እስክንድር ነጋ በጽልመት ውስጥ ፈንጥቆ ያንጸባረቀ የእውነት፣ፍትህ፣ነጻነትና እኩልነት ቀንዲል ብርሃን ነው!!!
ወንድወሰን ተክሉ
ባለታሪኩ እስክንድር ነጋ
የግፉአን ተስፋ ግፈኞችን እሚያሰጋ
መፈክሩ ድል ለዴሞክራሲ
አዲስ አበቤን ነጻ ሊያወጣ ከህወሃት ወራሽ ሌጋሲ ተከርችሟል ዛሬ በወህኒ ቤት
ብርሃን ሆኖ ስለመራው በጨላማው ጽልመት
***
እስክንድር ነጋ የዚህ ትውልድ Extraordinary የሆነ ሀብት ነው፦
እስክንድር በዘመናችን ትውልድ ውስጥ የተፈጠረ ልዩ ሰው Extraordinary ነው፡፡ ይህ ልዩ የሚያደርገው ስብእናዊ ማንነቱ የጽናት ተምሳሌነቱ፤ የእውነት ቀንዲል ብርሃንነቱ ሳይወላውል ሳያፈገፍግ ከእንግዲህስ ይብቃኝን ስሜት ከቶም ሳይፈጥር «ሀ»ብሎ የህትመት ስራውን ከጀመረበት የመጀመሪያ እትሙ ኢትኦጲስ ከ1984/1992 ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በጽኑ አቋሙ ቆሞ የምናየው ህያው Legend በመሆኑ ነው፡፡ አብረውት የጀመሩት እነጋዜጠኛ ተፈራ አስመራ ጋዜጠኛ ወርቁ በህልፈተ ህይወት ይህቺን የትግል ዓለም ተሰናብተው ሲያልፉ ከእሱ በኃላ የጀመሩትና በቁጥር ከ500በላይ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች አባላት አብዛኞቹ ሀገር ጥለው ለስደት ጥቂቶችም ሙያ ቀይረው ወደ ሌላ አዲስ ህይወት በተሸጋገሩበት ሁኔታ እስክንድር ነጋ ግን በመጀመሪያ ህትመቱ ኢትኦጲስ ምክንያት የእስርና የማሳተም እገዳ ሲጣልበት ከእስር እንደወጣ ዘ-ሐበሻን እንግሊዘኛ ጋዜጣን ለጥቆም ወንጭፍ ጋዜጣንና መጽሄትን (እኔም ተሳታፊ የነበርኩበት የህትመት ስራ ነው)ከዚያም ዝነኛውን ምንሊክን፣አስኳልን፣ሳተናውን …ወዘተ እየቀያየረ በማውጣት አይበገሬነቱን በገሀዳዊ ተግባር ያሳየ ብቸኛ የነጻው ፕሬስ እማይጠፋ የቀንዲል ብርሃን ነው፡፡
እናም ዘጠኝ ግዜ ያሰሩት እጁ እስኪወላልቅ ድረስ በማእከላዊ እየተፈራረቁ የደበደቡት የትናንትኞቹ ባለስልጣናት የዛሬዎቹ ተደምሳሽ ህወሃቶች የሚጠሉትን ያህል እጅግም የሚፈሩት ብሎም በጥላቻቸውም ውስጥ በእጅጉም የሚያከብሩት ሰው ለመሆን የበቃው በማይናወጥ ጽኑ አቋሙና ለድርድርና ለግላዊ ጥቅም በማይለወጡት ህያው የሆነ ህዝባዊና ሀገራዊ ህልሞቹ ምክንያት ነው፡፡
በአንድ ወቅት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ክህወሃት ተለይቶ የራሱን የህትመት ስራ የጀመረው የሪፖርተሩ አማረ አረጋዊ በየመንግስት ቃለ አቀባይ በሆነችው ሰሎሜ ታደሰ ቦሌ ወሎ ሰፈር ጽ/ቤት ተገናኝተን ስለእስክንድር ያለኝን አልረሳውም፡፡ «ከሁላችሁም የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ውስጥ እጅግ በተለየ ሁኔታ ጽኑ ዓላማ ይዞ ሲንቀሳቀስ እማየው አንድ እስክንድር ነጋን ብቻ ነው» በማለት ነበር ጋዜጠኛ አማረ አረጋዊ ስለእስክንድር የነገረኝ፡፡ ምክንያቱንም በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን መቼም ቢሆን የማልረሳው የአማራ ቃላቶች -ከኪሱ ወረቀትና እስክሪብቶ በማውጣት -ኢትኦጲስ፣ዘ-ሐበሻ፣ወንጭፍ፣ምንሊክንና አስኳል የሚለውን የጋዜጣ ስሞችን ከጻፈ በኃላ «አብዛኛው የነጻ ፕረስ ጋዜጠኛ አንድና ሁለት የህትመት ስራዎቹ ሲታገዱበትና ሲታሰር ወይ ህርገር ለቀው ይሰደዳሉ አሊያም ስራ ቀይረው እራሳቸውን ከመንግስት ጋር የሚያደርጉትን ፍጥጫና ፍልሚያን ያቆማሉ፡፡ እስክንድር ግን ይለያል፡፡ ይህንን ስራ እንደጀመርኩ (የሪፖርተርን ጋዜጣ ማለቱ ነው)አካባቢ ቱሪስት ሆቴል ተገናኝተን በፍጹም አታሸንፉንም እኛ ነን የምናሸንፋችሁ፤ እንተያያለን ብሎ አፍጥጦብኝና አስፈራርቶኝ ነው በተቀመጥኩበት ጥሎኝ የሄደው፡፡ በመካከላችሁ እሱን የመሰለ ሶስት አራት ጋዜጠኞች ቢኖሩ ኖሮ ለኢህአዴግ ከባድ አደጋ ይደቅኑ ነበር…» በማለት አማራ በጠላትነት ፈርጆ በጠላት አይን ስለሚያየው እስክንድር በ1992ዓ ም (2000)ላይ በሰሎሜ ታደሰ ቢ/ሮ የነገረኝን አልረሳሁም፡፡ ከወዳጅ ምስክርነት ይልቅ የጠላት ምስክርነት ይበልጥ ሚዛን ይደፋልና ከሌሎች አቻ ባልደረቦቹ አንደበት ሲስተጋባ ከነበረው ይልቅ ይህ እስክንድርን በጠላትነት ከፈረጀው የሪፖርተሩ አማራ አረጋዊ አንደበት የተነገረውን እውነት ለማስታወስ ወደድኩ፡፡
አዎን እስክንድር በእርግጥ በብዙ መልኩ በተለየ ሁኔታ ልዩ የሆነ ስብእናን መርህን እይታዊ አስተሳሰብን ይዞ የተፈጠረ የዚህ ትውልድ Extraordinary የሆነ ህያው Legend ነው፡፡
ከአማረ አረጋዊ ምስክርነት በኃላ ጥቂት ቆየት ብሎ በ1993/2000 ላይ ሟቹን ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያምን ኢንተርቪው ላደርግ ቤታቸው ድረስ በሄድኩበት ወቅት ጥያቄህን ስጠኝና መልሴን በጽሁፍ እሰጥሃለሁ ባሉኝ መሰረት ላቀረብኩላቸው ጥያቄ የጻፉትን መልስ መሰል መጣጥፍ (አርቲክል) ስቀበል ጽሁፉን እየሰጡኝ ሳለ በድንገት ያ ጠይም ወጣት ቀጠን ብሎ ረዘም ያለው ጋዜጠኛ እንዴት ነው ሲሉ ጠየቁኝ ? ብዙም ማሰብ ሳይገባኝ እስክንድርን ነው የሚሉት ስላቸው አዎን ያ ዘ-ሐበሻን ኢትኦጲስን ሲያሳትም የነበረ ጎበዝ ጋዜጠኛ የትገባ ስሙን ማየት ካቆምኩ ቆይቻለሁ ሀገር ጥሎ ተሰደደ እንዴ ?? ሲሉ ነበር የጠየቁኝ፡፡ ፕ/ር መስፍን ይህንን ጥያቄ በሚጠይቁኝ ወቅት እስክንድር ምንሊክና አስኳል የሚባሉ በነጻው ፕረስ ታሪክ ውስጥ በአንድ ብር ዋጋ ባለ24ገጽና ባለ16ገጽ ጋዜጦችን (በወቅቱ በአንድ ብር ዋጋ የሚሸጡ የነጻ ፕረስ ጋዜጦች በሙሉ የገጾቻቸው ብዛት 8ገጽ ብቻ ነበር)እያሳተመ ከፍተኛ ተነባቢነትን ያተረፉበት ወቅት ቢሆንም እስክንድር አብዛኛውን መጣጥፍ፤ ዜናና ሀተታዎችን የሚጽፍ ቢሆንም ስሙን ስለማያሰፍርና ብሎም በማንኛውም ግብዣ Reception ላይ እንደ እኔና ሌሎቻችን የማይታደም በመሆኑ ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም ሀገር ጥሎ የተሰደደ ሊመስላቸው ችሏል፡፡ እናም የለም በሀገር ውስጥ ነው ያለው በማለት እየሰራቸው ያሉትን ጋዜጦች ስም እንደነገርኳቸው «ገባኝ፡፡ አሁን ገባኝ ምንሊክና አስኳል ጋዜጦች ለምን እጅግ የተለዩና ተነባቢ ተወዳጅ ጋዜጦች እንደሆኑ ..» በማለት ከተናገሩ በኃላ «እሱ ልጅ በጣም ጎበዝና ከሁላችሁም የተለየ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በርታ በለው»በማለት ነገሩኝ፡፡
እንደ አጋጣሚ ሆኖ የአማራ አረጋዊንም ሆነ የፕ/ር መስፍን ወልደማሪያምን አስተያየትና መልእክት ለእስኬው ሳልነገረው እስከዛሬ ቆይቻለሁ፡፡ ለእስክንድር ያልነገርኩበት ምክንያት እንዲህ አይነቶችን የሞራል ድጋፍና አድናቆትን በሙሉ ልብ የሚያደምጥበት አፕታይት Appetite ስለሌለው በዝምታ ማለፉን ስለመረጥኩ ሳልነግረው ቀርቻለሁ፡፡
እስክንድር ነጋ በጽልመት ውስጥ ፈንጥቆ የበራ ቀንዲል ነው፦
የጨለማ ህልውና የብርሃንን ህልውና በእጅጉ አድምቆ እንደ እንቁ የሚንጸባረቅ የብርሃን ጮራ አድርጎታል፡፡ ምናልባትም ጨለማ ባይኖር የብርሃን ዋጋና ትርጓሜ ዛሬ ካለው ብርሃናዊ ዋጋና ትርጓሜ የተለየ ይሆን ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ጨለማና ብርሃን ህብረት የላቸውም፡፡ የጨለማን ግዛት እያሸበረ የሚደፍርና ኃላም ጨለማን አባርሮ ፍጥረትን ነጻ የሚያወጣው ብርሃን ነውና ጨለማ ምንግዜም የብርሃን ተጻራሪ ባላንጣና ጠላት ነው፡፡ ብርሃን እውነት ነው፤ፍትህ ነው፣ነጻነትና እኩልነት ነው፣ጥበብና ልማትም ነው ብርሃን፡፡ በአንጻሩ ጨለማ ደግሞ የዚህ የብርሃን ትርጓሜን በተጻረረ መልኩ ሀሰተኝነት፣ግለኝነት፣ጨቋኝና በዝባዥነት፣ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን ከብዙኃናዊ እኩልነትና አንድነት ይልቅ የጥቂት ገዢ ኃይሎችን የበላይነትና በብዙኃኑ ላይ በፈላጭ ቆራጭነት ያለአንዳች ተጠያቂነት ስልጣንን አማክሎ ለግል፣ለቡድንና ከፍም ካለ እጅግ ለተወሰኑ ውሱን የገዢው አካል የጎሳ አባላት የሚዘረጋ ጥቅመኝነትና ቡድናዊነት የጨለማው አስተሳሰብ መገለጫዎች ናቸው፡፡
እናም እስክንድር በጨላማ ውስጥ የተቀጣጠለ የእውነት፣የፍትህ፣የዴሞክራሲ፣የነጻነትና የፍትሃዊ እኩልነት ቀንዲል ብርሃን ሆኖ በኢትዮጵያ ግዛት በነገሰው ስርዓታዊው ጨለማ ውስጥ ሆኖ እያንጸባረቀ የበራ ቀንዲል ሆነ ማንም ምንም ባላለበት ወቅት፣ማንም ባልነቃበት ወቅት ብድግ ብሎ ስለአዲስ አበባና ስለአቢይ መራሹ የኦህዴድ አፓርታይዳዊ ሴራን በግልጽና በድፍረት መግለጽ ሲጀምር፡፡
ከመቶ በላይ የሚቆጠሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ህጋዊ ፍቃድ አግኝተው ዋና ጽህፈት ቤታቸውን በከፈቱባት አዲስ አበባ የተባበሩት የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ጉዳይ አንድ የሆነ አቋም ይዘው አዲስ አበባ የኦሮሚያ ናት ብለው በኦህዴድ መሪነት በይፋ በገለጹበት ወቅት ለአዲስ አበባ ድምጽ ሆኖ ብድግ ያለ ሰውና ድርጅት ቢኖር አንድ ድርጅት አልባ የነበረ አንቂ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ብቻ ነው ስለ አዲስ አበባ ድምጽ ሆኖ ብቻውን የተባበሩትን የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የተጋፈጠው፡፡ በወቅቱ ባልደራስ የሚባል ሲቪክ ተቋምም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም ሊቋቋም ይቅርና እስከነ አካቴውም ለመወለድ ያልተጸነሰበት ወቅት ነበርና እስክንድር ብድግ ብሎ በአቶ ለማ መገርሳ በኦሮሚኛ ቋንቋ የተላለፈውን የአዲስ አበበን ህዝብ አሰፋፈርን(ዲሞግራፊን) የመቀየርን ሴራና በገፍ ሲታደል የነበረን የመታወቂያ እደላን ሴራ አደባባይ በማውጣት መጋፈጥ ሲጀምር ማንም ሰውም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ነን ባዮች ትንፍሽም አላሉም ነበር፡፡
በ1997ቱ ህዝባዊ ምርጫ የአዲስ አበቤን ልብ አግኝቶ ለከተማዋ ከንቲባነት ተመርጦ የነበረው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከስደት ተመልሶ አዲስ አበባ ውስጥ መምነሽነሽ ከጀመረ አምስትና ስድስት ወራቶችን ያስቆጠረ ቢሆንም በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የተባበሩት የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ገዢው የኦህዴድ ፓርቲ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ናት የሚል ግልጽና ይፋዊ አቋም በአደባባይ ባሳወቁበት ወቅት በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው ግንቦት 7ድርጅት የአዲስ አበባን ህዝብ ታላቅ ውለታን አሸቅንጥሮ በመጣል በኦሮሚያ ክልሉ ሚዲያ OBN ላይ ቀርቦ «በኢንጂነር ታከለ ኡማ ከንቲባነት ፍጹም አምናለሁ፡፡ ባለአደራ ገለመሌ የሚባል ነገር መስማት አልፈልግም» በሚል መልስ በአዲስ አበቤው ላይ የክህደት ውሃ ሲቸልስ እስክንድር ነጋ ነበር በግል ተነሳሽነት የአዲስ አበባን ህዝብ ጠርቶና አወያይቶ ህዝቡ እራሱ የባልደራስ ሆቴል Consensus ውጤት የሆነውን የባለአደራ ምክር ቤትን ወልዶ ለማቋቋም ያበቃው፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ታሪክ የአንድ አቋመ ጽኑ እስክንድር ነጋ ስራና ታሪክ ብቻ ሳይሆን የመላ አዲስ አበቤ ህዝብ መሪ ኮክብ ሆኖ እንደ ቀንዲል ባበራው እስክንድር ነጋ መሪነት የመሰረቱት መሰረተ ህዝብ የሆነ የድርጅት ታሪክ ነው፡፡
ከገዢው የኦህዴድ/ብልጽግና ፓርቲ ጀምሮ በተቃዋሚው ጎራ ያለውና ከመንግስት ጋር የተሰለፈው መላ የኦሮሙ ፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ አንድ ግንባር የፈጠሩበት የአዲስ አበባ ህልውና የኦሮሚያ አድርጎ የማቅረቡ ዘመቻና ሴራዊ ፖለቲካ የቱንም ያህል ቢጧጧፍ ከታሪክ፣ከህግ፣ከሞራልና ከስነ ህዝብ አሰፋፈር አኳያ እውነት የሚያደርግ ኢምንት ያህል ነጥብ የሌላቸው ሆነው ሳለ በእንደነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መራሹ ግንቦት7 ኃላም ኢዜማ አይነቶቹ ተቃዋሚ ተብዬዎች ችሮታና ስምምነት ኦህዴድ ያሰለፋቸውን ከ10በላይ የኦሮሞ ፓርቲዎችን ግንባር ፈጥሮ አዲስ አበባን ለመሰልቀጥ ያደረገውን የመጀመሪያ ዙር የወረራ እርምጃን ማክሸፍና ማስቆም የቻለ አንድ አዲስ አበቤያዊ ኃይል ቢኖር በአቋም ጽኑው እስክንድር ነጋ መሪነት በመላ አዲስ አበቤያዊ የተመሰረተው የባለአደራው ምክር ቤት ኃላ የባልደራስ ሲቪክ ድርጅት መጨረሻም ላይ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሆነው ድርጅት ብቻ ነው፡፡
በዚህን ግዜ ነው በሰላም የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ሆኖ ዝናው በመላ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እየናኛ የነበረው አቢይ አህመድ አሊ እሳት ጎርሶና እሳት ለብሶ አይኖቹን እያጉረጠረጠ «ባለአደራ ምናምን የሚባል ነገር አናውቅም፡፡ ግልጽ ጦርነት እንከፍታለን» ሲል ያንባረቀው፡፡
ጠምሩ አቢይ አህመድ አሊና በሊቀመንበርነት የሚመራው ኦዴፓ/ኦህዴድ ከሌሎች ወደ አስር የሚጠጉ የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር በመሆን የአዲስ አበባን የኦሮሚያ ባለቤትነትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ያመነ ብቻ ሳይሆን ይህንንም እምነቱን ተግባራዊ አድርጎ በመላው የኦሮሞ ፓርቲዎችና ኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በተቀረው ኢትዮጵያዊ ዋጋ ከፋይነት ታላቅ ታሪክና ተወዳጅነትን ለማትረፍ ቋምጠዋል፡፡
የኦሮሞ ፖለቲከኞች አዲስ አበባ የኦሮሚያ ናት ብለው በድፍረት ሲናገሩ ከሚያቀርቡት መከራከሪያ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ከተማይቱ ዙሪያ የሰፈረው የኦሮሞ ህዝብ ስለሆነ የተገነባችበትም መሬት የኦሮሞ መሬት ነው የሚለው ቅድሚያ የሚሰጡት የመከራከያ ነጥባቸው ነው፡፡
ግን ይህ የመከራከሪያ ነጥባቸው ለስም ያህል ይጥቀሱት እንጂ አንዳችም መሰረት የሌለው ነጥብ በመሆኑ አቢይና የኦሮሞ ፖለቲከኞች አዲስ አበባን በውዴታዊ ህግ ሳይሆን በሁሉንም ኬኛ የወረራ ስልት ወርረው ለመሰልቀጥ ሲነሱ የተጋፈጣቸው አንድ እና አንድ የሆነ ሰውና ድርጅት ብቻ ነው፡፡፡ያም ሰውና ድርጅት እስክንድር ነጋና የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ነው፡፡
አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሬት ላይ ነው የተሰራችው የሚለው የኦህዴዳዊያኑ
ጩህት መሰረት አልባ የሚሆንበት ዋና ምክንያት የአዲስ አበባን መሬት ጠፍጥፎ የሰራው የኦሮሞ ህዝብ ሳይሆን የዓለም ፈጣሪ እግዚአብሔር ጠፍጥፎ የፈጠረው በመሆኑና በ1878 ከተማይቱን የቆረቆረውና ብሎም የምህንድስና ሙያውን አውሎባት ከተማዋን የገነባው ኦሮሞና ኦሮሚያ የሚባሉ ስሞች እስከነመፈጠራቸው ባልታወቁበትና ባልተሰሙት ዘመነ ንጉሰ ነገሰት ዳግማዊ ምንሊክ ወቅት ሆኖ ሳለ የከተማይቱ ነዋሪ ህዝብ አሰፋፈር የአንድ ጎሳ የበላይነት የሰፈነበት አይነት ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያዊያን ብሄርብሄረሰብ ተወካዮች የሰፈሩባት ትንሺቷ ኢትዮጵያ የመሆና ሀቅ እጅግ እየተስፋፋ የመጣው የኦሮሞ ፖለቲከኛ ዛሬ ላይ ደርሶ አዲስ አበባ የተሰራችው በኦሮሚያ መሬት ላይ ነው፡ ዙሪያዋንም ከቦ የሰፈረው የኦሮሞ ህዝብ ነውና ከተማይቱ የኦሮሚያ መሆን አለባት ብሎ ሲነሳ የተማመነው ነገር ወራሪነቱንና ዘራፊነቱን እንጂ ታሪካዊ ዳራውን መሰረት አድርጎ እንዳልሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአጽንኦት የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡
ይህንን ሀቅ ገልጾ ሀሰትን ለመጋፈጥ የመርህ፣የፍትህ፣የእውነትና የፍትሃዊ እኩልነት አማኝ ሰው መሆንን ይጠይቃል፡፡ በእነ ብርሃኑ ነጋ የሺዋስ አሰፋና ወዘተ ዘንድ ያልተገኝና ብሎም ሊገኝም እማይችል ድንቅ ስብእናን እና አቋምን የተጎናጸፈው እስክንድር ነጋ ብድግ ብሎ የሀሰት ትርክቶቻቸውን እያንኮታኮተ ለነፍሱ ሳይሳሳ እራሱንና ህልውናውን አስይዞ ፊት ለፊት በመጋፈጥ ስለአዲስ አበቤያዊ ህልውና ሲል ግንባሩን ሳያጥፍ ሊጋፈጥ የቻለ ሰው ሆነ፡፡
በእስክንድር ህይወት ታሪክ ውስጥ ተደጋግሞ (ከ10 ግዜ በላይ ) የተከሰተው የእስር ክስተት በአንዷም ጉዳይ ቢሆን ስለራሱ ሲል የታሰረ ሳይሆን ስለሀገር ስለፍትህ ስለህዝብ ስለነጻነትና ስለዴሞክራሲ ሲል እየከፈለ ያለ ታላቅ መስዋእትነት ነው እንጂ ስለአንድ እራሱ ቢሆን ብዙዎች እማያገኙትን የውጭ እድል አይደለም ዛሬ ያኔ በ1980ዎቹ በ1990ዎቹና መሰል ቀጣይ አመታት ውስጥም ያለው ሆኖ ሳለ አንዲትም ቀን ቢሆን ለሰከንድ እንኳን ይህንን ስለአንድ እራሱ ስለ ውድ ባለቤቱና ስለብቸኛው አንድዬ ልጁ ሲል አስቦ የማያውቅ ልዩ የሆነ ለዓላማውና ለህዝብ ታምኖ የቆመ ጽኑ ሰው ነው እንጂ እንደ አብዛኞቻችን ቢሆን ኖሮ ዛሬ እስክንድርን በቃልቲ እስር ቤት ውስጥ የምናገኘው ሰው ሳይሆን እጅግ በተሻለና ምቹ በሆነ ግላዊ ህይወቱ ወይ በአዲስ አበባ አሊያም በአሜሪካ ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ የምናየው ሰው ነበር፡፡
በእርግጥ ዛሬ እስክንድር ነጋ በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ የባልደራስ-መኢአድ ጥምር ፓርቲዎች መሪ ተደርጎ በሌለበት የተመረጠ ሰው ነው፡፡ሁለቱ ፓርቲዎች በመጪው ምርጫ ላይ ብቁ ተፎካካሪ ሆነው ለመገኘት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ይህንን የሁለቱን ጥምረታዊ ንቅናቄን በተመለከተ በቀጣይነት እንደማቀርብ እየገለጽኩ የዛሬውን ሀተታዬን በዚህ ልገታ እወዳለሁ፡፡ ሁላችንም ከብርሃን ጋር እንሰለፍ-ሚናችንንም ከጨለማ ጋር ከማድረግ ይልቅ ከብርሃን ጋር እናድርግ፡፡ ለእስክንድር ወይም ለባልደራስ-መኢአድ ወይም ለአዲስ አበባ ብለን ሳይሆን መጀመሪያ ለራሳችን ብለን ሚናችንን ከብርሃናማው እውነት፣ፍትህ፣ፍትሃዊ እኩልነት፣ነጻነትና ከዴሞክራሲ ጋር እናድርግ፡፡!!