅር ስለ ሰላም እየወተውቱ ናቸው፡፡ ህዋህትን ደደቢት በረሀ ወስዶ ያሳደጋት አጋንንት ፍቅርና ሰላም የሚባሉትን ቃሎች አያውቃቸውም ብቻ ሳይሆን ይጠላቸዋል፡፡ በደም ላይ አረማምዶ አራት ኪሎ ያስገባቸውን የደደቢት ልጆቱን በምድር ላይ ያለን የወንጀልና የሐጢአት አይነት ሲያሠራቸው ኖረና አጨራረሳቸውንም አሳዛኝ አደረገው፡፡ በህዋህት ግፍ የተንሳ ለምዝገባ የሚያታክት የብዙ ንጹሐን ደም በከንቱ ፈስሷል፡፡ ፈስሶ ዝም አይልም ወደ እግዚያብሔር ይጮሀል፡፡ ቃየን እንደተጠየቀው፣ እንዲሁ እያንዳንዱ የህዋህት ነፍሰ ገዳይ እግዚያብሔር ይጠይቀዋል፡፡ “ የወንድምህ የደሙ ድምጽ ከምድር ወደኔ ይጮሀል” ዘፍ 4፡10፡፡ እነሆ እንደ ጣዝማ ማር ከገደል ሥር እየተጎተቱ ሲወጡ ለማየት በቃን፡፡ ስዬ ጥያቄውን ሲመልስ፣ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ መንግሥት ማስጠንቀቂያ የሚያስተላልፍ ባለሥልጣን ይመስል ነበር፡፡ ያሳይ የነበረው ትዕቢት የታላቁን የሥነ ጽሁፍ ሰው ከበደ ሚካኤልን ግጥም አስታወሰኝ፡፡

ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት/አእምሮ/

ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት፣

አይገላገሉም እንድህ በቀላሉ፣

እመሬት ላይ ወርደው ሳይንከባለሉ፡፡” 

እግዚያብሔርን መዳፈር ከሰገነት አውርዶ እንደ ፍልፈል ጉድጓድ ውስጥ መደበቅን ያስከትላል፡፡ በየጎጡ የንጹሀንን ደም የምታፈሱ ከነ አቦይ ስብሀት አወዳደቅ ተምራችሁ ብትመለሱ መልካም ይሆንላችኋል፡፡ እግዚአብሔር ሲታግስ ከመጥፎ ሠሪዎች ጋር ተባበረ ማለት እንዳልሆነ መረዳት መልካም ነው፡፡

Filed in: Amharic