>

“ህወሓቶች ፀአዳ ማሽላ የላኩዋቸው በርካታ የትግራይ ወጣቶች በህይወት አልተመለሱም ...!!!“ (አቶ ግርማይ ሀደራ የኢዲዩ ነባር ታጋይ)

“ህወሓቶች ፀአዳ ማሽላ የላኩዋቸው በርካታ የትግራይ ወጣቶች በህይወት አልተመለሱም …!!!“

 
 አቶ ግርማይ ሀደራ የኢዲዩ ነባር ታጋይ

 

ህወሓቶች ፀአዳ ማሽላ የላኩዋቸው በርካታ የትግራይ ወጣቶች በህይወት አልተመለሱም የኢዲዩ ነባር ታጋይ አቶ ግርማይ ሀደራ አመለከቱ። ባላባቶችንና ታሪክ አዋቂዎችን ልቅም አድርገው አድነው ማጥፋታቸውን አስታወቁ።
 
አቶ ግርማይ ሀደራ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት ፣ ህውሃቶች ፀአዳ ማሽላ የሚሉት ቦታ አላቸው ፤ ትርጉሙ ነጭ ማሽላ እንደማለት ነው። አበርጌሌ አካባቢ የሚገኘው ነው ፣ በትግሉ ወቅት ወደዛ አካባቢ የላኳቻ በርካታ የትግራይ ወጣቶች በህይወት አልተመለሱም።
 
ከትግሉ ወቅት ጀምሮ በፖለቲካ አመለካከቱ ያልተመቻቸውን ታጋዮች ከደርግ ጋር ተገናኝተዋል ፣ከነራስ መነገሻ ስዩም ጋር ታሪካዊ ፍቅር አላቸው ወዘተ በሚል ፀአዳ ማሽላ በመላክ ገድለው እዛው ይቀብሯቸው እንደነበር አመልክተዋል።
 
ቡድኑ ገና ከፍጥረቱ ጀምሮ ጥንታዊነትን፣ አባታዊነትን እና ታሪካዊነትን የማይፈልግ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግርማይ ፣ የድሮ አባቶች ባይማሩም በተፈጥሯቸው የአዕምሮ እድገታቸው እና ስለሀገር አንድነት ያላቸው ግንዛቤ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
 
ህወሓቶች እነሱ በሚቃኙት መንገድ ዝምብሎ የሚጓዝ አዲስ ትውልድ ለመፍጠር ሲሉ የቀደመውን ታሪክ እና ተጨባጭ ሁኔታ የሚያውቁ እንዲሁም ያለፉ መንግስታት የሰሩትን ቀን እና ሰዓት እንኳን ሳያዛቡ የሚናገሩ አባቶችን ማጥፋት እንዳለባቸው ወስነው መንቀሳቀሳቸውን ጠቁመዋል።
 
በዚህም ባላባቶች እና ታሪክ አዋቂዎችን ልቅም አድርገው አድነው እንዳጠፏቸው ፣ በዚህ ምክንያትም ከዚያ በኋላ የመጣው የትግራይ ወጣት ትውልድ ስለትግራይ ትክክለኛ እውቀት እንዳይኖረው ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
 
ትውልዱ ትክክለኛዋን ትግራይ ከቀደመው ታሪክ እንዳያውቅ አድርገውታል ያሉት አቶ ግርማይ፣ ከዛ ይልቅ ትግራይ ታምረኛ ህዝብ ፤ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብሮ መኖር የማይፈልግ ፣እንዲሁም ሁሉን አዛዥ ሆኖ የሚኖር አድርገው በተሳሳተ የታሪክ ትርክት እንደቀረጹት አስታውቀዋል።
 
“በአንጻሩ የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ ”ሀ‘ ብሎ የሚጀምረው ከትግራይ ነው። የአክሱም ስርወ መንግስት፤ ንግስተ ሳባ እንዲሁም የየሃ ጥንታዊ ታሪኮች የሚነሱት ከትግራይ ነው። ታሪኩ እስከ ጎንደር እና ላሊበላ እንዲሁም ሸዋ ጋር ይተሳሰራል። በስነጽሁፉም ሆነ በስነ ህንጻ ጥበብ ሙያ እና ዕውቀት የነበራቸው ሰዎች ነበሩ። ቀይባህር እና ላሊበላ እንዲሁም ጣና ውስጥ ዋሻ ፈልፍለው የሚሄዱ አባቶች ነበሩን” ብለዋል።
 
ይህን ታሪክ ግን ወጣቱ ትውልድ እንዳያውቅ እና አንድነቱን እንዳያጠናክር ህወሓቶች በትግራይ የሚገኙ ታሪክ አዋቂዎችን እና ባላባቶችን አድነው ሲያጠፉ ኖረዋል። ወጣቱንም በእነሱ ትርክት ለመያዝ ታሪክና ታሪክ አዋቂዎችን ማጥፋት ላይ ተጠምደው እንደነበር አመልክተዋል።
 
“እነሱ እኮ በትግል ላይ ባሉበት ወቅት ስልጣን ከያዝን ግብር አትከፍሉም እያሉ ህዝቡን ሲዋሹት ነበር። ኋላ ስልጣን ሲይዙ ግብሩ እንደማይቀር ያወቀው ህዝብ ከሃዲነታቸውን የበለጠ አወቀው። ግብር ለአንድ ሀገር የገቢ ምንጭ መሆኑን እያወቁ ለአላማቸው ማሳኪያ እንዲሆን ግን የፖለቲካ መጠቀሚያቸው አድርገውታል”ብለዋል።
 
ህወሓቶች የሚያምኑት በመግደል እና በማግለል ነው። ስልጣን ላይ እያሉም ህዝቡን ጠርተው ስብሰባ ያደርጉና የፈለጋችሁትን ተናገሩ ይላሉ። አንድ ሰው ደግሞ ዳር ተቀምጦ ማሳሰቢያ የሚሰጠውን እና ይህን አስተካክሉ የሚለውን እየለየ ይጽፋል። በስብሰባዎች የሚናገሩ የትግራይ ልጆች በቀጣዮቹ ቀናት ተገድለው ይገኙ እንደነበር አመልክተዋል።
 
በኢኮኖሚውም ቢሆን በህዝቡ ስም የኤፈርት ድርጅቶችን አቋቁመው ለግል ጥቅማቸው እና ለቤተሰባቸው ኑሮ ማደላደያ ሲዘርፉ እና ሲያከማቹ መኖራቸውን አመልክተው፣ አርሶ አደሩ ግን በባሰ ድህነት ሲሰቃይ መቆየቱን አስታውቀዋል።
 
አርሶ አደሩን ካለው ላይም የስጦታ ቀን በማለት ካለው ከብቶች ላይ በግዴታ እንዲለግስ ሲያደርጉት ቆይተዋል። ካልሰጠ ደግሞ የሚደርስበትን በደል ያውቃልና ይሰጣል። ለእርሻው የሚሆን ማዳበሪያ ወስዶ እህሉ ባይበቅልለት እንኳን ካልከፈለ በሬውን ከመንገድ ወስዶ ስለሚያስቀርባቸው ለቀጣዩ እርሻ በሬውን እንዳያጣ ተበድሮም ቢሆን ብድሩን እንዲከፍል ያስጨንቁት እንደነበር ጠቁመዋል።
 
የትግራይ እናትም ልጆቿን በደረቷ አቅፋ እና በጀርባዋ አዝላ ድንጋይ ስትሸከም እንዲሁም አፈር ስተቧጥጥ ትውላለች። እናቶች ከሰሩ በኋላ ምግብ ይሰፈርላቸዋል። ይህም ምግብ ለስራ አሊያም ሴፍቲኔት ብለው ሰይመውታል። የህወሓት አመራሮች ግን ግማሽ ኢትዮጵያን ሊያለማ የሚችለ ሃብት የያዙ ትላልቅ የኤፈርት ድርጅቶችን ሃብት እየተቀራመቱ ኑሯቸውን ያደላደሉ ነበር ብለዋል።
Filed in: Amharic