>

ዛሬም በርሃብ ይዋሻል ማለት ነው? (ያሬድ ሀይለማርያም)

ዛሬም በርሃብ ይዋሻል ማለት ነው?

ያሬድ ሀይለማርያም

የፌዴራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣው መግለጫ በትግራይ ለርሃብ የተጋለጠ እና በርሃብም ምክንያት የሞተ ሰው የለም። ነገር ግን የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልገው ሰው ቁጥርም 2.5 ብቻ ነው ሲሉ ገልጸዋል። ይሁን እና ትላንት ለቪኦኤ መግለጫ የሰጡት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብረሃ ደስታ ደግሞ ክልሉ ውስጥ በተፈጠረው ከፍተኛ የምግብ እጥረት የተነሳ ርሃብ መከሰቱን፣ በርሃቡም ሕጻናትን ጨምሮ ሰዎች መሞታቸውን፣ አሁንም በርካታ ሰዎች አፋጣኝ እርዳታ የማይደርስላቸው ከሆነ ለከፋ አደጋ ሊዳረጉ እንደሚችሉ እና የርሃብ አደጋ ያንጃበበባቸው ሰዎች ቁጥርም 4.5 ሚሊዮን መድረሱን ገልጸዋል።
አቶ አብረሃም አያይዘው በበርካታ የክልሉ ከተሞች ከፍተኛ ዝርፊያ ጭምር መካሄዱን ገልጸዋል። 2.5 ሚሊዮን ሕዝብም ከመኖሪያው መፈናቀሉን ገልጸዋል።
እግረ መንገዴን፤ ትግራይ ውስጥ አስከፊ እርሃብ በጦርነቱ ሳቢያ ተከስቷል ሲባል፤ ድሮም የክልሉ ሕዝብ በርዳታ ነው የሚኖረው፣ የርሃቡ መንስዔ ወያኔ ነው፣ በመተከልስ ሰው ተርቦ የለም ወይ፣ በጦርነት ርሃብ ቢከሰት ምን ይደንቃል፣ ህውሃት የዘረፈው ሃብት ተሽጦ ለርሃብ ይዋል የሚሉ ፍጹም ሰብአዊነት የጎደለው፣ የነውረኝነት እና ተራ የካድሬ መከራከሪያ እያነሳቸው ልባችንን የምታወልቁን ሰዎች እባካችሁ በርሃብ ላይ እንዲህ ያለ ቧልት የወረድንበትን ዝቅጠት ነው የሚያሳየውእና ትንሽ ወደ ህሊናችው መለስ በሉ። በመተከልም ሆነ በትግራይ ለርሃብ አደጋ ለተጋለጡት ወገኖቻችን እጅ መዘርጋት የሰውነታችን መገለጫ ነው። ርሃብን እያወዳደሩ እና ሰበብ እየፈለፈሉ ትግራይ ላይ የተከሰተውን የርሃብ አደጋ ለማንኳሰስ መጣር ግን ህሊና ካለው ሰው አይጠበቅምና ተመከሩ።

4.5 ሚሊዮን የትግራይ ሕዝብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ

መለስካቸው አምሃ

መቀሌ እና አዲስ አበባ —በትግራይ ክልል በአሁኑ ጊዜ 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈለገው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የማኅበራዊ ጉዳይ ቢ ሮ አስታውቋል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ አብርሃ ደስታ ለአሜሪካ ድምፅ እንዳስታወቁት በክልሉ ውስጥ 2.5 ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል። በረሃብ ምክኒያትም የሰው ሕይወት እያለፈ ነው ብለዋል።

“ሰብዓዊ ርዳታውን ለማቀላጠፍ ሁሉንም የክልሉን መስሪያ ቤቶች በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው” ብለዋል።

Filed in: Amharic