>

እናት ኢትዮጵያ...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

እናት ኢትዮጵያ…!!!

አሰፋ ሀይሉ

 

ይህ ዳን ኮኔል የተባለ የወቅቱ ወጣት አሜሪካዊ ምስጢራዊ ሰው – የኤርትራን ከኢትዮጵያ የመገንጠል ሂደት – እነርሱ ‹‹የነፃነት ትግል›› ብለው የሚጠሩትን – ከሥር ከመሠረቱ ጀምሮ – ራሳቸው ፈጣሪዎቹና ተዋናዮቹ የሰጡትን ምስክርነት፣ በታሪክ ተወዳዳሪ በማይገኝለት የኢትዮጵያ የውድቀትና የውድመት አፋፍ ላይ በቦታው ተገኝቶ፣ በጦርነት እሳቶች መሐል ተሹለክልኮ፣ ከሻዕብያና ከሌሎች የኤርትራ ታጣቂ ግንባሮች ጋር ባሳለፋቸው ወቅቶች ያያቸውን፣ የታዘባቸውንና የሰማቸውን ነገሮች ሁሉ አንድም ሳይቀር ልቅም አድርጎ ለታሪክ መታሰቢያ ያኖረበት መጽሐፍ ነው፡፡
አዲስ ታሪካቸውን ለማፃፍና ለማያውቃቸው የዓለም ሕዝብ ለማስተዋወቅ ያለሙት የኤርትራ ‹‹ነፃ አውጪዎች›› ይህን መጽሐፍ በደራሲው ተጽፎ እንዲወጣላቸው ከ60ዎቹ ጀምረው – የመገንጠል ጉዟቸውን በድል እስካጠናቀቁበት እስከ 80ዎቹ ድረስ ያደረጉት የታሪክ፣ የገንዘብ፣ የቁሳቁስና ለደራሲው ሁኔታዎችን የማመቻቸት እገዛ ሁሉ በከንቱ የቀረም አይመስልም፡፡ ደራሲው የመጽሐፉን መታሰቢያነት ‹‹ለነፃነታቸው ሲዋጉ ለተሰዉት የኤርትራ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሁንልኝ›› ሲል በአደራ ያስረክባቸዋል፡፡
ደራሲው መጽሐፉ ተጀምሮ እስኪጨረስ ‹‹ጠላት›› እያለ የሚናገረው እኛን ኢትዮጵያውያንን እና የኢትዮጵያን መንግሥት ሠራዊቶች ነው፡፡ የአንድ ወገን አርበኝነቱና ውግንናው ለጉድ ነው፡፡ በተዋጊዎቹ ከኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በየዕለቱ ስለሚዘረፉት ህልቆ ወ መሳፍርት የሌላቸው ንብረቶች፣ የጦር መሣሪያዎች፣ የጤና፣ የምግብ፣ የመሠረተ ልማት ቁሳቁሶች ሁሉ ደራሲው ያለው የጀብደኝነትና የድጋፍ አተያይ እጅግ ይገርማል፡፡ የገንጣዮቹን ሥርቆት፣ ግድያ፣ ዝርፊያ፣ እገታና ደም ማፋሰስ ሁሉ ደራሲው እንደ ተለመደ የዕለት ተዕለት የነፃነት ትግል ግብዓት ቆጥሮታል፡፡ ከአንድ ሠላም ከሰፈነበት የምዕራቡ ዓለም – ከአሜሪካ – ምንም እንኳ የቱንም ያህል የአንድ ወገን ተልዕኮ አንግቦ ቢመጣ – እንዴት እነዚህን ነገሮች እንደ ቀላል የፍጆታ ዕቃዎች ሸመታ እንደቆጠራቸው ሲታይ አንባቢን ማስገረሙ አይቀርም፡፡
ደራሲው በአካል የተገኘባቸውን የጦርነት ውሎዎችና ለረዥም-ጉዞ-የታለሙ የጦር ዝግጅቶችና እንቅስቃሴዎች – ከአፋ እስከ ናቅፋ፣ ከከረን እስከ ተሰነይ፣ ከአፋቤት እስከ አዲ ቋላ፣ ከአስመራ እስከ ምፅዋ፣ ከባርካ እስከ ከሰላ፣ ከባሬንቱ እስከ ሰናሃይት፣ ከአቆርዳት እስከ አሰብ፣ ከዴካማሬ እስከ ሂርጊጎ፣ ከቆላ እስከ ደጋ ያለውን ረዥሙን የክህደትና የሸፍጥ፣ የጭቆናና የሥቃይ፣ የዝርፊያና የደም መፋሰስ፣ የነፃነትና ሀገር የመገንጠል ታሪክ… አንድም ሳይቀር በመጽሐፉ መዝግቦ አኑሮታል፡፡
ደራሲው ለመጀመሪያ ጊዜ በ1967 ላይ አዲስ አበባ መጥቶ፣ በጭነት መኪናና በአውቶብስ ተሳፍሮ ወደ ትግራይ ያቀናበት መንገድ፣ መቀሌን፣ አድዋን፣ አዲግራትን፣ ዛላንበሳን፣ ራማን አልፎ ወደ አስመራ የገባበት መንገድ፣ አስመራ ላይ የገጠመው ልክ የበዓሉ ግርማዋን የኦሮማይ ገጸ ባህርይ ፊያሜታ ጊላይን የመሰለች ነቢያት የተባለች እውነተኛ የሻዕቢያ ምስጢራዊ አስገዳይ ስኳድ አባል – እስራኤል ሀገር የሠለጠነውን የኢትዮጵያ ጦርሠራዊት አዛዥ ኮሎኔል ቢሻውን ለወራት በውበቷ አማልላና አጥምዳ በመጨረሻ በአስመራ ዳውንታውን በሚገኘው ‹‹ከባቢ ባር›› በራፍ ላይ እንዴት ለሻዕቢያ የከተማ ገዳይ ኮማንዶዎች ጥይት አሳልፋ እንደሰጠችው ያየውን የሰማውን እማኝነት ያስቀምጥልናል፡፡
ደራሲው ከበዓሉ ቀድማ ፊያሜታን በአካል የተወነችና ሻዕቢያዊ ግዳጇን በብቃት የተወጣች ይህች አደገኛ ሴት ኢትዮጵያዊውን የደህንነት ሹም ኮሎኔል ቢሻውን በአስመራ ባስገደለች በዓመቱ በኤርትራ ሳህል በረሃዎች በተቀላቀለችበት የሻዕቢያ የትግል አምባ አግኝቷት ስለተፈጠረው ጉዳይ ቢጠይቃት ለመናገር ፈቃደኛ እንዳልሆነችለት፣ ነገር ግን ለኤርትራ መገንጠል ሁለት ዓመት ሲቀረው – ሌላ ኢንግቦርግ ኤሊያሰን የተባለ ደራሲ ኖርዌይ ውስጥ አግኝቷት ያደረገላትን ሙሉ ቃለመጠይቅ እንዳገኘው ገልጾ ዝርዝር ታሪኳን ያወጋናል፡፡
ከኮሎኔል ቢሻው በኤርትራ ነፃነት ግንባር (ገና ሻዕቢያ ሳይመሰረት የነበረው) ስኳዶች ከተገደለ በኋላ በአስመራ ዳውንታውን ላይ ስለወረደው የጅምላ የበቀል ግድያና እልቂትም ይተርክልናል፡፡ ይህቺን ነቢያት የምትባል ሴት እያሰከብኩ ፍቅር ከግዳይዋ ያናጠባትን ፊያሜታን መርሳት አልቻልኩም፡፡ ምናልባት ኋላ በቀይ ኮከብ ዘመቻ በዓሉ ግርማ የጻፈልን የፊያሜታ የተቀባባ ታሪክ የዚህች የነቢያት እውነተኛ ታሪክ ይሆን? የሚል ቅዠት የመሰለ የድርሰትና የእውኑ ዓለም ግጥምጥሞሽ ሀሳብ በጨረፍ ዳስሶኝ ሄደ፡፡
ይህ ደራሲ – ዳን ኮኔል – ለመጀመሪያ ጊዜ ኤርትራ ሄዶ ሲመለስ – ንጉሡን ከሥልጣን ያወረደችው ወታደራዊት ኢትዮጵያ ከኤርትራ ተገንጣይ ቡድኖች ጋር ሠላማዊ ድርድር ለማድረግ ደፋ ቀና የምትልበት ወቅት ነበር፡፡ ነገር ግን ደራሲው ከድርድሩ ባሻገር ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ሚሊሻዎችን በስፋት እየመለመለች፣ ለስንቅ የሚሆን ድርቆሽና ኮቾሮ በከፍተኛ መጠን እያዘጋጀች፣ መደበኛ ሠራዊቶቿንና የጦር መሣሪያዎቿን ወደ ተለያዩ የጦር ማዕከሎች እያሰባሰበች የነበረችበትን ሁኔታ በአካል ከአዲስ አበባ እስከ ኤርትራ ድረስ ተዘዋውሮ ሰልሎ በመገምገም – የቀይ ኮከብ ጥሪ ክተት ገና ሳይታወጅ አስቀድሞ – ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ‹‹ኢትዮጵያ በኤርትራ ተገንጣዮች ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ልታካሂድ ዝግጅት እያደረገች እንደሆነ›› መረጃ የሰጠና፣ ያንንም ኢትዮጵያዊ ምስጢር በዋሺንግተን ፖስትና ኒውዮርክ ታይምስ፣ እና ሌሎች የተለያዩ የዩኤስ አሜሪካ ተነባቢ ጋዜጦች የፊት ገጾች ላይ ዜና ተደርጎ እንዲወጣ ያደረገ የመጀመሪያው ሰው መሆኑን ምንጭ እያጣቀሰ ይመሰክራል ስለራሱ፡፡
በእርግጥ ደራሲው ወደ ኤርትራ ነጻነት ግንባርና፣ ወደ ኤርትራ ህዝባዊ ነጻነት ግንባር (ሻዕቢያ) ጥብቅ ምስጢራዊ የጦር ሰፈሮች ዘልቆ እንዲገባና አብሯቸው እየኖረ የፈለገውን ነገር እንዲመለከትና በማስታወሻው እንዲያሰፍር የተፈቀደለት በዚያ መንገድ ታማኝነቱን በማረጋገጡና በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በተሰጠው ልዩ ተልዕኮ የተነሳ ይመስላል፡፡ ደራሲው ከአስመራ አዲስ አበባ ተመልሶ ጥቂት ይቆይና ሻዕቢያን ጨምሮ የኤርትራን ታጣቂ ቡድኖች ሁሉ በሀገሯ መጠለያ፣ ስንቅና ትጥቅ – ወታደሮች ጭምር – ሰጥታ ወዳስጠለለችው ወደ ሱዳን ይበራል፡፡ ከዚያ ደግሞ ይነሳና በድጋሚ ወደ ኤርትራ ይነጉዳል፡፡
ይህን የዳን ኮኔልን መጽሐፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው አንድ ቀን በስፋትና በዝርዝር እንደምመለስበት እርግጠኛ ነኝ፡፡ ግን ይህን በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ዘመን እ.ኤ.አ. በ1952 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድጅርት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ቁጥር 390 አማካይነት ኢትዮጵያና ኤርትራ በፌዴሬሽን እንዲዋሃዱ ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ የተከናወነውን በኢትዮጵያ ላይ የማሸመቅ ታሪክ በኤርትራ ተገንጣዮቹ ወገን በመሆን የተጻፈውን የሰቆቃ ታሪክ ከመጽሐፉ እያነበብኩ አሁንም፣ አሁንም፣ አሁንም… ሺህ ጊዜ.. መልሶ መላልሶ እየደጋገመ የሚመጣብኝ ሀሳብ የዚህች ኢትዮጵያ የሚሏት አፍሪካዊት የነፃነት ምድር ላይ ከሩቅም፣ ከቅርብም የተሰለፈባት የጠላት መዓት ነው፡፡ እጅግ ይገርመኛል በጣም ይህ ነገር፡፡
ቻይና ኢሳያስንና ተገንጣይ ጓዶቹን እንዴት ባለ መልኩ አሰልጥናና አስታጥቃ በኢትዮጵያ ላይ እንዳሰማራቻቸው ይነግረናል ደራሲው፡፡ በነገራችን ላይ ደራሲው ኢሳያስ አፈወርቂን በአስመራ ልዑል መኮንን ሃይስኩል እንዴት ባለ መልኩ እንደተማረ፣ ከዚያ ወደ አዲስ አበባው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ እንዴት ኢንጂነሪንግ ሊያጠና እንደመጣ፣ እና ያንን አቋርጦ እንዴት ወደ ሱዳን ከሰላ ሄዶ የኤርትራ ነጻነት ግንባርን (ኢኤልኤፍን) እንደተቀላቀለ ሲነግረን – ኢሳያስ አፈወርቂ በቀኝ ትከሻው ላይ እስከተነቀሰው ‹‹E›› የሚል የኤርትራ ነጻነት ግንባር መታሰቢያ ንቅሳቱ ጭምር ነው አንጠርጥሮ የሚነግረንና የሚያውቀው፡፡
ሁሉንም እንደዚያው ነው የሚያውቃቸው ደራሲው፡፡ ለምሳሌ ስለ ስብሃት ኤፍሬም ሲናገር የጣልያን ሆስፒታል አስተዳዳሪ ከነነበሩት አባቱ፣ ከቃኘው ሻለቃ በሚመጡ የአሜሪካ መምህሮች ስለሚዘወረውና ስብሃት ስለተማረበት የአስመራው ሉተራን ትምህርት ቤት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ትምህርቱን ትቶ እንዴት ሻዕቢያን እንደተቀላቀለ፣ በጦር ልምምድ ወቅት በተከሰተ አጋጣሚ ስለረገፉት የፊት ጥርሶቹ ጭምር እያነሳ ነው የሚተርከው ደራሲው፡፡ ስለ ሌሎቹም ስለ እያንዳንዳቸው ያለው መረጃና ዕውቀት የሚገርም ነው በእውነቱ፡፡
የ1950ዎቹን የኤርትራ የኤርትራ ነጻነት ንቅናቄ (ማህበር ሸዋተን – ወይም ኢኤልኤምን) በካይሮ ስለመሠረቱት እነ ኢድሪስ ሞሀመድ አደም ይተርካል፣ የቀድሞው የኤርትራ ሙስሊም ሊግ መሥራች ኢድሪስ ሃሚድ አወቴ – እንዴት አድርጎ የኤርትራ ነፃነት ግንባርን (ኢኤልኤፍ) እንደመሠረተ፣ እንዴት ሱዳን ዘጠኝ የታጠቁ ወታደራዊ መኮንኖቿንና ወታደሮቿን ለነጻነት ግንባሩ እንደሰጠች፣ ኢድሪስ ሃሚድ አወቴ ሲሞት እርሱን ተክቶ የኤርትራ ነጻነት ግንባርን ስለመራውና በቅጽል ስሙ ‹‹አቡ ጣያራ›› እየተባለ ስለሚጠራው የኤርትራ ነፃ አውጪ መሪ ሱዳናዊው የጦር መኮንን ሞሀመድ ኦማር አብደላ ታሪክ፣  ልክ እንደ ቆሎ ጓደኛቸው ነው እያንዳንዷን ዝርዝር ነገራቸውን ከታሪኩ ተዋናዮች አንደበት ተቀብሎ፣ መርምሮ፣ አጥንቶ ከሽኖ የሚያቀርብልን፡፡
በምጽዋ ጠረፋማ አካባቢ በአስተማሪነት ሲያገለግል ስለነበረውና የኤርትራ ነጻነት ግንባር መሪ፣ የኤርትራን የመገንጠል እንቅስቃሴ ከአረብ ሀገራት ጋር ስላስተሳሰረው፣ የሻዕቢያና የሌሎችም ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ዋነኛ አስተባባሪና የውጭ ግንኙነት ሰው ስለነበረው ኦስማን ሳሌህ ሳቤም ደጋግሞ ነው የሚነግረን ይህ ደራሲ፡፡ በንጉሡ ዘመን አፍቃሬ-ኢትዮጵያ የነበረው የኤርትራ መማክርት ጉባዔ ፕሬዚደንት ሃሚድ ፋራጅ – እንዴት ኢትዮጵያን ክዶ ለኤርትራ ነጻነት ግንባር ተሰልፎ በመሪነት እንደተዋጋና የኤርትራውን ገዢ የእነ ጄኔራል አብይን ግድያ እንዳስፈጸመ፣ በአቆርዳት 22 ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ያለቁበትንና ከ120 በላይ የቆሰሉበትን ከፍተኛ የፈንጂ ጥቃት እንዴት እንዳቀነባበረ ይተርክልናል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1965 በሱዳን ከሰላ ላይ ስለተቋቋመው የእርትራ ነፃነት ግንባር ላዕላይ ምክርቤትና – አልጄሪያ በፈረንሣይ ቅኝ ገዢዎች ላይ የምታካሂደውን ፅንፍ የረገጠ ህዝባዊ የትጥቅ ትግል በሞዴልነት ያስቀመጠ ፀረ-ኢትዮጵያ የክተት አዋጅ እንዴት እንደተላለፈ ይነግረናል፡፡
ከእስራኤል-አረብ ጦርነት መፈንዳትና በእስራኤልና በምዕራብ አጋሮቿ አሸናፊነት መጠናቀቅ ተከትሎ የኤርትራ ተገንጣዮች በሙሉ እንዴት የፍልስጥዔም ህዝባዊ ግንባርን ደግፈው፣ በፀረ-ኢምፔሪያሊስትነት (በፀረ-አሜሪካነት) እና በፀረ-እስራኤልነት (አንታይ-ዛዮኒስት) እንደተሰለፉ፣ እና በዚህ አሰላለፋቸው አማካይነት ከሩቅና ቅርብ የአረብ ሀገራት ይሰጣቸው ስለነበረው የገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ የወታደራዊ ሥልጠና፣ የመሣሪያና የሌሎች ድጋፎች ይነግረናል ደራሲው፡፡ የህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) አመሠራረትም ልክ የፍልስጥዔሙን ነፃ አውጪ ህዝባዊ ግንባር፣ የኦማን ነጻ አውጪ ህዝባዊ ግንባር፣ የባህሬይን ነጻ አውጪ ህዝባዊ ግንባር፣ ወዘተ ተከትሎ በዚያው ዓይነት መንገድ የተቋቋመ መሆኑን ያሳየናል ደራሲው፡፡
የኤርትራ ነፃነት ግንባር በፀረ-ኢትዮጵያው ጦርነትና የሽምቅ ውጊያ እና የተለያዩ የሽብር ተግባራት ላይ ተሠማርተው ህይወታቸው ለምታልፍ የግንባሩ አባላት ቤተሰቦች የኑሮ መቆያ የሚሆን የማቋቋሚያ ፈንድ ዘርግቶ እንደነበር ይነግረናል፡፡ የሟችና የተዋጊ ቤተሰቦችን በካምፕ አስጠልሎ የሚረዳ፣ የሞተባቸውን ሃላፊነት የሚወስድ፣ አካላቸው የተጎዱትን በኑሮ የሚያስተዳድር ቱባ የገንዘብ አቅም ያለው ድርጅት ተቋቁመዋል በኤርትራ፡፡ እነዚህ ሁሉ ልክ የፍልስጥዔምና ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ‹‹አሸባሪ›› ድርጅቶች ለአባሎቻቸው የሚያደርጓቸው መሆናቸውን ይጠቁመናል ደራሲው፡፡
ኢትዮጵያን ለሚወጉት የኤርትራ ገንጣይ ድርጅቶች የገንዘብና የጦር መሣሪያ እርዳታ ከሱዳን፣ ሶማሊያ፣ አልጄሪያ፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሶሪያ፣ ከያሲር አራፋቱ የፍልስጥኤም ነፃ አውጪ ይጎርፍላቸው እንደነበር ደራሲው በግልጽ የሚመሰክረው የታሪክ እውነት ነው፡፡ በወቅቱ እንደ ካርሎስ ቀበሮው የመሳሰሉት ዓለማቀፍ ፀረ-ፅዮናዊ አሸባሪዎች ጭምር በአባልነት ይንቀሳቀሱበት የነበረውና በርካታ የአረቦችን ካፒታልና የሰው ኃይል አስተባብሮ ፍልስጥኤሞችንና አረቦችን ነጻ አወጣለሁ ብሎ በደቡብ የመን ዋና መቀመጫውን አድርጎ ይንቀሳቀስ የነበረው የአረብ ናሽናል ሙቭመንት (ኤኤንኤም) ዋነኛ የኤርትራውያኑ አጋር በመሆን ከፍተኛ ውለታ እንደዋለላቸውም ሳይዘግብ አያልፈውም ደራሲው፡፡
የገረመኝ የኩባ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ረድታ ከሶማሊያ ወረራ ያስጣለችው ኩባ – ቀደም ብላ ግን ከኢትዮጵያ የባህር ኃይል ከድቶ የኢኤልኤፍ (የኤርትራ ነፃነት ግንባር) ዋና የጦር አዛዥ ለመሆን የበቃውን (እና ኋላ በእኛ በ70ዎቹ መጨረሻ ግድም በኢትዮጵያ ሠራዊት በጦርግንባር የተገደለውን) ኢብራሂም አፋን ባህር አሻግራ ወታደራዊ ሥልጠና አሰልጥና ጦር ሸልማና አስታጥቃ በኢትዮጵያ ላይ ያሰማራች ሀገር ሆና እናገኛታለን፡፡
የቻይናማ የጉድ ነው! በካይሮ የሃይስኩል ትምህርቱን ጨርሶ የሁለተኛ ዓመት የአርኪቴክቸርና ማቴማቲክስ የኮሌጅ ትምህርቱን አቋርጦ ኢኤልኤፍን የተቀላቀለውና ኋላ የሻዕቢያ ዋና ፀሐፊ የነበረውን ሮመዳን ሞሀመድ ኑርን – እና ምክትል ዋና ፀሐፊውን ኢሣያስ አፈወርቂን – ደግሞ  ሀገሯ ወስዳ አሠልጥና አስታጥቃ የላከችብን ቻይና ነበረች፡፡ ሮመዳን በሶርያም ሄዶ ተመሣሣይ ወታደራዊ ሥልጠናዎችን ወስዶ የተመሰለ እጅግ አደገኛ ፀረ-ኢትዮጵያ ሸማቂ ነበረ፡፡ ሌሎችንም ብዙዎችን አሠልጥናብናለች ቻይና፡፡ ይህን ለመቀልበስ ኋላ ባለቀ ሰዓት ጃንሆይ ቻይና ድረስ ሄደው ማኦን መለማመጥና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመመሥረት ተገደው እንደነበረ ደራሲው ባይነግረንም የምናስታውሰው የኢትዮጵያችን ታሪክ ነው፡፡
የሻዕቢያ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ የነበረውን አል አሚን ሞሀመድ ሰዒድን ደግሞ ሀገሯ ወስዳ ለ6ወራት ወታደራዊ ሥልጠና ሰጥታ በኢትዮጵያ ላይ ያሰማራችው ሶሪያ ነበረች፡፡ ሳዑዲም አሠልጠናዋለች፡፡ ከነጻነት በኋላ የኤርትራ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው አሊ ሰይድ አብደላ፣ የሻዕቢያ የፖለቲካ ክንፍ ኃላፊ የነበረው – እና ከተገነጠሉ በኋላ – የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር የሆነው ሃይሌ ወልደተንሳይ፣ ኮማንዶዎችን እየመራ አስመራንና ምጽዋን ሊቆጣጠር ተቃርቦ የነበረው ደፋርና ጀብደኛ የሻዕቢያ የጦር መሪ እነ ኤርሚያስ ደበሳይ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተካሄደውን የመጨረሻ ወታደራዊ ዘመቻዎች የመሩት እነ መስፍን ሀጎስ፣ እና በቅጽል ስሙ ‹‹ሸሪፎ›› እየተባለ የሚጠራው (እና የኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚ/ር የተደረገው) ማህመድ አህሙድ ማህሙድ ከእነዚህ መካከል ይገኙበታል፡፡
የግራ ዘመም አፍቃሬ-ሶቭየት የሌበር ፓርቲ የመሰረቱት – እና የኤርትራ ነጻነት ግንባርን የተቀላቀሉት – እነ ባዜን ያሲን፣ አብደላ ሱሌማን፣ ኢብራሂም ቶቲል፣ እና በቀኃሥ ዘመን የኤርትራ የመጀመሪያ ገዢ የነበሩት የተድላ ባይሩ ልጅ ህሩይ ተድላ፣ ወዘተ በተለያዩ የአረብና ሶሻሊስት ሀገራት እየሄዱ ኢትዮጵያን የሚወጉበትን የወታደራዊ ሥልጠና፣ የፋይናንሺያል፣ የሎጂስቲክና ሌሎች እርዳታዎችን ያገኙ የሻዕቢያ የቁርጥ ቀን ሰዎች ናቸው፡፡ ኋላ አንዳንዶቹ በባህር ማዶ ሆነው የኤርትራን የመገንጠል እንቅስቃሴ በዓለም ሀገራት በማስተባበር የተሰማሩ ነበሩ፡፡
የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ዳን ኮኔል ከሚነግረን ነገሮች ያልዘነጋሁት – የሰሜን አሜሪካ ተማሪዎች ህብረት ጉዳይ ነው፡፡ የሰሜን አሜሪካ የኤርትራ ነፃነት ደጋፊዎች ማህበር – ይባል የነበረው – ስሙን ቀይሮ በሰሜን አሜሪካ የኤርትራ ተማሪዎች ማህበር በመሠኘት እንቅስቃሴውን የቀጠለ የፕሮፓጋንዳና ድጋፍ ማሰባሰቢያ ማህበር ነው፡፡ በጣም የገረመኝ ነገር ይህን ማህበር በመደገፍ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት አማካይነት ይወጡ የነበሩት ፀረ-ኢትዮጵያ (እና አፍቃሬ-ተገንጣይ) ጽሑፎች ናቸው፡፡
አረቦቹ፣ አሜሪካኖቹ፣ ኩባና ቻይናዎቹ ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ መሰለፋቸው ሳያንስ – የኢትዮጵያ ተማሪዎች ዩኒየን ከሰሜን አሜሪካ ሆኖ የኤርትራን ተማሪዎች የነጻነት ትግል እየደገፈ ፕሮፓጋንዳ ይሠራላቸው ነበር፡፡ ግርም አለኝ፡፡ እና ብዙ ጊዜ ባሳለፍነው ሥርዓት በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ስሙ ተደጋግሞ የሚጠራለትን የእኛውን ጉድ (የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሬን) ፕ/ር አንድርያስ እሸቴን አስታወስኩት በአግራሞትና በሀዘን፡፡ ገረመኝ፡፡ የነገሮች ግጥምጥሞሽ፡፡ ኋላ ፕ/ር አንድርያስ በኤርትራ ‹‹ነፃነት›› አከባበር በዓል ላይ የተጋበዘበት አኳኋን፣ ከወያኔ መሪዎች (ከእነ መለስ፣ ክንፈና ሃየሎም ከመሳሰሉት) ጋር የነበረው እጅና ጓንትነት፣ ወዘተ.፡፡ ጉድ እያልኩ ከመቀጠል ውጭ አማራጭ አልነበረኝም፡፡
መጽሐፉ በጋሄር እና ዳአባት በመሳሰሉት የኤርትራ የሽምቅ አካባቢዎች በመገንጠል ሂደቱ ወቅት በሻዕቢያ አማካይነት በነዋሪዎች ላይ የተካሄዱትን ማህበራዊ ቤተሙከራዎች (ሶሻል ኤክስፐርመንቶች) ያስነብበናል፡፡ ሻዕቢያና ኢኤልኤፍ የኤርትራን ዘጠኝ ብሔረሰቦች ተሻግረው፣ ከብሔር ክፍፍል፣ እና ከሐይማኖት ጎራ ራሱን ያላቀቀ አንድ የጋራ ሶሻሊስታዊ ማህበረሰብ ስለሚፈጥሩበት መንገድ ሰዎችን በሰፈራና በካምፕ አሰባስበው አስቀምጠው የሠርቶ-ማሳያ ሙከራ ያከናውኑ ነበር፡፡ የጋሄሩን ቤተሙከራ የምትመራው አስካለ መንቆሪዮስ የተባለች ደፋርና ዳሌያም ሴት ነበረች፡፡ ደራሲው ሳይለከፍባት አይቀርም፡፡ ኋላ ለሻዕቢያ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ተመርጣ የነበረች ሴት ናት፡፡
የዳአባቱ ሶሻል ኤክስፐርመንት ላቅ ያለ ነገር ነበረው፡፡ የወደፊቷ ኤርትራ ኢንደስትሪ አብዮት መጠንሰሻ ሆኖ እንዲያገለግል ተወጥኖ፣ ከኢትዮጵያ በተዘረፉና በሚዘረፉ ግብዓቶች ሎጂስቲኩ እየተሟላ በኅቡዕ የሚሰራ ነበር፡፡ የሚገርመው ብዙ (ቁጥራቸው በአስራዎቹ የሆኑ የታወቁ የህክምና ዶክተሮች የሚመሩት) ከሻዕቢያ የጦር ቁስለኞች መታከሚያነት አልፎ – ለእኔ እንደ ናዚ ዘመን ምስጢራዊ የእነ ሜንጌሌ ወታደራዊ የህክምና ምርምር ካምፖች የመሰለ ቅርጽና ተግባራት ያሉት እስኪመስለኝ ድረስ በግርምት የዋጠኝ – ታላቅ ሆስፒታል ነበረ፡፡ ደራሲው ይህንን በሻዕቢያዎች ምስጢራዊ ወታደራዊ ጠንካራ ይዞታ – በፋህ – ሠንሠለታማ ተራሮች መሐል እንደ ስምጥ ሸለቆ በረዥሙ የተዘረጋ ኮሪደራማ የበረሃ ሆስፒታል ‹‹ከዓለም ትልቁና ረዥሙ ሆስፒታል›› እያለ ይጠራዋል፡፡ በአንድ ግቢ ከታጠሩ የምዕራቡና የሌላው ዓለም ሆስፒታሎች አንጻር ተመልክቶት ተገርሞ መሆን አለበት፡፡
የዚያ የሻዕቢያ የትግል ዘመን ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶ/ር ነርዓዮ ተክለሚካኤል የተባለ በአዲሳባ፣ በቤሩትና አሜሪካ የተማረ ዕውቅ የህክምና ባለሞያ ነው፡፡ ከአሜሪካ ሥራውን ጥሎ መጥቶ በሻዕቢያ የሽምቅ ኮሪደሮች ውስጥ በተዘረጋው ሰንሰለታማ ሆስፒታል – የሻዕቢያዎችን ቁምጣና ሸበጥ አድርጎ – ፕሮጀክቶቹን ለደራሲው ሊያስጎበኝ ተፍ ተፍ ሲል – ደራሲው ‹‹ከነቁምጣው ገና አንድ ፍሬ ታዳጊ ኅፃን ልጅ ይመስላል›› ሲል በአግራሞት ይሳለቅበታል፡፡ በወኔውና በመስዋዕትነቱ ይገረማል፡፡ በእሱ ብቻ አይደለም በሁሉም፡፡ ብዙ ነርሶች፣ አዋላጆች፣ የተለያዩ ባለሙያዎች – ከአስመራና አዲሳባ እና ከውጭ ሀገራት ፈልሰው መጥተው በዚያ በረሃ እየተቃጠሉ ፀረ-ኢትዮጵያ ‹‹የነጻነት›› ግዳጃቸውን ያለምንም ማማረር ይወጣሉ፡፡
ፅናት፡፡ ፅናታቸው፡፡ እና የዓላማ ቁርጠኝነታቸው፡፡ መስዋዕትነታቸው፡፡ ሁሉም በየቻለውና በየተሰማራበት መስክ፡፡ ጉልበቱን፣ አዕምሮውን፣ እና የማትተካ ህይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ቆርጦ ነው የተሰማራው፡፡ ያስደምማል፡፡ ደራሲውን ይህ የሻዕቢያዎች ነገር አስደምሞት በዚያው እንደቀረ ያስታውቅበታል በብዙ የመጽሐፉ ገጾች ባሰፈረው ጭብጨባ፡፡
እና ዶ/ር ነርዓዮ ተክለሚካኤልን ይጠይቀዋል ደራሲው፡፡ ‹‹ለዚህ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ የመድሃኒት፣ የምርመራ ቁሳቁስ፣ የላብራቶሪ፣ የመኝታና አልባሳት፣ የምግብና ሌሎች ለህክምና አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ከየት ነው የምታገኙት?›› ብሎ፡፡ መቼም የህክምና ነገር መቋረጥ የሌለበት አገልግሎት ነው፡፡ ተገርሞ መሆን አለበት ደራሲው፡፡ እና ተገርሞ ሲጠይቅ በዓለም ይኖራል ብሎ ያልጠበቀውን ፍጹም ያስገረመውን መልስ አገኘ፡፡ እንዲህ ብሎ ይመልስለታል የሻዕቢያው ቆራጥ ዶክተር ነርዓዮ ተክለሚካኤል፡-
‹‹የሆስፒታላችንን ግብዓቶች ሁሉ የምናሟላው ከኢትዮጵያ መንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማትና መጋዘኖች  ላይ እየዘረፍን (እየተቆጣጠርን) ነው!››፡፡ ክው አለ ደራሲው፡፡ ጨመረለት ዶ/ር ነርዓዮ፡፡ ‹‹ለማንም አትንገረው እንጂ – የሆስፒታሉን የግብዓት ጥያቄዎች መሠረት አድርገው የሚታቀዱና የሚተገበሩ የሻዕቢያ የዘረፋ ኦፕሬሽኖችም እኮ አሉ! ያለነዚያ ይህ ሁሉ የገነባነው ታላቅ ሰብዓዊ አገልግሎት ፉርሽ ነው የሚሆነው፣ እና ግንባር ካሉት ተዋጊዎቻችን ጋር እየተናበብን ነው የምንሠራው!›› ብሎት እርፍ፡፡
ጉድ! አልኩ፡፡ ኤርትራውያኑ ሸማቂዎች የፈጠሯቸው የትግራይ ነጻ አውጪ ሠራዊቶች ለትግራይ ሕዝብ የሚላክን የእርዳታ እህል ይዘርፉ እንደነበር ከፕ/ር መስፍን ወልደማርያም የመጽሐፍ እማኝነት ያነበበኩት ነው፡፡ የእነርሱ እየገረመኝ ስኖር – የፋህ ሆስፒታል በእግሩ ቆሞ እንዲሄድ ሲባል – በኢትዮጵያ የህዝብ ሆስፒታሎችና መሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ጦርነት ከፍተው የታቀደ ዝርፊያ የሚፈጽሙት የኤርትራ ነፃ አውጪዎች ደግሞ መጡብኝ፡፡ ወቸ ጉድ! ወይ አንቺ ኢትዮጵያ!
ከላይ ስለጠቃቀስኳቸው አስገራሚ የሰው ልጅ ቤተሙከራዎች፣ ስለ እልህ አስጨራሹ የኤርትራውያን ‹‹የነጻነት›› ፀረ-ኢትዮጵያ ጉዞ፣ እና ሌሎችም የመጽሐፉ አስገራሚ ገጾች ለማካፈል ሌላ ጊዜ ተመልሼ ለመምጣት ቃል እገባለሁ፡፡ እስከዚያ ፈጣሪ ይጠብቀን ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ መራር ታሪኮች አልፈዋል፡፡ አሁን ያሉት እነዚያ ሰዎች – በህይወት በተሞክሮ በዕውቀት በዝተው ሌሎች ሰዎች ሆነዋል፡፡ የድሮው አሰላለፍ አሁን ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ ብዙ ነገሮች ተቀያይረዋል፡፡ ወደፊትም ይቀያየራሉ፡፡
ነገር ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ.. ሀገሬን ከሩቁ ውቅያኖስ አቋርጬ እየቃኘሁ የዳን ኮኔልን ገጾች በለሆሳስ እገልጣለሁ፡፡ ብዙ ነገሮቼን ነው ጠምዶ የያዘብኝ ይሄ መጽሐፍ፡፡ እያነበብኩ በሃሳቤ ወደ ኋላ ወደ ፊት እባክናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ስለምትባለው ሀገሬ፡፡ ይቺ ኢትዮጵያ ግን… ስንቱን መቅሰፍት ነው ያስተናገደችው? ስንቱ ዓይነት ጠላት ነው የተረባረበባት? ስንቱ መዓት ነው የዘነበባት? ስንቱ እፉኝት ነው የበቀለባት? ስንቱን ጠላት ነው ከቅርቡ ከሩቁ ያፈራችው? መች ነው የጠላቶቿ፣ የአድሚዎቿ፣ የተቀናቃኞቿ ማለቂያ? መች ነው የጠላቶቿ ሰልፍ ማብቂያው? መች ነው ግንባረ ጥቁሯ ሀገሬ የሚያነሳትን፣ የሚገነባትን፣ የሚያሻግራትን፣ የሚጠግናትን፣ የሚሰበስባትን፣ የሚደርስላትን፣ አብሯት የሚያለቅስ፣ አብሯት የሚፈነድቅላትን የልብ ወዳጅ የምታገኘው? ወይስ ማግኘት ጀምራ ይሆን? የመከራዋ የመጠላቷ፣ የመድማቷ፣ ልጆቿን የመገበሯ ታሪክ መቋጫ እያገኘ ይሆን? እኔንጃ፡፡ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ አይመስለኝም፡፡ ፈጣሪ በቃሽ ይበላት ለዘመናት ስሙን የጠራነው ፈጣሪ አምላክ ኢትዮጵያን እናቴን፡፡
“አስጠለፍኩ እንጂ ጥለቱን ጥለቱን ፣
አልጨረስኩትም ቁጭቱን ቁጭቱን ፡፡”
      (- ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ)
መቋጫው እምቢ አለኝ፡፡ ግን ለዛሬ አበቃሁ፡፡
ስለ ጽሑፉ መብዛት የአንባቢውን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡
_____________________
— ከአስገራሚዎቹ የዳን ኮኔል “ኧጌይንስ ኦል ኦድስ – ኧ ክሮኒልክ ኦፍ ዘ ኤርትሪያን ሪቮሉሽን” የመጽሐፍ ገጾች የተወሰደ የታሪክ ማስታወሻ)
Filed in: Amharic