“የዋልድባና የህወሃት ፍጥጫ…”
መስከረም አበራ
*…ወያኔ እንዲህ አሳፋሪ ሞት እስክትሞት ድረስ ያልተተናኮለችው ፍጡር አልነበረም። ከገዳማዊ እስከ ፖለቲከኛ ሁሉንም ነካክታ ቀብሯላይ የሚቆም ወዳጅ እንዳይኖር ከድርጋ ነው ወደ ሞቷ ያዘገመችው!!!
ሞቷን የጀመረችው የዋልድባ መነኮሳትን እንደ ወንበዴ እጃቸውን በሰንሰለት ካላሰርኩ፣የምንኩስና ቀሚሳቸውን አውልቄ የእስረኛ ቱታ ካላለበስኩ፣የገዳሙን መሬት አርሼ ሸንኮራ አገዳ ካላበቀልኩ ያለች ጊዜ ነው። የማያድግ ጥጃ ከበሬ በፊት ይበላል አይነት ነገር!
የአምላካቸውን ጉልበት ከወያኔን ብርታት ጋር ለውድድር እንደማይቀርብ ያወቁት የዋልድባ መነኮሳትም እስከመጨረሻው ተፋለሙ። ከነዚህ በፈጣሪያቸው ከተወራረዱ አባቶች አንዱ አባ ገብረኢየሱስ ኪዳነማርያም ነበሩ። እኒህ አባት ታስረው ብዙ ተንገላተዋል። በዚህ እንግልት መሃል ደግሞ “የዋልድባና የህወሃት ፍጥጫ”በሚል አርዕስት መፅሃፍ ፅፈው አስነብበውናል።
በበኩሌ አንድን ታሪካዊ እውነት ሳያዛቡ ለታሪክ ፅፎ ማቆየትን የመሰለ ለመጭው ትውልድ ውለታ የማስቀመጥ ስራ የለም።
አባ ኪዳነማርያም ትናንት በጥምቀት በዓል ጎንደር ላይ ለዚሁ አበርክቶታቸው መሸለማቸውን ሳይ በጣም ነው የተደሰትኩት።ሆኖም ከዚህ በላይ ሰፋ ያለ ሃገራዊ መድረክ ተዘጋጅቶ ቢሸለሙ ይመስለኛል ተጋድሏቸውን የሚመጥነው የሽልማት።
በሃገሪቱ የሃይማኖት አባቱን ከካድሬው መለየት ባስቸገረበት ዘመን ወያኔን የተፋለሙ የአቡነ ጴጥሮስ የመንፈስ ልጅ ናቸው አባ ኪዳነ ማሪያም።በተለይ ቪኦኤ ላይ ቀርበው እንቅጭ እንቅጯን ሲናገሩ ትምክህታቸው በአምላካቸው ብቻ እንደሆነ ድፍረታቸው ያስታውቅ ነበር።
የሆነው ሆኖ በስተመጨረሻው እውነት አሸንፋ ዛሬ እስረኛው አባት ተሸላሚ አሳሪው ወያኔ ደግሞ እስረኛ መሆኑ አስገራሚ ነው። አባ ኪዳነ ማርያም እንኳን ደስ አለዎት እያልኩ እናንተ ወዳጆቼ ደግሞ ይህችን አባ የፃፏትን መፅሃፍ እንድታነቡ ልጋብዝ፣መፅሃፏን አምስት ኪሎ ፍሬው የመፅሃፍት መደብር ነው እኔ ያገኘኋት እዛ ማግኘት ትችላላችሁ።