>
5:13 pm - Tuesday April 18, 2705

"... ነፃነት ያላቸው ስለባርነት አያስቡም ሆዳቸው የሞላም ስለረሃብ አይነጋገሩም...!!!" መላኩ በያን 

“… ነፃነት ያላቸው ስለባርነት አያስቡም ሆዳቸው የሞላም ስለረሃብ አይነጋገሩም…!!!”
መላኩ በያን 

በብዙዎች ዘንድ ያልታወቀ፤ ብዙ ሊባልለት ሲገባ ምንም ያልተነገረለት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ዶክተር መላኩ በያን
   በ1892 ዓ.ም  ሚያዝያ 21 ቀን ወሎ ክፍለሀገር ተወለደ። በልጅነቱ ቤተሠቦቹ ወደ ሐረር ሲሔዱ ይዘውት ሔደው በራስ መኮንን ግቢ ትምህርት ሲማር አደገ።
    በ1913 ዓ.ም 21 ዓመት በሆነው ጊዜም ለህክምና ትምህርት ከሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት ጋር ወደ ሕንድ ሀገር ሔደ። በሕንድ ሀገር ያለው ትምህርት ስላልተስማማውና በተለይም አብራው ለትምህርት የሄደችው ሴት በመሞቷ ምክንያት የሕንድ ኑሮው አላስደሠተውም።
   በ1914 ሚያዝያ ወር ከቀሪዎቹ ሁለት ወንድ ጓደኞቹ ጋር በመርከብ በመሳፈር ወደ አሜሪካ ተጓዘ።ከዚያ እንደደረሰም ማሪየታ ኮሌጅ ገባ። በ1918 መላኩ የከፍተኛ ትምህርት ዲግሪውን ሲያገኝ አፍሮ አሜሪካን የሚባለው ጋዜጣ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በመስከረም 14,1925 ባወጣው ዕትሙ “… በአሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያዊ ዲግሪ ተሠጠ።…” በማለት ፅፎለታል።
   መላኩ በ1920 ኮሎምበስ ውስጥ ኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርስቲ ገባ እዚያም አንድ ዓመት ከተማረ በኋላ ወደ ሃዋርድ ዩኒቨርስቲ ዞሮ የሕክምና ትምህርቱን ቀጠለ።
  በሰኔ ወር 1928 ዓ.ም ከሃዋርድ ዩኒቨርስቲ መላኩ በያን በዶክተርነት ተመረቀ። ያ ዘመን ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የከፈተችበት ጊዜ ስለነበር ዶክተር መላኩ በያን አገሩን ለመርዳት በተመረቀ ወር ሳይሞላው በሐምሌ ወር ወደ ሀገሩ ጉዞ ጀመረ።
  አዲስ አበባም እንደደረሰ ለጊዜው በአሜሪካ ሚሽን ሆስፒታል ስራ ቢጀምርም ጦርነቱ እየተባባሠ በመሄዱ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ተመዝግቦ ወደ ኦጋዴን ዘመተ።
  የኢጣልያ ፋሺስት አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ መላኩ በያን ወደ እንግሊዝ በዚያም አድርጎ ወደ አሜሪካን አገር ሔደ።
ከዚያም ሆኖ ስለ ኢትዮጵያ በግፍ መወረር ራሱ ባቋቋመው ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ እየሠበከ ርዳታ ይለምን ጀመር። በግብፅ በጂቡቲ በሱዳንና በሌላም ቦታ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለመርዳት ” ምኒልክ ክበብ ” የተባለ ድርጅትም በማቋቋም ገንዘብ ለማግኘት ሲል የኢትዮጵያን ምስል ያለበትን ቴምብር እያሳተመ በእያንዳንዱ ሠው ቤት እየዞረ ይሸጥ ነበር።
  መላኩ በያን እያሳተመ ስለሚሸጠው ቴምብር የአንድ ጋዜጣ ወኪል ላቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ “… ነፃነት ያላቸው ስለባርነት አያስቡም ሆዳቸው የሞላም ስለረሃብ አይነጋገሩም በማለት መልሶለታል።
  ይህ በእንዲህ እንዳለ ማህበሩን በማስፋት በላቲን አሜሪካና በዌስት ኢንዲስ የማህበሩን 22 ቅርንጫፎች አቋቁሞ ስለኢትዮጵያ የለፋ ወጣት ነበረ።
  በነሐሴ ወር 1931 ዓ.ም ታመመ። ነሐሴ ሲያልቅም ህመሙ ተሻለውና ያንኑ የትግል ስራውን ጀመረ። እንደገና በመጋቢት ወር 1932 በኒሞኒያ ህመም ተለከፈ። በጠና ስለታመመም ሮክላንድ ደሴት ሆስፒታል ገባ። በሚያዝያ 26 ቀን 1932 ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
  በአሜሪካ እና በሌላም አገር ያሉ ታላላቅ ጋዜጦች የመላኩን መሞት በታላቅ ኀዘን ፃፉለት። አገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ የለፋላትን ኢትዮጵያ ነፃነት ሊመለስ አንድ ዓመት ሲቀረው በአርባ አመት እድሜው ተቀጨ።
Filed in: Amharic