>

ባልደራስ ሆይ - ከፌዝ ፖለቲካቸው ልምድ ውሰድ... ኦነግን ላድን ነው፤  ድንጋይም ፍልጥም... እይዛለሁ በላቸው !!! (ጌታቸው ሽፈራው)

ባልደራስ ሆይ – ከፌዝ ፖለቲካቸው ልምድ ውሰድ… ኦነግን ላድን ነው፤  ድንጋይም ፍልጥም… እይዛለሁ በላቸው !!!
ጌታቸው ሽፈራው

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን ባልደራስ አዲስ አበባ ላይ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና የለውም ብሎታል። ስህተቱ የባልደራስ ነው። ለምን ትሳሳታለህ ባልደራስ?  በዚህ ወቅት ኦሮሚያ ውስጥ በየቀኑ ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣልኮ። እያየን ነው። ባልደራስ ሆይ ልምድ ውሰድ እንጅ?
እየውልህ ባልደራስ! ከተማ ተመዘበረ ተብሎ ድምፅ ለማሰማት ሰልፍ አይወጣም፣ ንፁሃን ተፈናቀሉ ብሎ ድምፃቸው ለመሆን ሰልፍ መውጣት ወንጀል ሆኗል።  መንግስት ሲወሰልት አደብ ለማስገዛት ሰልፍ መውጣት ተከልክሏል። የማይፈቀድ ነገር አትጠይቅማ! ሰላማዊ ሰልፍ መብት መሆኑም ተዘንግቷል።  ለምን በኦሮሚያ ከተሞች በየሳምንቱ ከሚደረጉት ሰልፎች ልምድ አትወስዱም ግን? ልምድኮ ጥሩ ነው!
ምን ታደርጋለህ መሰለህ ባልደራስ?  የሰልፉን አላማ የሚገለፅበት ክፍል አለ አይደል? አዎ፣ እዛ  ላይ “ኦነግን ለማደን” ትለዋለህ። በሕግ ከሚታወቀው ሰልፍ በተቃራኒ ዱላም ድንጋይም መንገድን በድንጋይ የሚዘጋ ሰውም ይዞ መገኘት አይከለክልም ይህኛው። ፌሮም፣ መጥረቢያም፣ ቆንጨራም እንይዛለን ብለን የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ወረቀቱ ላይ ታክልበታለህ። ከፈለክ ሰልፉን እውቅና የሚሰጡ ሰዎች ድምፅ አልባም ተተኳሽም የሚጨመር  ከሆነ ይነግሩሃል።  ችግሩ እዚህ ላይ ነው። ምቾት ያበዙብሃል። የሰልፉ ጉዳይ የሚያገባው ባለስልጣን ታዲያ  “ምን አልባት መሳርያ ካነሳችሁ ሰልፍ ከተደረገባቸው አካባቢዎች እንዲያውሷችሁ ማድረግም ይቻላል። አሊያም ፖሊስ በተለያየ ጊዜ ቀምቶ ያስቀመጣቸው መሰል መሳርያዎች አይጠፉም።” ብሎ ያለ ቅጥ ቁጭ ብድግ ብሎ ይተባበርሃል። ለተከታታይ ድራማ መሳርያ ብቻ ሳይሆን ከእነ ሙሉ ልብሱኮ ያውሱታል። አንድ ቀን ለምታደርገው ሰልፍ አስመርጠው ይሰጡሃል። ያው የኦሮሚያ ከተሞች ላይ እንዳየኸው ኦነግን የሚያድኑት ቅጠል ለቅመው የሚሸጡት እናቶች ወደሚገቡባቸው የከተማው ጓሮ ደኖች ገብቶ ሲርመሰመስ ነበር። ባልደራስ ሰልፍ ሲጠራም ከሆቴሎቹ በስተጀርባ ባሉት ጫካዎች ሻይ ቡና ልበል ብሎ ተመሳስሎ ገብቶ ተደብቆ ይሆናል ትለዋለህ። ቤተ ክርስትያንና መስጊድ አካባቢ ተደብቆ ይሆናል ትለዋለህ። መርካቶ አካባቢ፣ ፒያሳም አካባቢ ተደብቆ ይሆናል ብለህ ትነግረዋለህ። በቅርቡ የተሰሩት የአዲስ አበባ ፓርኮች ውስጥ ተደብቆ ይሆናል ማለት አለብህ! ተበላሽቶ የቆመ ባስ ውስጥ ሳይቀር ገብተህ መፈለግ አለብህ። ይህን የሰልፍ አላማ ያየ አካል ራሱ ሚዲያዎችን ይጠራልሃል። ተንጋግተው ይመጣሉ። ባይገኙ እንኳ ሳይዘገዩ ከሌላው ወስደው ይሰሩልሃል።
ቀልድ እንጅ ባልደራስ! በዚህ ፌዘኛ ፖለቲካ  ነገሩን የምር አታድርገው። ማን ሊሰማህ? የቀልድ ነው ፖለቲካው። ሰልፍ የሚፈቀደው እንዲህ እየቀለድክ ነው። አየህ ኦነግን ለሕግ ሊያቀርቡ ሰልጥነው ከኦነግ ጋር ከሺህ  በላይ  ፖሊስ ተባባሩ የተባለውኮ ኦነግን ለማደን የወጡትን ሰልፈኞች ከፊት ሆኖ የሚመራውን ጭምር ነው።  ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ቆንጨራ ይዘው ኦነግን ሱቅ በደረቴ በስተጀርባ ካርቶን ሳይቀር እየገለጡ የሚፈልጉትን ወጣቶች  ከፊት ሆኖ የሚመራቸውን በርካታ ፖሊስ አላየሁም እንዳትል?  አንተ አዲስ አበባ ላይ ኦነግን ልፈልገው ብትል ከፊት ሆኖ የሚመራልህ አሁን ሰልፍ ተከለከለ ብሎ መንገድ የሚዘጋብህ ጭምር ነው። ሰልፉ ተከልክሏ ብሎ በገፁ የፃፈብህ ሳይቀር በአራት ኪሎ ኦነግን እያደንክ የወላክበትን ፎቶ አብዝቶ ይለጥፍልህ ነበር። ችግሩ ፖለቲካው አልገባህም። ቀልድ አታውቅም። ቀልድ ዝም ብለህ። ሰልፍ በሕግ የተቀመጠ መብት መሆኑ መቅረቱን ዘንግተኸዋል። አንተንጋማ ባልደራስ! ትቀልድ እንደሆነ ቀልድ! ኦነግን አድነው ዝም ብለህ! ከፈለክ  በቀጣዩ ቀን ደግሞ “ጁንታውን ለማደን” ብለህ የሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ደብዳቤ አስገባ። ክላሽ ሳይቀር ይሰጡሃል!
ቶሎ በል ባልደራስ! ከቀልድ ፖለቲካው ልምድ ውሰድ! ሰላማዊ ሰልፍ አይፈቀድም። ቆንጮራ፣ ዱላ ምናምን ያለውን ነው የሚፈቅዱት። ኦሮሚያ ክልል  ሲፈቅዱ አላየህም ወይ?
Filed in: Amharic