>

እኛ አዲስ አበቤዎች ነን!!! (ጋዜጠኛ ብርሃኑ ተክለያሬድ)

እኛ አዲስ አበቤዎች ነን!!!

ጋዜጠኛ ብርሃኑ ተክለያሬድ


 ውልደታችንም እድገታችንም አዲስ አበባ የሆነ የብሄርን አጥር የተሻገርን በራስ መቀለድ ጤንነት መሆኑን አምነን የተቀበልን ለእንግዳ ተቀባይነት የምንመረጥ ለተጠቃሚነት ጎሳ የሚመረጥብን ከተማችንን ይህኛው የኔ ያኛውም የግሌ ባላት ቁጥር ከኔ ካልሆንክ ተዘጋጅ እንደ ቤት ሰራተኛ ፌስታልህን ይዘህ መውጣትህ ነው የምንባል።
እኛ አዲስ አበቤዎች ነን!!!
የርእሰ ብሄሩም የርእሰ ፓርቲውም የርእሰ ክልሉም መቀመጫዎች የሆንን ተቀምጠውብን ቆረቆራችሁ እንዴ? ሳይሉ ሌላ ተቀማጭ የሚደርቡብን ከተማችንን ለመምራት ያልተፈቀደልን የኦህዴድ የብአዴን የህወሓት የደኢህዴን እንጂ የአዲስ አበቤነት ሽታ የሌላቸው ከንቲባዎች በገፀ በረከትነት የሚሰጡን ይህኛው ለራሱ ጀግና ግንባራችን ላይ ት/ቤት ያኛው ለራሱ ጀግና አናታችን ላይ ሱቅ የሚከፍትብን።
እኛ አዲስ አበቤዎች ነን!!!
 እስከአፍንጫው የታጠቀ አግአዚን በጥርብ ድንጋይ የገጠምን አቃጣሪን በፍልጥ እንጨት ያንቆራጠጥን ከዛፍ ከጉድባ ስር ሳንመሽግ በግልፅ አደባባይ በድፍረት ገዳዮችን ያርበደበድን የጓድ ሬሳ ተሸክመን “የደፈረሽ ይውደም”ን የዘመርን መሪዎቻችን ካልተፈቱ አንማርም ያልን ሀገር ተወረረች ስንባል ከወላጆቻችን በመስኮት እየዘለልን አምልጠን ተጠራርተን ሎንቺናዎችን ሞልተን “አሸው” እያልን ማሰልጠኛ የከተምን።
እኛ አዲስ አበቤዎች ነን!!!
 በድንጋይ ያርበደበድናቸው “በደንጎላ ኮሎኔል ማራኪዎች” በምርቃታችን ማግስት የድንጋይ ማንጠፍ ስራን ያበረከቱልን ያቄሙብን ገዢዎች በኑሮ ውድነት የጠበሱን በጦርነቶች ሁሉ የጥይት ማብረጃ እንሆን ዘንድ ከፊት አጥር ያሰለፉን ጦርነቱ ሲያበቃም እንደ ፎረፎር ያራገፉን ሊያቀርቡን ሲፈልጉ እናትህ የት ተወለደች?  አባትህስ? የሚሉን ።
ነፃ አውጪዎች ሁሉ ቢሮአቸውን ከፍተው የከተሙብን ከእኛ ለልማት ከቀዬአችን መባረርና ሜዳ መበተን ሽንቁር ይልቅ የምርጫ ቦርድ የበጀት ድልድል ቀመር የሚያስጨንቃቸው ፓርቲዎች የከተሙብን ውሀ የመሰለች ክላሽ አንግቦ እንደ ቆመጥ እንኳን ሳይጠቀምባት እጅ የሰጠ “ታጋይ” አዲስ አበባ ደሞ ምን ታጋይ አላት ብረት ጨብጦ የማያውቅ ሁሉ ብሎ የሚያናፋብን ሌሎች ፋኖ ቄሮ ዘርማ ወዘተ እያሉ ትግሉን ሲያስተባብሩ እኛ አንድ ኮሚክ ሸነግ የምትባል የፌስ ቡክ ቢሮ ከፍቶ እያረርን የሚያስቀን።
እኛ አዲስ አበቤዎች ነን!!!
 በበቀለኛ መንግስት ተሳደን እንደ ጅንስ ሱሪ በኮንቴይነር ታሽገን ስደት የምንወጣ በisis ካራ የምንታረድ ለወንድሞቻችን ለቅሶ አደባባይ ስንወጣ ሌላ ካራ የሚመዘዝብን መሪዎች ባለፉ ባገደሙ ቁጥር እንደ ቡዳ ፊታችሁን አዙሩ የምንባል እንጀራ ፍለጋ እኛ ጋር የከተሙ በፌሮ አንገት መቺዎች በኮብልስቶን ማጅራትን ብሎ ጣይዎች ከእርጉዝ ሴት ሀብል ነጣቂዎች የባላገር ኪስ መንታፊዎች በሰሩት ስራ “አዲስአበባ የሌባ አገር” እየተባልን ፍዳችንን የምናይ።
እኛ አዲስ አበቤዎች ነን ለ40/60 የስራ ምደባ የተዘጋጀን 40/60 የኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤት ምደባ የማይመለከተን በከተማችን ባይተዋር የሆንን በፎቅና በመንገድ አሳደግናችሁ የምንባል  ግን በፎቆቹ ግንባታ ምክንያት ቤታችን የሚፈርስብን በመንገዶች ግንባታ ምክንያት ማዶ ለማዶ ከምንተያይ ጎረቤቶቻችን የምንነጣጠል አዲስ አበቤ ባልሆነ ከንቲባ ማዘጋጃ ቤት ምክር ቤት ክፍለ ከተማ ወረዳ ወዘተ የተከበብን ከተማ አልባ ህዝቦች ባለቤትና ወኪል አልባ ነዋሪዎች
እኛ አዲስ አበቤዎች ነን!!!
Filed in: Amharic