>

አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ : በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ አስቸኳይ መፍትሔ ይሻል! (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ

አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ : 
 
በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ አስቸኳይ መፍትሔ ይሻል!
 
ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ – ኢሰመጉ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ ነጻና ገለልተኛ የሆነ እንዲሁም  ከማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የኃይማኖት ተቋም፣ የብሔረሰብ ቡድን፣ ማኅበራዊ መደብ ወዘተ የማይወግን፣ ለትርፍ  ያልተቋቋመ የሰብዓዊ መብቶች ተከላካይ ተቋም ነው፡፡
ኢሰመጉ፤ በትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት ምክንያት ባልታጠቁና ሰላማዊ በሆኑ ሰዎች  ላይ የተፈጸመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስፋት፣ በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ፣  በብሔር ማንነታቸው ብቻ ለጥርጣሬ እና መድልዎ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ሁኔታ እና አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ  ወገኖች ጉዳይ ከፍተኛ ሥጋት አሳድሮበታል፡፡ በወቅቱ ተከስቶ በነበረው ችግር ምክንያት ለስድስት ወራት ያህል የሚቆይ  የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በመታወጁ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ገደቦች ተጥለዋል፡፡  ከእነዚህም መካከል ‹የሰዓት እላፊ ገደቦችን ጥሳችኋል› በሚል በጸጥታ ኃይሎች የኃይል እርምጃ የተወሰደባቸው ሰዎች መኖራቸውን ኢሰመጉ መረጃዎች  ደርሰውታል፡፡
ለአብነት ያህል ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እና በረከት በርሄ ጥር 11 ቀን 2013 ዓ.ም በጸጥታ ኃይሎች  መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኢሰመጉ የእነዚህ እርምጃዎች ሕጋዊነት ከፍተኛ ጥርጣሬ አሳድሮበታል፡፡
ኢሰመጉ በጦርነቱ ወቅት እና ከዚያም ወዲህ ባሉት ጊዜያት አስገድዶ መድፈርን፣ ከፍርድ ውጪ የሆነ ግድያን፣  ሕገ-ወጥ እስራትን እና እገታን ጨምሮ ዓይነተ-ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በልዩ ልዩ አካላት እየተፈጸሙ ስለመሆኑ የሚጠቁሙ አቤቱታዎችን ተቀብሏል፣ በርካታ መረጃዎችንም አሰባስቧል፡፡ በእነዚህ የመብት ጥሰቶች ሴቶች፣ ሕጻናት፣  አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ቀዳሚ ሰለባዎች ስለመሆናቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሌሎች የሐገሪቱ አካባቢዎችም  በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚንቀሳቀሱ የትግራይ ተወላጆች እስር፣ እንግልት እና መድልዎ እየደረሰባቸው ስለመሆኑም  ኢሰመጉ በርካታ አቤቱታዎች ደርሰውታል…
Filed in: Amharic