>

ምርጫ ቦርድ ህወሓትን፣ ዓዴፓን፣ባይቶናን እና  ሣወትን ህጋዊ ሰውነት ሰረዘ...!!! (ነጋሪት)

ምርጫ ቦርድ ህወሓትን፣ ዓዴፓን፣ባይቶናን እና  ሣወትን ህጋዊ ሰውነት ሰረዘ…!!!

ነጋሪት 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 98/1//4/ መሠረት የህወሓትን ህጋዊ ሰውነት ሰርዞታል። በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 99 መሠረት የፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንደማይችሉም ውሳኔ አስተላልፏል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በፓርቲው እና በፓርቲው አመራሮች ላይ በሚያደርገው ምርመራ የሚገኙ በህወሐት ሥም የተመዘገቡ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ንብረቶችን በተመለከተ ያገኘውን ዝርዝር መረጃ እንዲልክ ቦርዱ ጥያቄ አቅርቧል።
የፓርቲው ንብረት በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 99/2/ መሠረት ንብረቱ ተጣርቶ ዕዳ ካለበት ለዕዳው መሸፈኛ እንዲውል፤ ይሁንና እዳውን ሸፍኖ የሚተርፍ ንብረት ከተገኘ ቀሪው ገንዘብና ንብረት በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 99/3/ መሠረት ለሥነ ዜጋና መራጮች ትምህርት እንዲውል ቦርዱ ወስኗል፡፡ ቦርዱ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሶስት ፓርቲዎችን ላይ በቦርዱ የትግራይ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በቀረቡ መረጃዎች እና ሌሎች ጥቆማዎች መሰረት ተጨማሪ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ስለእንቅስቃሴያቸው ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቷል። ትእዛዝ የተሰጣቸው ፓርቲዎችም የሚከተሉት ናቸው።
ሀ. “ዓሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /ዓዴፓ/”- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሂደት ላይ እያሉ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በተካሄደ ህገወጥ ምርጫ ስለመሳተፋቸው
ለ. “ብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ /ባይቶና/” – በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሂደት ላይ እያሉ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በተካሄደ ህገወጥ ምርጫ ስለመሳተፋቸው እንዲሁም የፓርቲው አመራሮች በአመጻ ተግባር በመሳተፋቸው ለቦርዱ መረጃ በመድረሱ
ሐ. “ሳልሳይ ወያነ ትግራይ /ሣወት/”- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሂደት ላይ እያሉ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በተካሄደ ህገወጥ ምርጫ ስለመሳተፋቸው እንዲሁም የፓርቲው አመራሮች በአመጻ ተግባር በመሳተፋቸው በቦርዱ መረጃ በመድረሱ
Filed in: Amharic