“አልሃምዱሊላሂ ታቦታችን ገባ!”
አቲካ አህመድ አሊ
በዚህ የስልጡኖቹ ወሎዬዎች አባባል ላይ ሁሌ ሃሳቤን አሰፍራለሁ እያልኩ አልሞላልኝ ሲል ትቼው ነበር።
በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ ታቦት ይወጣል። ከጥምቀቱ በኋላም ወደየማደሪያው ይመለሳል። ታቦቱ ወደ ጥምቀቱ ቦታ ሲጓዝም ሆነ ወደ ማደሪያዉ ሲመለስ በበርካታ ምእመናን ታጅቦ ነው። ታቦቱ በምእመናኑ ታጅቦ በሚጓዝባቸዉ መንገዶች በሞላም በዓል ይሆናል። ይህ ክስተት ለኢትዮጵያዊያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ወንድሞቻችን የእምነታቸው አንድ አካል ነዉ። የታቦቱ በጥምቀቱ ቦታ በሰላም መድረስ እና ወደ ማደሪያዉ በሰላም መመለስ ለኦርቶዶክስ ክርስቲያን ምእመናን ትርጉም ያለው እና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግበት ነዉ። ታቦቱ በሰላም መመለሱ የህዝበ ክርስቲያኑ ሰላሙ ነዉ። የእምነቱ አንድ መገለጫ የሆነዉ ታቦቱ በመንገዱ ላይ እክል ከገጠመዉ ምእመኑም ሰላሙን ያጣል።
ታቦት ለአንድ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም የእምነቱ አካል ባይሆንም ቅሉ፣ የአገሪቷ ግማሽ አካል የሆነዉ ህዝብ ሰላሙን ካጣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሰላም ሊኖረዉ እንዴት ይቻላል!? እኔ ሙስሊም ብሆንም መላዉ ኦርቶዶክስ ህዝበ ክርስቲያን፣ ጎረቤቶቼ፣ ጓደኛቼ፣ ዘመዶቼ ሌሎችም ሰላማቸው ተናግቶ፣ እያለቀሱ፣ እያዘኑ፣ ሙሾ እያወረዱ እንዴት ልደሰት፣ ሰላሜ ሊጠበቅ ይቻለኛል!?
ምንም እንኳን ሙስሊም ብሆንና የማመልከዉ በመስጅዶች ውስጥ ቢሆንም እንደ ዜጋ ግን አብያተ ክርስቲያናቱም ቸርቾቹም የኔም ናቸዉ። መስጂዶቹ ደግሞ ለአንድ ክርስቲያን የእርሱም ጭምር ናቸዉ። እናማ ቀደምት አያቶቻችን “አልሃምዱሊላሂ ታቦታችን ገባ” ሲሉ በጭቆናም ሆነ በበታችነት፣ በአላዋቂነት፣ ለራስ እምነት ባለመቆርቆር ወይም በተገዢነት አልነበረም! በፍቅር፣ በየኔነት፣ በመተሳሰብ፣ በጋራ ጥቅም፣ በመከባበር እና በወንድማማችነት ስሜት እንጂ!
በሰላም ወጥታችሁ ግቡ!መልካም የከተራ እና የጥምቀት በዓል ወዳጆች!
የዘገሊላ ‘ለት የዘገሊላ ‘ለት ነይልኝ በኔ ሞት!