አባ መላ ሚስታቸውን የዳሩ እለት…!!!
በቀለ ላቀው
ከዕለታት አንድ ቀን ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ የችሎት ሥራ ሠርተው ለምሳ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ባለቤታቸው የፊጥኝ ታስረው ደረሱ። ባለቤታቸው ብቻ ሳይሆኑ እንድ ሌላ ታማኝ አሽከራቸውም በተለየ ክፍል ውስጥ ታስሯል።
ፊታውራሪ ለቁጣም ሆነ ለነገር የማይቸኩሉ፤ «ነገር ከሥሩ ውሃ ከጥሩ» እንዲሉ፤ ሁኔታዎችን ጠይቀው፣ አጥንተውና አጣርተው ውሣኔ ላይ የሚደርሱ ብልህና አስተዋይ ሰው ነበሩ፡፡ ታዲያ የባለቤታቸው መታሰር እምብዛም ሳያስደነግጣቸውና ሳይሰቀጥጣቸው በአካባቢው የነበሩትን ሌሎች ወታደሮች ጠርተው ጉዳዩን ጠየቁ። እነርሱም እመቤታችን ከጌታዬ አሽከሮች መሃል ከአንዱና በአሁኑ ሰዓት ተይዞ ከሌላኛው ክፍል ታስሮ ካለው ጋር ተኝተው ነውር በመፈፀማቸው ነው ያሠርናቸው። ስለዚህ እርሱን አንገቱን በጐራዴ እንቁረጠው፣ ወይም እርስዎ በመሰሎት ሌላ ቅጣት ይበቀሉት፤ ሕግ ይደግፎታል አላቸው።
እርሳቸውም ጉዳዩን ሰምተው እንዳበቁና ትንሽ አሰብ ካደረጉ በኋላ በሉ ሁለቱንም ፍቷቸው፤ የሚበላም እህል ስጧቸው፤ ትንሽም ከተዝናኑ በኋላ ወደኔ አምጧቸው ብለው ትዕዛዝ ሰጡ። በትዕዛዙም መሠረት ሌሎች ወታደሮች ግዳጃቸውን ተወጡ። ከዚህ በኋላ ነበር ፍቅረኞቹን በግል ያነጋገሩትና ለምን ያህል ጊዜ እንደሚተዋወቁ፣ መዋደድ አለመዋደዳቸውን የጠየቁት። እነርሱም ያለምንም ማመንታትና መወላወል እንደሚዋደዱ ገለፁ።
ይህን ካጣሩ በኋላ በሉ ተመለሱ ብለው አሽከሮቻቸውን ጠሩ። ለሰላሣ ሰው የሚበቃ እራት እንዲዘጋጅ አዝዘው ግብዣው ተዘጋጅቶ ጥሪው ለሰላሣ መካንንት ከነሚስቶቻቸው ተላከ፡፡
የራት መሰናዶው አልቆ እንዳበቃ የግብዣው ሰዓት ደረሰ። የተጠሩትም እንግዶች ከነባለቤቶቻቸው ወደ ተጋበዙበት አዳራሽ ፊታውራሪን እጅ እየነሱ መግባት ጀመሩ። እንግዶቹ ተጠቃለው መግባታቸውን ፊታውራሪ እንዳወቁ አጭር ንግግር ለማድረግ ብድግ አሉ። ስለመጣችሁ በጣም አመሰግናለሁ ካሉ በኋላ ድንገት ሳይታሰብ ዛሬ ይህንን ግብዣ ያደረግኩት በይፋ ያልወጣ ሰርግ ከዛሬ ጀምሮ ይፋ እንዲወጣና ሁለቱ ተጋቢዎች የጋብቻ ሥነሥርዓታቸውን እንዲያከብሩ ነው። ብለው ሳይጨርሱ፤ በመከንንቱ መሃል የቅሬታና የሹክሹክታ ድምፅ ተሰማ። ወዲያው ከተጋቢዎቹ አንዷ ባላቤታቸው መሆኗ ተረጋገጠ። ግብዣው ተደርጉ ካበቃ በኋላ ባላቤታቸው ለነበሩትና ለአዲሱ ባለቤታቸው ሁለት ሁለት ሙሉ ልብስ፣ ጌጥ፣ በቂ መሬት፣ ከብት እንዲሁም የዓመት ቀለብ አሰፍረው አዲስ ኑሮ ወደ ሚመሰርቱበት ሸኟቸው።
ምኒልክ ይህን ጉዳይ ሲሰሞ ሀብተጊዮርጊስን ጠርተው ለምን እንዲህ እንዳደረገ ጠየቋቸው። ሀብተጊዮርጊስም ሲመልሱ እንዲህ አሉ፤ «ጃንሆይ የኔ ያንድ የንጉሠ ነገሥት ጦር ሚኒስትር ሚስት በክብርም ሆነ በሀብት ምንም ጥቅም ከማይሰጣት ሰው ጋር ከሄደች በፍቅር እንጂ በሌላ ምክንያት ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ሴትዮዋ የፍቅር እንጂ የገንዘብ ሰው አለመሆኖን አደንቃለሁ፤ እደግፋለሁ፤» በማለት መልስ ሰጥተው በዚሁ ተጠናቀቀ።