>

" የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ፈጽሞ ከህወሀት ጋር አይቀበርም...!!! (ኦፌኮ)

” የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ፈጽሞ ከህወሀት ጋር አይቀበርም…!!!

ኦፌኮ

  “በርካታ አባሎች ታስረውብኛል፤ ፅ/ቤቶችም ተዘግተውብኛል” የሚል ተደጋጋሚ አቤቱታ የሚያሰማው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፤ በዘንድሮ ምርጫ በመሳተፍና ባለመሳተፍ መሃል እየዋለለ ይገኛል፡
በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ም/ሊቀ መናብርቱ አቶ ሙላቱ ገመቹና አቶ ገብሩ ገ/ማሪያም እንዲሁም ዋና ፀሃፊው አቶ ጥሩነህ ገምታ፣ ባለፈው ረቡዕ ለተወሰኑ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ መግለጫ ላይ የተገኘው ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ በተለይ ከአዲስ አድማስ የቀረበላቸውን ጥያቄና የአመራሮቹን ምላሽ እንዲሁም የመግለጫውን ፍሬ ሃሳብ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ተ/ምክትል ሊቀ መንበሩ አቶ በቀለ ገርባና አባሉ ጃዋር መሃመድን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ አመራርና አባላቱ እንደታሰሩበት የገለጸው ኦፌኮ፤ በዚህ ሁኔታ በዘንድሮ  ምርጫ የመሳተፉ ነገርም አጠራጣሪ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡
“ለፖለቲካ ችግሮቻችንም ሆነ ለነፃ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱ ወሳኝ ነው” በሚል ረቡዕ እለት መግለጫ የሰጠው ኦፌኮ፤ በአሁኑ ወቅት ስፍር ቁጥር የሌላቸው አመራሮችና አባላቱ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ በልዩ ሃይል ካምፖች፣ በድርጅት ፅ/ቤቶች፣ በመደበኛ እስር ቤቶችና በትምህርት ቤቶች ጭምር ታስረው እየተሰቃዩ እንደሚገኙ በመጠቆም፤ ጉዳዩን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲከታተሉት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ፅ/ቤቶቹም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንደተዘጉበት ያስታወቀው ኦፌኮ፤ በእነዚህ ተደራራቢ ሁኔታዎች የተነሳ በቀጣይ ሃገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ እንደሚቸገር ገልጿል። አፋጣኝ ፖለቲካዊ ማሻሻዎች ካልተደረገ ሃገሪቱንም ሆነ ክልሉን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት የፖለቲካ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችልም ፓርቲው አሳስቧል፡፡
ኦፌኮ በዚሁ መግለጫው፣ የብሔር ፌደራሊዝምና የብሔር የፖለቲካ አደረጃጀት ከህወሃት ጋር መቀበር አለበት የሚሉ ድምጾች መበራከታቸውን በመጠቆም፤ አሁን ያለው የብሔር ፌደራሊዝም ሆነ የብሔር ጥያቄ ህወሓት የፈጠረው ሳይሆን ከህወሃት በፊትም የነበረ ጥያቄ ነው፤ ከህወሃት ጋር አብሮ የሚቀበር አይሆንም፣ ኦፌኮም ሆነ ሌሎች ለዚሁ በፅናት ይታገላሉ ብሏል፡፡ በእለቱ ከአመራሮቹ ጋር ከተደረጉ ጥያቄና መልሶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

አባሎቻችሁ መታሰራቸውንና ፅ/ቤቶቻችሁ መዘጋታቸውን በምክንያትነት ጠቅሳችሁ፤ በምርጫው ለመሳተፍ ይቸግረናል ብላችኋል፡፡ ሁኔታዎች በዚሁ ከቀጠሉ የመጨረሻ ውሳኔያችሁ ምንድን ነው የሚሆነው?
እኛ በመሰረቱ ሰላማዊና ቅቡልነት ያለው ምርጫ ሊደረግ ይችላል የምንለው ሃገሩ ሰላም ሲሆን ነው፡፡ ሰው የተረጋጋ ሲሆን ነው ምርጫ ማድረግ የሚቻለው፡፡ ለመመረጥ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩ ማቅረብ አለባቸው፡፡ እጩዎች ታሰሩብን ነው እያልን ያለነው፡፡ ታዲያ ማንን ነው የምናቀርበው? እጩ ማቅረብ፣ ቢሮ ውስጥ ስራ መስራት ባልቻልንበት ሁኔታ እንዴት ነው የምንሳተፈው? እኛ እኮ እንደውም በመግለጫችን የህዝብን ስሜት ላለመንካት ከሚፈፀምብን በደል አሳንሰን ነው ያቀረብነው፡፡ እየደረሰብን ያለው መዋከብና በደል ከሚነገረው በላይ ነው፡፡ ታዲያ በዚሁ ሁኔታ ውስጥ ምን አይነት ምርጫ ነው የምናካሂደው? ከትናንትናው መማር አለብን፡፡ ትናንትና በ2007 በሃይልም በወከባም ምርጫ ተደረገ፤ ነገር ግን ህዝቡ ያላመነበት ስለነበር ያ ሁሉ  ተቃውሞ ተፈጠረ፡፡ ዛሬስ ያ የማይደረግበት ምን ሁኔታ አለ? እኛ አሁንም ሁኔታዎች ካልተስተካከሉ ምርጫ ውስጥ ለመግባት እንቸገራለን፡፡
ይህን ችግር ለተለያዩ የመንግስት አካላት ስታሳውቁ መቆየታችሁን ገልፃችኋል፡፡ የተሰጣችሁ ምላሽ ምንድን ነው?
እስከ አሁን ምንም ምላሽ አልተሰጠንም። አሁንም አባሎቻችን እንደታሰሩ፣ ጽ/ቤቶቻችንም እንደተዘጉ ነው ያሉት፡፡ ምርጫ ቦርድም ነገሩን  በትኩረት አላየውም፡፡
ምን ያህል ናቸው የታሰሩባችሁ? በግልጽ ብታስቀምጡት…..
ቁጥር መግለጽ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም፤ ነገር ግን በተለያዩ መንገዶች ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ ጥያቄያችሁ ቁጥር ከሆነ ለምሳሌ ከ200 በላይ የኦፌኮ አመራሮችና አባላት በጅማ ዞን ታስረዋል፡፡ በምስራቅ ሸዋና አርሲ ዞኖች ላይ ብቻ እንኳ ከ700 በላይ አመራርና አባላት ታስረው ይገኛሉ። ሌሎች ዞኖች ላይ ደግሞ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው አባላትና አመራሮች ናቸው  የታሰሩብን፡፡ አርሲ ገደብ አሳሳ የሚባል ቦታ ላይ እስር ቤቱ አንሷቸው  አዲስ እስር ቤት በቆርቆሮ እስከ መሰራት ተደርሷል፡፡ የኛ አባላት ለምን ታሰሩ አይደለም ጥያቄያችን። ለምን አፋጣኝ ፍትህ አያገኙም? ለምን ንፁሃን ሳይጣራ ይታሰራሉ ነው ጥያቄያችን። ፍ/ቤት ነፃ ነው ብሎ የፈታቸውን ሰዎች ሳይቀር ፖሊስ መልሶ አስሯቸዋል፡፡ ይሄ በሀረርጌ፣ ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ተፈፅሟል፡፡
የምስራቅ ወለጋ ዞን የኦፌኮ ተጠሪ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አራት ጊዜ ነው የታሰረው፡፡ የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተባባሪ ከታሰረ አንድ ዓመት አልፎታል፡፡ ግን ምንም የተጨበጠ ክስ አልተሰማም፡፡ ይሄን ሁሉ አቤቱታ ለምርጫ ቦርድ ብናመለክትም፣ ይሄ ነው የሚባል ውጤት አላገኘንም፡፡
እናንተ ለምታቀርቡት አቤቱታ መፍትሄ ብላችሁ የምትጠቁመት ምንድን ነው?
አንዳንዶቹ የታሰሩት አባሎቻችን ይፈቱልን፤ ጽ/ቤቶቻችን ይከፈቱልን። በተደጋጋሚ በየመግለጫዎቻችን ስናስገነዝብ እንደቆየነው፣ የፖለቲካ ሃይሎች በሙሉ ለብሄራዊ መግባባት ውይይት ይቀመጡ፡፡ የዚህ ሃገር ዜጎች የሆኑ ሁሉ የሚሳተፉበት ብሄራዊ መግባባት ቢደረግ፣ ለሃገራችን ፖለቲካዊ ችግር መፍትሄ ነው ብለን  እናምናለን፡፡ በተናጥል ኦፌኮ የተለየ ችግር አለበት ብለንም አናምንም፡፡ እኛ የምንናገረው ችግር ሌሎችም ጋ አለ፡፡ ለዚህ መፍትሄው ብሄራዊ መግባባት ነው፡፡ አንድ ነገር እዚህ  ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ በቀለ ገርባ የኢትዮጵያ ምርጫ በመጣ ቁጥር ወደ እስር ቤት ይወረወራል፣ደጀኔ ጣፋም በተመሳሳይ፡፡ ምርጫ ላይ ተሳትፈው አያውቁም፡፡ ሌሎች አለማቀፋዊ ተሰሚነት ያላቸው አባሎች እነ ጃዋር ሲራጅ መሃመድ ያልተገባ ነገር ተለጥፎባቸው ይታሰራሉ፤ ፍ/ቤት ይንከራተታሉ፡፡ ይሄ ነው እኛን የገጠመን ችግር፡፡ ይሄ ለነገ አብሮነታችን አይበጅም፡፡ ቁጭ ብለን መነጋገር ነው ያለብን፡፡ መገናኛ ብዙሃን የኛ ድምጽ ለመሆን እየፈለጉ አይደለም፡፡ እናንተና ጥቂቶች ናቸው የኛን ጉዳይ የሚከታተሉት። ይሄ ለምን ሆነ? እኛ ወንጀል የሰሩ ሰዎች አይጠየቁም አላልንም፡፡ ነገር ግን በህግ የበላይነት ስም ፖለቲካዊ እርምጃዎችን መውሰድ ለሃገራችን አይበጅም፡፡ እንደ ትናንቱ ዛሬም ቀዳዳ ይከፍታል፤ መልሶ አዙሪት ውስጥ ይከተናል፡፡ የውጭ ሃይሎች በውስጥ ጉዳያችን እንዲገቡ በር ይከፍታል። የሃገራችንን የአንድነት አካሄድ በእጅጉ ያዛባል፡፡ ለዚህ መፍትሄው ሁሉም እኩል የሚሳተፉበት የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ነው፡፡
በመግለጫችሁ “የብሔር ፖለቲካ ህወሓት የጀመረው አይደለም፤ ከህወሓት ጋር አይቀበርም” ብላችኋል፡፡ የብሔር ፖለቲካ አደጋ ውስጥ ወድቋል የሚል ስጋት አላችሁ ማለት ነው?
የብሔር ፖለቲካ በእኛ ሀገር ብቻ  አይደለም ያለው፡፡ ፈረንሳይም፣ አሜሪካም ሌላውም ጋ አለ፡፡  እኛ ጋ ብቻ ያለ ልዩ ነገር አድርጎ ማየት ተገቢ አይደለም። አሜሪካን ሃገር “ብላክ ላይቭስ ማተር” እየተባለ ሰልፍ ይወጣል፤ ሰዎች በጥቁርነታቸው ይደራጃሉ። ምን አለበት ታዲያ “አማራ ላይፍ ማተርስ”፣ ”ኦሮሞ ላይፍ ማተርስ”፣ ”ትግሬ ላይፍ ማተርስ” ብለን ትግል ብናደርግ? ይሄ ምን ችግር አለው? መንግስት ደግሞ ለዜጎቹ ሃላፊነትና ተጠያቂነት አለበት፡፡ አሁን ህወሓት ሲፈርስ የብሔር ፖለቲካና ፌደራሊዝሙ የመጨረሻ ግብአተ መሬቱ እንደተፈጸመ ተደርጎ ከተለያዩ ወገኖች የሚናፈሰውና የሚመታው ከበሮ የትም አያደርስም፡፡ የኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ከወያኔ ጋር አልመጣም። ይሄን አለማወቅ በግልጽ ቋንቋ የእውቀት ድህነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ከወያኔ ቀድሞ በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የነበረ ነው። ከወያኔ ጋር የመጣ አይደለም፤ ከወያኔ ጋርም የሚሄድ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ ይሄን የከበሮ ድለቃም በምንም መስፈርት አይቀበልም። ነገሩን ከወያኔ ጋር ማያያዝም የእውቀት ደካማነት ነው። ከብርሃነ መስቀል ረዳ፣ ከዋለልኝ መኮንን፣ ከኢብሳ ጉተማ በላይ ለብሔር ብሔረሰቦች የታገለ አለ? እነሱኮ ናቸው ብሔር ብሄረሰቦች ብለው የታገሉት፡፡ ወያኔ ያኔ የት ነበረች? በዚህ የእውቀት ድህነት ውስጥ ሆነው የሚለፍፉ ሃገርን ለመበተን ነው እያሰፈሰፉ ያሉት ናቸው። ይህ የትም አያደርስም። ይልቅስ ጠቃሚው መነጋገር መወያየት ነው፡፡
እኛ ወድቀን እየተነሳንም ቢሆን ትግሉን እዚህ አድርሰናል። ከ2006 ጀምሮ ብቻ የበርካታ ኦሮሞ ወጣቶች ደም ለዚህ አላማ ፈሷል። በእነዚህ የኦሮሞ ልጆች ደም የሚቀልድ የለም። ፈፅሞ አንቀልድም። ሃሳቡ የቆመው በደም ላይ ነው። በቀልድ አልቆመም። ስለዚህ ይሄ በየሚዲያው የሚነዛው ጥላቻ አዘል ፕሮፓጋንዳ አካሄዱ አደገኛ ነው። ለሃገሪቱ አንድነት ፈጽሞ አይበጅም። ወያኔ ደርግን አሸነፈ እንጂ የሃሳቡ ምንጭና ባለቤት አይደለም። ይህን ታሪኩን መመርመር፣ የነበሩበትን ሰዎች ጠይቆ መገንዘብ ይቻላል። እነዚህ ሰዎች ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል። ይልቁንስ በጋራ የምንቆምባትን ኢትዮጵያ ብንገንባ ነው የሚጠቅመው።
ከመድረክ ጋር ያላችሁ ግንኙነት እንዴት ነው?
አሁንም ጥሩ ግንኙነት አለን። በአንድ ፓርቲ ምክንያት ትንሽ መንገራገጭ ተፈጥሮ ነበር፤ ነገር ግን አሁን እየተነጋገርንበት ነው፤ ችግሩን ፈትተን በጋራ መጓዛችን አይቀርም። የጎላ ችግር የለብንም።

Filed in: Amharic