ለጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የተላከ ግልፅ ደብዳቤ…!!!
DW
ሰሜን አሜሪካ እና አውሮጳ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ምሁራንና የመብት ተሟጋቾች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፃፉት ግልፅ ደብዳቤ አቶ እስክንድር ነጋ እና ሌሎች የታሰሩ የባልደራስ አመራቾች በአስቸኳይ ፍትህ እንዲያገኙ ጠየቁ። እነዚህ 24 ምሁራን በፃፉት ደብዳቤ «የኢትዮጵያ መንግሥት መፍትሄ እና መዋቅራዊ ለውጥ ከማድረግ ይልቅ ውስጣዊ ችግሮች እንዲባባሱ እያደረገ ይገኛል።» ሲሉ መንግሥትን ይወቅሳሉ። ለዚህም ምሳሌ ሲሉ ያቀረቡት « በባልደራስ አመራሮች ላይ የተጀመረው መሰረት አልባ ክስ እና የፍትህ መጓተት ነው።» ብለዋል። የፍርድ ሂደቱንም እጅግ በማጓተት «አመራሮቹን ከምርጫ ውድድር ውጭ ለማድረግ እየተሞከረ እንደሆነ» በመግለፅ ይህ « ለሀገሪቱ ተጨማሪ ችግር ከመፍጠር ውጭ የሚያስገኘው አዎንታዊ ውጤት አይኖርምም።» ብለዋል። ስማቸው የተሰነዘሩት ኢትዮጵያውያንም መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥበት የሚፈልጉትን አራት ጥያቄዎች በዝርዝር አስፍረዋል። ምሁራኖቹ የባልደራስ አመራቾች በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ ከመጠየቅ ባሻገር «የፖለቲካ ድርጅቶችና አባላት ላይ የሚካሄድ ኢፍትሃዊ ተጽዕኖ እና መገለል እንዲቆም፣ ህገ መንግስቱ እና የጎሳ ፌደራሊዝም ከሃገሪቱ እንዲወገድ እና ዘላቂ ህልውና በሚያስጠብቅ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርአት እንዲተካ» ሲሉ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ምሁራኑና የመብት ተሟጋቾች በማንነት ላይ መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በላኩት ግልጽ ደብዳቤ አካተዋል።