>

የሙዚቃው ንጉስ ጥላሁን ገሰሰ እና ኮሎኔል መንግስቱኃይለማሪያምን ያገናኘች አጋጣሚ‼ (እንዳለጌታ ከበደ)

  1. የሙዚቃው ንጉስ ጥላሁን ገሰሰ እና ኮሎኔል መንግስቱኃይለማሪያምን ያገናኘች አጋጣሚ
እንዳለጌታ ከበደ

ወ/ሮ ሮማን የረሳችውን መድኃኒት ለማምጣት ወደ ክፍላችን ስትገባ ስልኩ ጠራ አነሳችው።”ጤና ይስጥልኝ”አለችው የማታውቀው ሰው ነው ደክሟትና ሰልችቷት ስለነበር መልዕክት ተቀብላ ወደ እኔ ለመምጣት ተጣድፋ ነበር።
*
“ማን ልበል?!” ስትል፣
“ከጓድ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃ/ማርያም ቢሮ ነው የተደወለው ጥላሁን ገሠሠን ማግኘት ፈልጌ ነው!”አለ
“ከሊቀመንበር?”አለች፣ግራ ገብቷትና ተደናግጣ።
“አዎ! ከሊቀመንበር መንግስቱ ኃ/ማርያም! እኔ ረዳታቸው ነኝ።ጥላሁንን ማግኘት ፈልገው ነበር..”
“አሁን ይኸው አመጣዋለሁ ጌታዬ . . .ምሳ ለመብላት ወደ ሬስቶራንት ሄዶ ነበር. . . አሁኑኑ . . . ከአምስት ደቂቃ በኋላ መልሰው ይደውሉ!”
በፍጥነት ሊፍት ውስጥ ገብታ ወረደችና እየንተንደረደረች መጥታ፣”ስልክ!…ስልክ!…ስልክ!…”አለችኝ።
ደግሞ ልታመጣው የነበረውን መድኃኒት አልያዘችም።በዊልቸር እየገፋች ወደ ፎቅ ሰናመራ ነው፣የሰማችውን ነገር የነገረችኝ።እኔንም ገርሞኛል።እንዴት?ሊቀመንበር መንግስቱ?! አንድ ቀልድ ያማረው ሰው በስሜታችን ሊጫወት ያሴረ መሰለኝ።
**
ሊቀመንበር መንግስቱ እኔ ስዘፍን ሰምተውኝ ያውቃሉ።እኔና ጓደኞቼ አገር ነክ የሆኑ ሥራዎቻችንን ይዘን ለሠራዊቱ አባላት በምንጫወትበት ጊዜ ታንክ ላይ ተቀምጠው ያዳምጡን እንደነበር አስታውሳለሁ።በአንድ ወቅት ከሱዳኑ ፕሬዚዳንት ጋር ሆኜ ስቴጅ ላይ ፎቶ መነሳቴን አልዘነጋም።ይህንን ዕድል ግን ከሊቀመንበር መንግስቱ አግኝቼው አላውቅም።ከመንግስቱ ጋር የተነሳሁትን ፎቶ አይቸው አውቃለሁ ያለኝ ሰው አለ።እኔ ግን መቼ፣የትና በምን ሁኔታ አግኝቻቸው ፎቶ እንደተነሳሁ አላስታውስም።
***
የሆነው ሆነና ወደ ክፍላችን ስንገባና ስልኩ ሲጮህ እኩል ሆነ።ወ/ሮ ሮማን አነሳችው፣”ሃሎ? ማን ልበል?!”
ረዳታቸው መሆኑን ነገራት።ስልኩን አቀበለችኝ።
“ሊቀመንበር ነኝ!” አለኝ አንድ ድምጽ።
***
“ሊቀመንበር ማን ?” አልኩ ኮስተር ብዬ።
“ስንት ሊቀመንበር አለህ?” አለኝ ሰውየው እየሳቀ፣ “ያው ጓድ መንግስቱ ኃ/ማርያም ናቸው! ከሀራሬ፣ዚምባብዌ!”
“እሺ ጌታዬ!”አልኩ።
እሳቸው ቀረቡ።
“ጓድ ጥላሁን! እግዚአብሔር ይማርህ! የእግርህን መቆረጥ ሰማንና በጣም አዘንን።ምን ይደረግ።መጥተን እንዳንጠይቅህ ያለንበት ሁኔታ ታውቃለህ. . .”
**
“አውቃለሁ ጌታዬ! ይህም ይበቃኛል!”አልኳቸው።
**
“አይዞህ! ምን ከእንግዲ ወዲህ እንደነ ኃይሌ ገብረስላሴና ቀነኒሣ በቀለ ማራቶን አትሮጥበት! አይዞህ! ለእናት አገርህ ብዙ ሠርተሃል።ከእንግዲ ወዲህ የሚቀርህ ነገር ስለሌለ እግሬን አጣሁ ብለህ ብዙ አትጨነቅ! አይዞህ በርታ!” አሉና ተሰናበቱኝ።
በወቅቱ:- እጅግ የልብ ወዳጆቼ አርቲስት አለም ጸሀይ ወዳጆ፣ አርቲስት ታማኝ በየነ እና ሌሎችም ወዳጆቼ ከአሜሪካ ሊጠይቁኝ መጥተው በስፍራው ነበሩ።
…………………………………………………………………………
ምንጭ፦  ያልተቀበልናቸው፣እፍታዘር አታሚዎች፣ነሐሴ 2009
Filed in: Amharic