>

ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከተቋቋመባቸው መሰረታዊ ዓላማዎች ዋነኛው በተረኝነት መንፈስ አዲስ እበባን የአንድ ወገን ብቸኛ ንብረት ለማድረግ እየተፈጽመ ያለውን ደባ መታግል ነው። በዚህም መሰረት ፓርቲያችን ያለ ህዝብ ይሁንታ በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ተስይመው ይህን አደገኛ የጥፋት ድርጊት  እግር በእግር እየተከታተለ በማጋለጥ ስፊ የሆነ ስራ ሰርቷል። የሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ፣የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤቶች ንጥቂያ፣ አዳዲስ ሰፋሪዎችን ለማደላደል በነባር የከተማው ነዋሪዎች ላይ የሚፈጽም ቤት የማፍረስ እና የማፈናቀል ዘመቻዎች በተፈጸሙባቸው ቦታዎች እየተገኘን ነዋሪውን በማነጋገር የደረሰውን ጉዳት ለህዝብ እና የሰብአዊ መብት ተቋማት አሳውቀናል።በዚህም አንዳንድ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እና የስብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ትኩረት እንዲሰጡት ተደርጓል።በዚህም የባልደራስ ፓርቲ እና አመራሮቹ የእስር፣ አካላዊ ጥቃት እና ሌሎች እንግልቶች እንዲቀበሉ ተደርገዋል።
በግዜው የመንግስት ተቋማትም በመፈጸም ላይ የነበረውን የመሬት ወረራ፣የኮንዶሚኒየም ቤቶች ንጥቂያ፣  በነባር የከተማው ነዋሪዎች ላይ የሚፈጽም ቤት የማፍረስ እና የማፈናቀል ዘመቻዎችን በመካድ ህገወጥ ድርጊቱ መፈጽሙን ባጋለጡ የባልደራስ መሪዎች ላይ ወከባ እና እንግልት በመፈጸም የማሸማቀቅ እርምጃ ይፈጽሙ እንደነበር የቅርብ ግዜ ትውስታ ነው። ከዚህምበተጨማሪ አንዳንድ የሲቪክ እና የፖለቲካ ድርጅቶች ይህን በአደባባይ የተፈጸመ አይን ያወጣ ድርጊት በማቃለል በህብረተሰቡ ዘንድ ትኩረት እንዳያገኝ ያሳዩት ቸልተኝነት አስተዛዛቢ ሆኖ አልፏል።
እንደ ባልደራስ እምነት የዚህ ችግር ምንጭ ስርዓታዊ እና በሃገሪቱ ውስጥ ባሉ ከፍተኛ የመንግስት አመራር አካላት ጭምር አቅጣጫ ሰጪነት በእቅድ የሚፈጻም ለመሆኑ ብዙ ጠቋሚ ምልክቶች አሉ። አሁን ያለው የከተማ መስተዳደርም ሆነ ፌደራል መንግስት ለተፈጸመው ድርጊት ተጠያቂ እንጂ ፣ገለልተኛ መርማሪ የመሆን የህግም ሆነ የሞራል በቃት የውም ብለን እናምናለን።ይህን የወንጀል ድርጊት በዚህ ወቅት በማንሳት ለህዝብ ጥቅም ተቆርቋሪ ሆኖ ለመታየት እየተሰራ ያለው ፖለቲካዊ ቧልት እንጂ የህዝብን ቅሬታ ለመመለስ በእውነተኛ ፍላጎት ላይ የተመሰረት ጥረት እንዳልሆነ ብዙሃኑ የከተማችን ነዋሪ የሚገነዘበው ጥሬ ሃቅ ነው። የምርጫውን ገዜ መቃረብ ታሳቢ በማደረግ ከዚህ ቀደም በነበረው ስርአት የተፈጽመ ብቻ በማስመሰል ወንጀሉን ወደ ሌላ አካል በማስተላለፍ፣የወቅቱ መስተዳድሮችን ጥፋት ለመሸፋፈን እየተካሄደ ያለው ድርጊት ለችግሩ ስር ነቀል መፍትሄ እንደማይፈጥር ሊታወቅ ይገባል።
በዚህ መሰረት፤
• በከተማችን የተፈጸመውን የሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ፣የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤቶች ንጥቂያ፣ አዳዲስ ሰፋሪዎችን ለማደላደል በነባር የከተማው ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመ ቤት የማፍረስ እና የማፈናቀል ዘመቻዎችን የሚያጣራ የከተማው መስተዳድር የሌለበት ገለልተኛ አጣሪ መርማሪ ቡድን እንዲቋቋም ይደረግ።
• የሚቋቋመው ገለልተኛ አጣሪ መርማሪ ቡድን ምሁራንን፣የከተማው ነዋሪ ተወካዮችን፣የህግ እና ስብዓዊ መብት ባለሙያዎችን፣ነጋዴዎችን፣የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን፣የሲቪክ እና ፖለቲካ ድርጅት ተወካዮችን አካቶ እንዲዋቀር እንዲደረግ።
• የማጣራቱ ሂደት የግዜ ገደብ ሳይደረግበት  በትህነግ አገዛዘ የተፈጸመውን ጨምሮ፣ አሁን ከተማውን እያስተዳደረ ባለው መስተዳደር  የተፈጽሙ ድርጊቶችን እንዲያካትት እንዲደረግ።
• ምርጫ ተካሂዶ በህዝብ የተመረጠ መስተዳደር እስከሚመሰረት ድረስ ተገኙ የተባሉት ባዶ መሬቶች፣ ህንጻዎች እና ቤቶች አንዲሁምሌሎች የህዝብ ሃብቶችለሌላ አካል ሳይተለፉ በእግድ እንዲቆይ እንዲደረግ።
በህዝብ እና በሃገር ላይ የተፈጽሙ ይህን እና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች መነሻቸው ገዢው ፓርቲ ከተለያዩ ክልሎች በከተማው ላይ የሚሾማቸው አስተዳዳሪዎች በመሆናቸው፣ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ የሚቻለው አዲስ አበባን ህዝብ ፈላጎት እና ስነ ልቦና የሚወክሉ በነዋሪው የተመረጡ አስተዳዳሪዎች ሲመጡ እንደሆነ የፓርቲያችን ጽኑእ እምነት ነው።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
ድል ለዴሞክራሲ
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ
Filed in: Amharic