>

ሁለት ሀገር እና ሁለት አይነት ዜጋ በልብ ይዞ የመዞር እዳ....!!! ሸንቁጥ አየለ

ሁለት ሀገር እና ሁለት አይነት ዜጋ በልብ ይዞ የመዞር እዳ….!!!
ሸንቁጥ አየለ

• የአቢይ መንግስት የራሱን ሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ በራሱ ባለስልጣን ሻረዉ::ሀገሪቱንም ለሱዳን  አሳልፎ እንደ ሰጠ አመነ
የኢትዮጵያ ህዝብ ሱዳን ልኡዋላዊት ኢትዮጵያን ጥሳ ገብታ የኢትዮጵያ መሬቶችን ወራለች እያለ ሲጮህ የአቢይ መንግስት ፕሮፖጋንዲስቶች እራሱን ዲና ሙፍቲን ጨምሮ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ገብታ የያዘችዉ መሬት የለም እያሉ ሲቀደዱ ነበር::እንዲያዉም ይባስ ብለዉ ህዝብ ሲሳደቡ እና ሲያንጓጥጡ ነበር::አሁን ግን ሳያፍሩ የራሳቸዉን ዉሸት በራሳቸዉ አንደበት አጋልጠዉት ቁጭ አሉ::
“እኛ ያስቀመጥነው ግልፅ እና ግልፅ precondition ወደነበራችሁበት ተመለሱ እና በግልፅ እንነጋገር ነው” ሰሞኑን ዲና ሙፍቲ የተናገረዉ ነዉ::ይሄ ማለት ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መሬት ዘልቃ ገብታለች::ይሄ ማለት የአቢይ መንግስት ሱዳን የወረረችዉን መሬት በሀይል እርምጃ ገፍትሮ ከማስወጣት ይልቅ በድርድር እና በመለማመጥ “ወደ ድነበራችሁበት ተመለሱ እና በግልፅ እንነጋገር ነው” እያለ ነዉ::
በድንበር አካባቢ የሚኖረዉ ህዝብ እራሱንም ድንበሩንም ለመከላከል የሀይል እርምጃ ሲወስድ የአማራ ክልል ሚኒሻ በኢትዮጵያዊዉ ላይ የሀይል እርምጃ እንዲወስድ እና ኢትዮጵያዊዉን እንዲያሸማቅቅ ያዘዘዉ የአቢይ መንግስት ሁለት ሀገር እና ሁለት አይነት ዜጎች በልቡ አዝሎ የኢትዮጵያን ልኡዋላዊነት በአንድ ልብ ሆኖ ይጠብቅላታል ማለት ዘበት ነዉ::በአቢይ መንግስት ልብ ዉስጥ ያለዉ አንዱ ሀገር ኦሮሚያ የሚባል የህልም ሀገረ ነዉ:: ኦሮሚያን በቤኒሻንጉል በኩል ካሰፋን እና ሌሎችን ነገዶች ጠርገን ካጠፋን በቃ ሀገር ኖረን የሚሉት ስንኩላን አክራሪ ኦህዴዳዉያን/ኦነጋዉያን የጋራ ሀገር ሚስጢር ሊገባቸዉ ስላልቻለ በጎንደር በኩል ያለዉ ምድር የአማራ ስለሆነ ከፈለጉ ይውሰዱት ብለዉ ማልመጣቸዉ መሆኑ ነዉ ሰላሳ ዉሸት የሚዘላብዱት::
ከትግራይ የፈለቁት ወያኔዎች ሁለት ሀገር በልባቸዉ አዝለዉ ኢትዮጵያን ለሃያ ሰባት አመታት እንዲመሩ እግዚአብሄር እድል ቢሰጣቸዉም እነሱ ግን ኢትዮጵያን የመሯት የትግራይ ነጻዉጭ ሆነዉ እስከ እለተ ሞታቸዉ በሁለት ልባቸዉ እያነከሱ ነዉ::ትግራይ የምትባል የህልም ሀገር እና ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አዝለዉ  ሁለት ልብ ሆነዉ ሲምታታባቸዉ የትግራይንም ህዝብ ሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ መቀመቅ ከተዉት ወደ አፈራቸዉ ወረዱ::ትግሬ የሚባል ዜጋ እና ኢትዮጵያዊ የሚባል ሁለት አይነት ዜጋ በሁለት ልባቸዉ አዝለዉ ሲምታታባቸዉ ሁለቱንም ለመከራ ዳርገዋቸዉ ወደ አፈራቸዉ ገቡ::
“ያዘላችሁት ሁለት ሀገር እና ሁለት አይነት ዜጋ እናንተንም ኢትዮጵያንም እያምታታ ነዉ::ስለዚህ ይሄን ነገር ቀይሩ”  ብሎ የነገራቸዉን እና የመከራቸዉን ሁሉ  ደግሞ “ትግሬን ትጠላለህ” እያሉ ህዉሃት ማለት ትግሬ ነዉ ብለዉ እራሳቸዉ አምነዉ የትግራይንም ህዝብም ሲያምታቱት ኖረዉ ዛሬ የትግራይን ህዝብ ለመከራ ጥለዉት ሄደዋል::
ሁለት ሀገር በልብ አዝሎ  እና ሁለት አይነት ዜጋን በልብ ተሸክሞ በሁለት ልብ ማንከስ ግን በህዉሃት አልበቃም::በኦነግ/ኦህዴድ ቀጥሏል እንጂ::እንዴዉም በከፋ እና በከረፋ መልክ ቀጥሏል::ኦነጋዉያን/ኦህዴዳዉያንም ልክ እንደ ህዉሃት ሁሉ “ሁለት ሀገር በልባችሁ አዝላችሁ እና ሁለት አይነት ዜጋ በልባችሁ ተሸክማችሁ አታንክሱ::ያላችሁ አንድ ኢትዮጵያ የሚባል ሀገር ነዉ::ያላችሁም አንድ ኢትዮጵያ የሚባል ህዝብ ነዉ ” ሲባሉ እየጮሁ እና እያጓሩ “እናንተ እንዲህ የምትሉት ኦሮሞን ስለምትጠሉ ነዉ::ኦህዴድ/ኦነግ ማለት እኮ ኦሮሞ ነዉ::”ይላሉ::ሆኖም ህዉሃት የትግራይን ህዝብ እንደማይወክል ሁሉ ኦነግ/ኦህዴድም የኦሮሞን ህዝብ አይወክልም::የህዝብ ቁመት ከፓርቲ ቁመት በላይ ብቻ ሳይሆን ህዝብ ከሀገር ጋር ህያዉ ሆኑ በታሪክ ፍሰት የሚቀጥል ነዉ::የኦሮሞ ህዝብ ሰፊ እና ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ ኦሮሚያ ሳይሆን ቁመቱ ኢትዮጵያ ነች::የተምታታበት የአቢይ መንግስት ግን ከኦሮሚያ ሌሎች ነገዶችን በማጽዳት እንዲሁም ቤኒሻንጉልን ወደ ኦሮሚያ በመከለል ከዚያ ብኋላ ነጻ ኦሮሚያ የሚባል ሀገር ለመፍጠር በሚቋምጡ ኋላ ቀር አክራሪ ኦነጋዉያን/ኦህዴዳዉያን የተሞላ ነዉ::
ለዚህ ነዉ እንደ ዲና ሙፍት ህዝብ እንኳን ይቅርታ ሳይጠይቁ ጠዋት ህዝብ እያመናጨቁ የካዱትን ነገር ማታ ደግሞ በቴሌቪዥን ወጥተዉ “እኛ ያስቀመጥነው ግልፅ እና ግልፅ precondition ወደነበራችሁበት ተመለሱ እና በግልፅ እንነጋገር ነው”
እያሉ የሚቀጥብሩት:: አሁን ድረስ የሱዳን ጦር አርባ ኪሎ ሜትር ተሻግሮ እና ገፍቶ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ሰፍሮ ሳለ እነ ዲና ሙፍቲ ግን ሽምጥጥ አድርገዉ “ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ አልገባም:: አሉባልታ ነዉ” ሲሉ ሰነበቱ::አሁን ደግሞ ተምታትቶባቸዉ እዉነቱን እራሳቸዉ አወጡት:: የዚህ ችግር በአንዱ ልባቸዉ ኢትዮጵያ ሀገራቸዉ የሆነች ይመስላቸዋል::በሌላዉ ልባቸዉ ኦሮሚያ የምትባል ሀገር አዝለዉ ይዞራሉ::
ይሄ  በሁለት ልብ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ የማንከስ የተረገመ አካሂያድ ለኦሮሞም ህዝብ ሆነ ለመላዉ ኢትዮጵያ ህዝብ ጥፋትን እንጂ አንዳች የሚረባ ነገር ይዞ አይመጣም:: የኢትዮጵያ ህዝብ እጣ ፈንታ የተሳሰር ነዉ::በዚህ የሚጠራጠር ካለ ሞኝ ብቻ ነዉ::ህዉሃቶች ትግራይን ብቻ ማበልጸግ የሚችሉ መስሏቸዉ ከሌላዉ ኢትዮጵያዊ የተለዬ ኢንቨስትመንት ትግራይ ላይ ለማድረግ በሌላዉ ኢትዮጵያዊ ላይ ያልፈጸሙት ወንጀል  የለም::ሆኖም ዛሬ የሚሰማዉ ነገር አስደንጋጭ ነዉ::ትግራይ ላይ የተገኘች መርፌ ሳትቀር ወደ ሻቢያ ምድር ተጠርጋ እየተወሰደች ነዉ ወይም በዉጊያዉ እየፈረሰ ነዉ እየተባለ ነዉ::በብዙ ሚሊዮን የትግራይ ህዝብም ለርሃብ እንደተጋለጠ እየተነገረ ነዉ:: ይሄ ሁሉ እዳ እና መዘዝ በህዉሃት ተንኮል:ምቀኝነት:ሰይጣናዊ የፖለቲካ ስሌት እና ሲነግሩት አልሰማም ባይነት የተከሰተ መዘዝ ነዉ::ኢትዮጵያንም ሆነ ትግራይን እሳት ላይ ጥሏቸዉ ህዉሃት ከስሟል::
ሆኖም ይሄዉ ሁለት ሀገር እና ሁለት አይነት ዜጎችን በሁለት ልብ አዞሎ የመዞር መዘዝ በኦነግ/ኦህዴድም እየተደገመ ነዉ::ደጋፊዎቹ አይሰሙ:አባላቱ አይሰሙ: መሪዎቹ አይሰሙ::ብቻ ዝም ብሎ ተራዉ የኛ ነዉ እያሉ ከቁመት በላይ መዝለል ነዉ:: የአቢይ መንግስት በብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ ዜጎች የዘር ፍጅት እና ማጽዳት ሲደረግባቸዉ አላዬሁም አልሰማሁም ብሎ የሚክደዉ ሁለት አይነት ዜጎች እና ሁለት አይነት ሀገር በልቡ ይዞ ስለሚዞር ነዉ::አንደኛዉ ሀገር እና አንደኛዉ አይነት ዜጋ ለእሱ የእንጀራ ልጅ ነዉ::ቢያልቅ:ቢፈናቀል:ቢሰደድ:ቢራብ : ቢጠማ ምኑም አይደለም:: ሌላዉ አይነት ዜጋ ደግሞ ከሀረር አምጥተህ አዲስ አበባ ቦሌ ቤት ሰርተህ የምታሰፍረዉ:ብርድ እንዳይመታዉ የምትጠነቀቅለት ዜጋ ነዉ::ከአዲስ አበባ ህዝብ መቶ ሽህ ኮንዶሚኒዬም ነጥቀህ ያለምንም ተጠይቅ የምታድለዉ ነዉ::ሌላዉን ኢትዮጵያዊ ነገድ እየጨፈጨፍክ የሌላዉን ኢትዮጵያዊ ቤትና ንብረት የምታድለዉ ነዉ::
ሁለት ሀገር በልብ ይዞ ሁለት አይነት ዜጎች በልቡ አዝሎ በሁለት እግሩ የሚያነክስ መንግስት የሀገር ጥፋት ምንጭ ነዉ::አቢይ ከስልጣኑ መነሳት ብቻ ሳይሆን ያለበት ሁለት ሀገር እና ሁለት አይነት ዜጎችን በመሪዎች እና በፖለቲከኞች ልብ ዉስጥ የሚቀርጽ የተረገመ የጎሳ ፖለቲካ በህግ መታገድ ይኖርበታል::ይሄ ግን በቅንጦት የሚገኝ ወይም በብዕር  ሀይል ድል የሚደረግ ሀገራዊ ገድል አይደለም::መራራ እና ጥልቅ ህዝባዊ ትግል ተደርጎ የሚገኝ ሀገራዊ ትርፍ እንጂ::አሜሪካኖች እንደሚሉት አንዲት ሀገር እራሷን በታላቅ የቅድስና እና የአንድነት ማማ ላይ ስታስቀምጥ ብቻ በመሪዎች እና በፖለቲከኞች ልብ ዉስጥ አንዲት ሀገር እና አንድ አይነት ሚዛን ላይ የሚሰፈር እኩል የተከበረ ዜጋ ይኖራል::
የታላቋ አሜሪካዊ መስራች አባቶች እንዳስቀመጡት “ONE NATION UNDER GOD INDIVISIBLE!” እንዲሉ ::  የቀደሙ ሀያላን ኢትዮጵያዉያን ነገስታት እንዳስቀመጡት ደግሞ “ኢትዮጵያዊ ሁሉ አንድ የእግዚአብሄር ህዝብ ነዉ::አንድ ሀገር አንድ ህዝብ ” እንዲሉ:: ሀገር በዚህ ደረጃ ላይ የቆመ የሀሳብ ማማ ላይ ስትቆም ብቻ ሁለት ሀገር እና ሁለት አይነት ዜጋ በልብ ይዞ የመዞር እዳ ተፍቆ ነጻ ሀገር እና ነጻ ህዝብ ይኖራታል::
Filed in: Amharic