የህወሃት መሪዎች ላይ የተወሰደው ርምጃና የመተከሉ ጥቃት…!!!
D.W
ከህዝባዊ ወያነ ትግራይ መስራቾችና አንጋፋ ከፍተኛ አባላት መካከል አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ መከላከያውን በመክዳት ጥቃት እንዲፈጸምበት ያመቻቹ ከተባሉት ወታደራዊ መኮንኖች መያዝን ከሰሙ በኋላ፤ አብዲ ኒዳ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «በህወሃት ባለሥልጣናት ላይ እያነው ያለው ውርደት የሚያሳየው ማንም ሰው ሥልጣኑንም ይሁን ጉልበቱን ተመክቶ ህዝብን መበደል ነገ የሚባል ቀን ደርሶ ዛሬ ይሆንና የእጁን እንደሚያገኝ ትልቅ ትምህርት መውሰድ አለበት። በዳይ በድሎ አይቀርም።» ሲሉ አንቶኒዮ ሙላቱ በበኩላቸው በትዊተር፤ «ለመነሳትም ለመውደቅም ጊዜ አለው።» ነው ያሉት። ዳንኤል ክብረትም በፌስቡክ፤ «ወደላይ የምናየውን ሰው ወደታችን እንደማየት አሳጣኝ ገጠመኝ የለም። ከሁሉም የሚያሳዝነው ግን ከዚህ የሚማር ሰው ከጠፋ ነው።» የሚል አስተያየት አጋርተዋል።
በቀናት ልዩነት እንዲሁ ከፍተኛ የህወሀት ሹማምንት ከሆኑት የአቶ ስዩም መስፍንና የአቶ አባይ ፀሐዬ የመገደል ዜና ሲሰማ ደግሞ ፤ ነአምን ዘለቀ በትዊተር፤ «ኢትዮጵያ እንደ ሶርያና የመን ትተራመሳለች ሲሉ የፎከሩት የህወሃት መሪዎች በእብሪት፣ ፍትህን ርትእን መርገጥ ለውድቀት፣ ለውርደት፣ ለመደምሰስም አበቃቸው። የብሔር ልሂቃንና አንዳንድ የገዥው ፓርቲ መሪ ካድሬዎች ይማሩበት ይሆን?» በማለት ሲጠይቁ፤ ሰሎሞን ግርማ በፌስቡክ፤ «የዘረኝነት መጨረሻ ይሄ ነው። በከበረው እከብራለሁ ብለህ በተዋረደውም መዋረድ እንዳለ ማስተማሪያ ነው።» ብለዋል። ፈቻሳ ከበደ በበኩላቸው፤ «በቀላሉ በሽምግልና የሚያልቅን አለመግባባት እምቢ ብለው ለዚህ ሁሉ ሞትና ቀውስ መድረሳቸው በጣም ያሳዝናል። ቢያንስ ሥልጣን አጥተው በሰላም ይኖሩ ነበር። ነፍስ ይማር።» ነው ያሉት።
ሃብታሙ ሽፈራው በፋንታቸው በዚሁ በፌስቡክ፤ «ኢትዮጵያን ክዶ ዕድሜ ማርዘም አይቻልም። ክብር ለመከላከያ ሠራዊታችን።» ብለዋል። ታደሰ ዲባባ ደግሞ፤ «በባዶ እጅና በባዶ የወረደ አስተሳሰብ የንብ ቀፎ አይገባበትም፤ ምንጊዜም ቢሆን ለውድቀት የሚዳርገን መጥፎ አስተሳሰብ ይዘን ስንጓዝ ለውድቀት ቅርብ ነን።» የሚል አስተያየታቸውን በፌስቡክ አጋርተዋል። ወልድ ዋህድ ይመኑም እንዲሁ በፌስቡክ፤ «ሰይፍ የመዘዘ ሰይፍ ይመዘዝበታል፤ የክፉ ሰው መጨረሻ ሞትና ውድቀት ነው። ትዕቢት ለዲያብሎስም አልጠቀመም፤ የኢትዮጵያ አምላክ ገና,,,» በማለት ኢትዮጵያን የሚነኩ ያሏቸውን አውግዘዋል። ሊዲያ ሃበሻ ደግሞ፤ «ኢትዮጵያን በክፉ ያለመ ምንም ጊዜው ቢዘገገይም ከባድ ዋጋ ይከፍላል።» ሲሉ ጀሚላ ያሲንም እንዲሁ፤ «አልሀም ዱሊላህ ኢትዮጵያን የነጃ መጨረሻው ይሄ ነው።» ብለዋል በፌስቡክ። መስፍን ተስፋዬ ደግሞ እንዲህ ነው የሚሉት፤ «እነሱ እኮ የሞቱት ኢትዮጵያን የነኩ ዕለት ነው፤ ስለዚህ አሁን እኛን የጨነቀን ሰበር ዜና እየተባለ ከሚለቀቀው ዜና በስተጀርባ ማቆምያ ያጣው በማንነታቸው የሚጨፈጨፉት ወገኖቻችንና በተረኝነት ስሜት የሚሠራው ድራማ ነው። ይህንን ማስቆም ካልተቻለ ቀጣይ ወደየት ልናመራ እንደምንችል ሁሉም ከወዲሁ እራሱን ይጠይቅ።»
የሰዎች ሞት ሊያስደስተን አይገባም ለሚሉ አስተያየቶች ግሩም በትዊተር፤ «አመጸኛን ለሕግ ማቅረብ እምቢ ካለም ርምጃ መውሰድ የመንግሥት ዋና ኃላፊነት ነው። እንደውም የቸገረን የመንግሥት በሚፈለገው መጠን ርምጃ አለመውሰድ ነው፤ (ለምሳሌ መተከል፤ ኮንሶ,,,) ደስታው ግን እምብዛም ያለ አይመስለኝም።»
« ጁንታውን ተደመሰሰ ፣ ጁንታው ተማረከ ” ከሚለው ዜና ይልቅ “ታረድን ተገደልን ” የሚለው የተገፊ ወገን ልብ ሰባሪ ጩኸት ጎልቶ ይሰማል ፤ መንግሥት “አለሁ ” ካለ የዘር ፍጅቱን ለማስቆም የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ ይገባል» ይላል ነብዩ ሲራክ በፌስቡክ ያጋሩት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቀጠለውን የንፁሐን ግድያ አስመልክቶ አስተያየት። ወርቂ ጫኔ ሃሳባቸውን ይጋራሉ፤ «አጀንዳ ማስቀየሪያ አይጠፋም የሚገርም ነው። ከሆነው ይልቅ ሊሆን የታሰበውን ተረባርቦ ማክሸፍ እየተቻለ እንቆቅልሽ ነው የሆነብን የመተከል ጉዳይ።»
ቲ ላቪ ላቪ በበኩላቸው፤ «ምንም ጥያቄ የለውም አረ ጎበዝ ወዴት ወዴት እየሄድን ነው? መንግሥት ይህንን ነገር የማያዳግም ርምጃ በመውሰድ ንፁሐንን መታደግ አለበት። አለበለዚያ በየቤታችን እያንኳኩ እስኪመጡ ነው እንዴ የምንጠብቀው?» በማለት ጠይቀዋል። ዘቢባ አህመድ ሃሳባቸው ይለያል፣፤ « እኔ የማዝነው በግፍ ለተገደሉት ሳይሆን ለገድይ አስገዳዮቹ ነው። አቤቱ ጌታዬ እንዴት ይሆን አሟሟታቸው? በቁም ለሞቱት። ያአላህ አንተ ፍረድ! የሰው ልጅ አይደለም የአምላክን ቁጣ ፍሩ ከባድ ነው። እውነት የእነዚህን ንፁሐን ደም እንዲሁ አያስቀርም።»
አስታጥቄ ደግሞ በትዊተር፤ «የሰው ልጅ ሕይወት እረከሰ ሞት ተለመደ፤ እንደ ዶላር ዋጋ ዛሬ ስንት ገባ (ሞተ) ብንል በቁጥሩ ማነስ እንፅናናለን። ሲጨምር ለጊዜው እንንጫጫለን።። ሞትና መፈናቀሉ ችግርና ሀዘኑ አዲስ አበባ እስካልገባ ድረስ ያን ያህል ግድ አይሰጠንም። ኢትዮጵያ፤ ኮንሶ መተከል!» ሲሉ፤ ሜድ ኢን ኢትዮጵያ ደግሞ፤ «መተከል እግዚአብሔር ይድረስልሽ! ግፍን ምስኪን ሕዝብ ላይ በእንዲህ አይነት መልኩ የትም አልታየም፤ ቃላት ያጥራሉ፤ ብቻ!» ነው ያሉት። ዴራን ማን በፌስቡክ፤ «ህወሃትን የሚያህል እስከ አፍንጫው የታጠቀን ኃይል በአንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሕግ ማስከበር ተብሎ ያህን ያህል ሠራዊት ተደምስሶ ከጥቅም ውጭ ከተደረገ በሰው ቁጥር እዚህ ግባ የማይባለው ባህላዊ የጦር መሣሪያ ይዞ የሚንቀሳቀሰውን ቡድን መደምሰስ ለምን እንዳልተፈለገ ግልፅ አይደለም።» ሲሉ፤ «በጣም ያሳዝናል እባካችሁ ተረዱ በቤንሻንጉል ጉዳይ፤ በውጭ በሱዳን በግብፅ ድጋፍ ቅስቀሳ የሚደገፍ ነው። ለህዝቡ ግንዛቤ ስጡ፤ ሴቶችና ሕጻናት ደካማዎቹን ማውጣትና ወንዶች ታጥቀው አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ነው። አሁን የሚፈለገው ግድቡ ባለበት አካባቢ ባጠቃላይ ጦርነት ማንሳት ነው። የግድቡ ነገር አንድ ስምምነት ላይ ካልደረሰ ችግሩ አይቆምም። ለህዝቡ ንቃት ስጡ።» ሲሉ መክረዋል።
ጥሩ ሰው ገረሱ የተባሉት የትዊተር ተጠቃሚ በቤንሻንጉል ከሚታየው ጋር በማገናኘት መንግሥትን ለሚተቹ ወገኖች ምላሽ የመሰለ መልእክት ነው ያካፈሉት፤ «ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ችግር ህወሀትና ጎሳን መሠረት ያደረገው ፌደራሊዝም ተጠያቂ ለመሆኑ ጠንካራ እምነት አለኝ። ዐቢይ አህመድ አሊ ከመተከል ወይም ከሱዳን ጉዳይ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም።» ይላሉ።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ሃገራት ዜጎችም እንደልብ አስተያየታቸውን ሲሰጡ መመልከት በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ ተጠናክሮ ይታያል፤ ከእነዚህ መካከል አንዱ ቶቢያስ ሃግማን የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፤ «የኢትዮጵያ ፖለቲካ የትኛው ጎሳ የተሻለ ቂም ቋጥሯል በሚለው ላይ ፉክክር የገጠመ እየመሰለ ነው። ቅሬታዎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይችላል። ለዚህም ነው ፖለቲካው የሚያስፈልገው። ሆኖም ግን ሌሎችም በኢፍትሃዊነት እየተንገላቱ መሆኑን መረዳትን ይጠይቃል። ይህም በጣም በጣም ከባድ ነው።» ይላሉ።
እስኪያልፍ ያለፋል በፌስቡክ፤ «በትክክል ሀገርን ለማዳን ወገንን ለመታደግ ይህን አይነቱን ዘግናኝ እና ሰቅጣጭ የሞት ሰቆቃና እልቂት እንዳይቀጥል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉና እንደ ሰው እሚያስብ ሰው የሆነ ሁሉ ቆም ብሎ በማሰeb መፍትሄ ማፍለቅ ግድ ይለናል።» ሲሉ መክረዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ