>
5:18 pm - Saturday June 15, 2301

‹አዎ ጊዜው አሁን ነው...!!!››  (አሰፋ ሀይሉ)

‹አዎ ጊዜው አሁን ነው…!!!›› 

አሰፋ ሀይሉ

 

*… ‹በባርነት ያልተገዛን ህዝቦች ነን› የሚል የቆየ መፈክራችንን እየተረትን በፍርሃት ተጠፍንገን፣ ከእኛ በድፍረት ብቻ ለሚለዩ ገዢዎች ተንበርክከን፣ ‹‹እምቢ!›› ብለን ለተቃውሞ እንደ ሙሉ የሰው ልጅ የመቆም ክብራችንን ተገፍፈን የምንኖርበት ይህ የባርነት ህይወት ማብቂያው ጊዜ አሁን መሆን አለበት! የፍርሃት ክንብንባችንን አሁኑኑ ገፍፈን የአባቶቻችንን የነፃነት መንፈስ ተላብሰን የመቆሚያው ጊዜ አሁን ነው!
  — ግን ጊዜን ይዤ ለመቆም የሚያበቃኝ – የትኛው ክብረወሰኔ? የቱ ሥራዬ? 
ሰሞኑን የተጀመረውን የፌስቡክ ሰልፍ ተቀላቅዬ፡- ‹‹ጊዜው አሁን ነው!›› ከሚል ጥቅስ ጋር ምስሌን ልሰቅል አሰብኩና ሰልፊ ተነሳሁ፡፡ ሳየው በአጋጣሚ ሆኖ ሰዓቱ 2፡05 ይላል፡፡ ሁለት ሰዓት ከዜሮ አምስት፡፡ ‹‹ሸምቃቃ…!›› እንዲል ክበበው ገዳ፣ እኔም በአፍታ ሽምቅቅ አልኩ፡፡
2፡05! ሁለት ሰዓት ከዜሮ አምስት! 2፡05 ከዓለም አትሌቶች ጋር በእልህ አስጨራሽ ውድድር ማራቶንን ድል እየነሱ፣ የሀገራቸውን ባንዲራ በያደባባዩ ከፍ አድርገው የሰቀሉ፣ ኢትዮጵያውያን ያስጠሩ አይበገሬ አሸናፊዎች የክብረወሰን ሰዓት ነው፡፡ እና ለሀገሬ ምን ሰርቼ? የትኛውን ክብረወሰን ሰብሬ? የቱን ያገሬን ተቀናቃኝ ድል ነስቼ? የትኛውን አኩሪ ገድል ፈጽሜ? ምን ሠራሁ ብዬ ነው – ገና ለገና ቀለለኝ ብዬ – ሰዓቴን ፊት ለፊቴ ገጭ አድርጌ የምነሳው? ብዙ የሕሊና ጥያቄዎች ናቸው ‹‹ከበው ያናገሩኝ!››፡፡ አንገቴን በሀፍረት እስክደፋ ድረስ!
ወንድሞቼ! እና እህቶቼ! በእርግጥ እውነት ነው፡፡ ጊዜው አሁን ነው፡፡ የተግባር ሰው የመሆኛ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ሥራ ሠርቶ የማሳያው ጊዜው አሁን ነው፡፡ ለሀገር ለወገን የሚጠቅም አንድ ነገር እንኳ ሠርቶ አበርክቶ ድምጽን አሰምቶ የማለፊያው ጊዜው አሁን ነው፡፡ ፍርሃትን ድል የመንሻው ጊዜው አሁን ነው፡፡ የጀግኖች አባቶቻችንን ልብ መላበስ ቢያቅት፣ ተውሰን ለአንዲት ቀን በልበሙሉነት ‹‹ነፃ ሰዎች ነን!›› ‹‹የሰው ልጆች ነን!›› ‹‹እንደ ከብት በእረኛ ጠባቂ አንነዳም!›› ‹‹በነፃነት ምድራችን ድምጻችንን የማሰማት መብት ያለን ኩሩ ነፃ ህዝቦች ነን!›› ‹‹ነፃነታችንን ማንም ምድራዊ ኃይል ሊቀማን አይችልም!›› ብለን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ተሞልተን የመቆሚያችን ሰዓት አሁን ነው!
ያለፉት ትውልዶች ከተለመደው የዕለት ተዕለት የማዝገም ህይወት ወጣ ብለው፣ ያልተለመደ ጉልበትን ተላብሰው፣ ያልተለመደ ጥበብን አንግበው፣ ያልተለመደ የድል ጮራን ለዓለም ፈንጥቀው፣ ያልተለመደ የጀግንነት ክብረወሰንን አስመዝግበው ነው ሀገራችንን ነፃነታችንን ያቆዩልን፡፡ እኛስ? ከተለመደው ድፍረትንና ብልግናን ከመላበስ በስተቀር – እንደኛው ሰው ከሆኑና፣ እንደኛው ተሰባሪ ከሆኑ ሰዎች ጥፊና እስራት፣ ዱላና መሸማቀቅ ወጥተን፣ ቀና ብለን በሀገራችን በምድራችን እንደ አንድ መብት እንዳለው ፍጡር ለአንዲት ቀን እንኳ ኖረን ለመሞት.. ምን ሠራን? ዝም ብሎ በለሆሳስ ማዝገም፣ በለሆሳስ መኖር፣ በለሆሳስ መብላት፣ በለሆሳስ መዋለድ፣ በለሆሳስ መሞት – ይሄ ‹‹የዝም ብሎ›› ህይወት ለመሆኑ.. ህይወት ነው ወይ? ክብረወሰናችን የታለ?
ሰዓት ይዘን በሰው ፊት የምንቆመው ምን ከተለመደው የህይወታችን የፍርሃት ጉዞ የተለየ ነገር ፈጽመን ነው? የትኛው ክብረወሰናችን ነው ሰዓት አስይዞ የሚያስወጣን? በህይወታችን ምን ያስመዘገብነው ድል አለ? መቼ ነው ለክብራችን ቀጥ ብለን የምንቆመው? መቼ ነው አንፈራም፣ አንኮራም፣ አንጠራጠርም ብለን በሥልጣን ጥመኞች፣ በሌቦች፣ በሙሰኞች፣ በዘረኞች፣ በነፃነት አፋኞችና አሳሪዎች ፊት በልበሙሉነት እንደ ሙሉ ሰው የምንቆመው? መቼ ነው እንደ ሰው ለመቆጠር ያጎደለንን የመንፈስ ባርነት ድል ነስተን በሙሉ መንፈስና ጀግንነት በአደባባይ እንደ ሙሉ ሰው የምንቆመው?
ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ የተቃውሞ ሠላማዊ ሰልፍ አታደርጉም ተብሎ ተከለከለ ተባለ፡፡ ትናንትም፡፡ ከትናንት ወዲያም፡፡ ነገም፡፡ ከነገ ወዲያም መከልከሉ አይቀርም፡፡ በዓለም ላይ ያለ አምባገነን ገዢ በሙሉ – አንድም ሳይቀር – የሚያደርገው ነው ይህ፡፡ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ሳይፈቅድልህ ሠላማዊ ተቃውሞ ማሰማት አትችልም፡፡ የሰሜን ኮሪያ ኮሚኒስቶች ሳይፈቅዱልህ ሠላማዊ ድጋፍም ማድረግ አትችልም፡፡ ከሰሜን ኮሪያና ከቻይና በምትብሰው ኢትዮጵያ ደግሞ እንኳን የተቃውሞና የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ ልታደርግ ሰብሰብ ብለህም ባደባባይ ብትገኝ ለአምባገነናዊ ሥርዓቱ የሀብታምን ቤት እንደሚጠብቅ ተናካሽ ውሻ በዘበኝነት የቆሙ የታጠቁ የሥርዓቱ ወታደሮች ሊበትኑህ ከፊትህ ይንቀዠቀዣሉ!
ቆይ የቅኝ ገዢዋ የጣልያን ወታደሮች በኤርትራውያን ተገዢዎቻቸው ላይ ካደረጉት የቅኝ አገዛዝ በምን ይለያል እኛ ከራሳችን ላይ ታክስ በሚሰበስቡ የራሳችን መልክ ያላቸው ቅኝ ገዢዎች አማካይነት የምንገዛው ግዞት? ኬንያውያንን ቀጥቅጠው አስፈራርተው አስለቅሰው ሰባብረው ከገዙት ከእንግሊዞች በምን ይለያሉ የእኛ ገዢዎች? የእኛዎቹ ‹‹መንግሥት›› ተሰኝተው በቤተመንግሥት የተቀመጡ ቅኝ ገዢዎች የሚናከሱ ውሾችን አሰማርተው የተቃውሞ ሰልፈኛን ስላላስነከሱ፣ እና ቆዳቸው ስለጠቆረ ብቻ ከደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ገዢዎች የሚለዩ የመሰለው ካለ በእውነቱ ራሱን የደለለ ነሆለል ብቻ ነው፡፡ እነዚህ በተናካሽ ውሾች ፈንታ በሰው አምሳል የተፈጠሩ ተናካሽ ወታደሮችን አሰማርተው ማስነከሳቸው፣ ማስዘልዘላቸው፣ ማጓራታቸው ብቻ ነው ልዩነቱ! ይሄን የማያውቅ ካለ ሆዱ ስለሞላና አፉን ለጉሞ በህይወት ስለተመላለሰ ነፃ እንደሚመስለው ያልነቃ ባርያ ንቃተህሊናን የተላበሰ ብቻ መሆን አለበት በእውነቱ!
አፍህን ዘግተህ – ሲጭኑህ እሺ! ሲከለክሉህ እሺ! ሲመቱህ እሺ! ሲቀሙህ እሺ! ሲያስሩህ እሺ! ሲገድሉህ እሺ! ሲፈነጩብህ እሺ! ከዚህ በላይ ባርነት ምን አለ? የባርነት ትርጉሙ እኮ ‹‹እምቢ!›› ለማለት ያለመቻል ነው! ባሪያ ‹‹እምቢ!›› የማለት መብት የሌለው ሰው ማለት ነው፡፡ ከዚህ በቀር ከሌላው ሙሉ ሰው የሚለይበት አንዳች ነገር የለም ባርያ፡፡ እና የኢትዮጵያ ህዝብ አባቶቹ በነፃነት ባስረከቡት ምድር ወደ ባርነት መውረዱ ብቻ እኮ አይደለም የሚያሳዝነው፡፡ በባርነት እየተገዛ እንደሆነም ራሱ አለማወቁ ጭምር ነው! ባርያ ብቻ ነው ‹‹እምቢ!›› ብሎ ተቃውሞውን ማሰማት የማይችለው፡፡ ባርያ ብቻ ነው ጌታው የሰጠውን ትዕዛዝ ጥሶ ‹‹ያን አደርጋለሁ!›› ወይም ‹‹ይሄን አላደርግም!›› ብሎ የመወሰን የአዕምሮ ፈቃድ የሌለው፡፡ ባርነት መለያው ይሄና ይሄ ብቻ ነው! ሌላ መስፈርት የለውም ለባርነት! ዛሬ በባርነት እየተገዛሁ አይደለም የሚል ኢትዮጵያዊ ካለ ራሱን ያታለለ ብቻ ነው!
ኬንያ ውስጥ ናይሮቢ በጣም ላጭር ጊዜ ሄጄ ነበር፡፡ የራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች ከኢስሊ ትንሽ ፈቀቅ ብሎ በሚገኝ ዋና የናይሮቢ የገበያ ማዕከል ላይ ተሰባስበው የተቃውሞ ድምጻቸውን ያሰማሉ፡፡ ‹‹ኦዲንጋ የሕዝብ ልጅ!›› እያሉ ይጮሃሉ፡፡ በስሜት ተሞልተው ይጨፍራሉ፡፡ በቁጣ እየነደዱ ይፎክራሉ፡፡ ገበያተኛው ሁሉ በጭብጨባ ይደግፋቸዋል፡፡ አብሯቸው ይጮሃል፡፡ ጥቂት ቆይቶ ፖሊሶች መጡ! ከዚህ ቦታ ንቅንቅ አንልም ብለው መጮሃቸውን ቀጠሉ! ኡሁሩ የቀማውን የምርጫ ድምጽ ይመልስ! መንግሥት የለንም! ኡሁሩ ውረድ! ነው የሚሉት፡፡ ወታደሮቹ (ፖሊሶቹ) መጨረሻ አስለቃሽ ጭስ መተኮስና በዱላ ሰልፈኛውን መበተን ጀመሩ፡፡ ኬንያውያኑ ፖሊስ ሲያዩ ነብር እንደመጣበት ፈሪ ዝም ብለው አይበታተኑም፡፡ ከፖሊሶቹ ጋር ግብግብ ገጥመው ነው፡፡
ከላይ ሶስተኛ ፎቅ ላይ ሆኜ እንደፊልም ነበር የማያቸው፡፡ ፖሊሶቹ መጨረሻ ጠብመንጃቸውን ወደ ሰማይ መተኮስ ጀመሩ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ወደ ሁለት ሰዓት በፈጀ ትርምስ ሰልፉ ተበተነ፡፡ ‹‹ኑ ወደዚህ አትመልከቷቸው በጥባጮች ናቸው!›› እያለ ከመስኮቱ ወደሌላ ክፍል እያሸሸን የነበረው ከኡሁሩ የቅርብ አለቅላቂዎች አንዱ ከኛ ጋር አብሮ ነበርና የእኔን በግርግሩ ተመስጦ በመስኮት መታደም ሲመለከት ደሙ ፈላ! ‹‹ይሄ እረፍት የለሽ ወጣት እየተንቀዠቀዠ አስቸገረኝ! አትሂድ አላልኩህም ወይ?!›› ብሎ በንዴት ተንጨረጨረ በእኔ ላይ!
ሰውየው ምናልባት በሆዱ በተቃዋሚዎቹ የአጉል ሰዓት አሳጪ ጩኸትም ይሆናል የበሸቀው፡፡ እና እኔ ስጨመርበት በኔ ላይ አወጣው ግልፍቱን፡፡ በንቀትና በትዝብት ከመመልከት በቀር የምለው አልነበረኝም፡፡ የአፍ ‹‹ይቅርታ›› ጠይቄው ከጎብኚ ቡድኔ ጋር ተቀላቀልኩ፡፡ በማግስቱ በኡበር መኪናችን እየተዘዋወርን – የናይሮቢ ጎዳናዎች በነፃ በሚበተኑ እና የትናንቱን ተቃውሞ በፊት ገጻቸው በያዙ ጋዜጦች እና ጋዜጣ በነፃ በየመስኮቱ በሚያድሉ አዟሪዎች ተሞልቶ ጠበቀን፡፡
ከኛ ጋር በወዳጅነት የሰነበተው ኬንያዊ ሹፌሩ ጆርጅ በጋዜጣው ላይ ያሉትን የራዬላ ኦዲንጋና የኡሁሩ ኬንያታን ምስል መልከት አደረገና፡- ‹‹እኛ እዚህ ሁለት መሪዎች ሆነውብን ተቸግረናል፣ የናንተ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሥልጣን መልቀቁን ሰምተናል፣ እና ትርፍ ስላለን፣ እባካችሁ ኡሁሩን ውሰዱልን!›› ብሎ በሳቅ ገደለኝ፡፡ ‹‹ኦዲንጋ – ኧ ማን ኦፍ ዘ ፒፕል!›› ነው አለን በስሜት ተሞልቶ፡፡ እና ከቀይ ወደ ቢጫ፣ ከቢጫ ወደ አረንጓዴ ሲቀየር የትራፊክ መብራቱ ጆርጅም ጋዜጣውን በዳሽቦርዱ ላይ አኑሮ ጉዞውን ቀጠለ፡፡  ለታሪክ ይሁነኝ ብዬ ጋዜጣውን ይዤው ተመለስኩ አዲሳባ፡፡
በዚያ ሁሉ ውስጥ የገረመኝ አንድ ትልቅ ነገር ነበር! በአዲስ አበባ የምንኖር ኢትዮጵያውያን – ዕድሜ ልካቸውን በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ የኖሩትን ኬንያውያን የሚያህል እንኳ ሩብ መብት የሌለን የጊዜው ባሮች ሆነናል! ኬንያውያን ቢያንስ የፈለጉትን መሪ መምረጥ ባይችሉ – መሪያችን ይሄኛው ነው ብለው የመቃወም ግን መብት ነበራቸው፡፡ ጎረቤታችን የእንግሊዝ ቅኞች የነበሩት ኬንያውያን ዛሬ የመቃወም መብት አላቸው፡፡ እኛ ለ3ሺህ ዓመት በነጻነት ኖርን የምንል ኢትዮጵያውያውያን ዛሬ ይህ ኬንያውያን ያላቸው የመቃወም መብት የለንም! ይህ እውነት ራሱን ለመደለል ላልፈለገ ህሊናና አዕምሮ ላለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ግልጽ መሆን ያለበት እውነት ነው! ያስቃል! ያሳቅቃል! ከፍ ሲልም ያስለቅሳል! ያንጨረጭራል! ከኬንያውያን ያነስን ባሮች የመሆናችን እውነት፡፡
ዛሬ ‹ጊዜው አሁን ነው› ብለን ስንነሳ – ሌላ ቀርቶ ከጎረቤት አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በታች ያዋለንን – በራሳችን ላይ የመወሰን የመንፈስ ነፃነታችንን የነጠቀንን ባርነታችንን ሰብረን ነፃ ሆነን ለመቆም፣ ከባርነት ለመውጣት አንድ ቁርጠኛ ነገር ለማድረግ ወስነን መሆን አለበት! ዛሬ ‹‹ጊዜው አሁን ነው!›› ብለን ሰው ፊት ስንቆም – እስከዛሬ ሆዳችንን እየሞላን ሰጥ-ለጥ ብለን፣ አሊያ እያደገደግን ብቻ እንድንኖር ከተጣፍንበት ከዚህ የተለመደና የቸከ የባርነት ህይወታችን ተለይተን፣ ከወትሮው የተለየ፣ ያልደፈርነውን፣ ሳናደርገው የቆየነውን፣ የአባቶቻችንን የጀግንነት ልብ ለአንድ ቀን፣ ለአንድ አፍታ፣ ለአንዲት ቅጽበት ተላብሰን ገዢዎቻችንን ‹‹እምቢ!›› ብለን ለመቆም፣ እና የራሳችንን የሰውነት ክብረወሰን ለማስመዝገብ ልናውጅበት ካልሆነ በቀር – ምንም ትርጉም የለውም! በየትኛውም ዓለም – አምባገነን መንግሥትን እያስፈቀዱ በማጎብደድና በፍርሃት በመራድ የመጣ አንድም ለውጥ የለም! አንድም እንኳን!
‹በባርነት ያልተገዛን ህዝቦች ነን› የሚል የቆየ መፈክራችንን እየተረትን በፍርሃት ተጠፍንገን፣ ከእኛ በድፍረት ብቻ ለሚለዩ ገዢዎች ተንበርክከን፣ ‹‹እምቢ!›› ብለን ለተቃውሞ እንደ ሙሉ የሰው ልጅ የመቆም ክብራችንን ተገፍፈን የምንኖርበት ይህ የባርነት ህይወት ማብቂያው ጊዜ አሁን መሆን አለበት! የፍርሃት ክንብንባችንን አሁኑኑ ገፍፈን የአባቶቻችንን የነፃነት መንፈስ ተላብሰን የመቆሚያው ጊዜ አሁን ነው! ባርያ አለመሆናችንን – ሙሉ ሰው መሆናችንን – የራሳችንን የመንፈስ ፈቃድ በመፈጸምና በልበሙሉነት ገዢዎቻችንን ተቃውሞ በመቆም የማስመስከሪያችን ጊዜ አሁን ነው! ከባርነት የመላቀቂያው – እና ሙሉ ሰው መሆናችንን የማስመስከሪያው – ጊዜው – አሁን ነው!
አምባገነኖችን በመፍራት – ፈጣሪ የሰጠንን ሙሉ ሰውነት – የአዕምሮ ፈቃዱን ወደተነፈገ የባርያ ማንነት አንቀይረው!
ፍርሃታችን ለአንድና ለአንድ ፈጣሪ አምላክ ብቻ ይሁን!
ፍርሃትን ድል የመንሺያው፣ ባርነትን የማብቂያው – ሙሉ ሰውነትን፣ ሙሉ ኢትዮጵያዊነትን የማወጃ ጊዜው አሁን ነው! 
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic