>

" የድንቁርና ጌቶች....!!!"  (ጸጋው ማሞ)

” የድንቁርና ጌቶች….!!!”

        ጸጋው ማሞ

 


 

  የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን የቁልቁለት ጉዞ  እራሱን ፋርሄዥያ ( እራስን ለአደጋ አጋልጦ የሚያውቁትን እውነት መናገር)  ብሎ በተለይ ለኛ ለኢህአዴግ ትውልዶች የሀገራችንን ጉድ እንድናውቀው  በድፍረትና በግልጽ በ400 ገጽ  ቀንብቦ በማቅረብ የዜግነት ድርሻውን ስለተወጣ  መምሕር ብርሃኑ ደቦጭን እጅ እንነሳለን ።  
  ——-
  የመጽሐፉ ደራሲ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚሰራና  በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች የሚጽፍ በተለይም በፍትህ መጽሔት ላይ በመጽሐፍ ግምገማ (Book review ) ላይ  የምናውቀው ሲሆን በመጽሐፉም ላይ እንደገለጸው የPHD ተማሪም  የሆነም ነው  ። የአ.አ ዩኒቨርስቲ እንዲስተካከል በመታገሉም ሁለት ጊዜ ሥራ የለቀቀም እንደሆነ በመጽሐፉ ነግሮናል ።
    —–
        ጸሐፊው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንቶች የፖለቲካ የትሮይ ፈረስነት በግልጽ በመረጃ በመንተራስ እነ እንድርያስ እሸቴን ፣ አድማሱ ጸጋዬን  እና ጣሰው ወልደሃናን የድንቁርና ጌትነታቸውን በትዝብትና በቁጭት ምስል ከሳች በሚመስል መረጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው ጽፎልናል ። የአካዳሚክ ማኅበረሰቡም የድንቁርና ጌትነታቸውን ሲጽፍ ለሀገር በመቆርቆር  መሆኑ ለድፍረቱ ዋስትና የሆነለት ይመስለኛል ። አሁንም ያለውን ተስፋቢስ የዩኒቨርስቲውን  ጉዞ መጠቆሙን አለማድነቅ አይቻልም ።
   —–
  በተለይ የ42ቱ የዩኒቨርስቲ መምሕራን በአቅም ማነስ በሚባል ምጸት የመባረር ሂደትና  መለስ ዜናዊ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባደረገው የምሁራኑንና የሀገሪቱን ክብር የነካ ስብሰባ ላይ ከዶ/ር አንማው እና ከአቶ ሙሉጌታ ጉልማ በስተቀር ሌላው ዝም ያለበትን የምሁራን ንጥፈት ጅማሬ አንስቶ እስከአሁኑ ጊዜ ያለውን በካበተ መረጃ በድፍረት ተንትኖታል ።የዩኒቨርስቲ ክሽፈት ሊያውም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ክሽፈት የሀገሪቷ የአሁናዊና የወደፊት ክሽፈት መሆኑን ለመረዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው ።
  ——
   በመጽሐፉ ላይ ከተገለጡት በመረጃ ላይ  የተመሰረተ በርካታ  ክሽፈት ውስጥ :-
 ከ2 ነጥብ በታች ያላት ልጅ በእንድርያስ እሸቴ አማካኝነት ውጭ  ተልካ ተምራ የአዲስአበባ  ዩኒቨርስቲ መምሕር ሆናለች
 — ለመመረቅ ውጤት ያልሞላለት ተማሪ የሌላ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዘዳንት ሆኖአል  ።
 — ብሔራዊ ፈተና የወደቀ ተማሪ አልፈሃል  እየተባለ ዩኒቨርስታው ይገባል
 — ወርቅ የወሰዱ ተማሪዎች እያሉ የቀበሌ ወረቀት ያላቸው ተማሪዎች ለመምሕርነት ይመለመላሉ  ።
 — ዩኒቨርስቲው የብሔር ፖለቲካ መሻኮቻ እንደሆነ
 — ውጭ ሀገር ተምረናል የሚሉ በቂ ዶክመንት የሌላቸው ሰዎች የሚያስተምሩበት
 –የውጭ ሀገሮች አገሪቷን ለማዳከም የዩኒቨርስቲውን  በስውር እንደሚያዳክሙትና በርካታ ከአ.አ ዩኒቨርስቲ የማይጠበቅ አሳፉሪ ድርጊቶችን ለማሳየት ሞክሯል ።
 ባጠቃላይ ኃላፊነት የሚሰማው ምሁራን እንደሌለ ሁሉም ለራሱ ጥቅም እንደሚሯሯጥ በግልጽ ይተነትናል ።
    ——
  ዩኒቨርስቲው ወይ የውጭውን ወይ የሀገርኛውን የትምህርት ሥርዓት ሳይዝ እንዲሁ የመሀይማን መጫወቻ እንደሆነ የኢትዮጵያ  ሕዝብ እንዲያውቀው  በመግለጽ  የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ተወጥቷል ። ህወኃት – ኢህአዴግ ” አቅመቢስ ትውልድ ፈጥሬ ፓለቲካውን ፣ ኢኮኖሚውን እና የጸጥታውን ክፍል መቆጣጠር እችላለሁ ” በሚል ያዳከመው ዩኒቨርስቲ  ወደ ፊትም ትንሳኤ ማግኘቱን ጸሐፊው ካለው አሁናዊ  ሁኔታ በመነሳት ይጠራጠራል ። ገጽ 341
          በመጨረሻ
       —————–
 ጸሐፊው ብርሃኑ ደቦጭ  እንዲህ ይላል ” ሕዝቡ ከጀርባው ሲሰራው የነበረውን ነገር በጥቂቱም ቢሆን እንዲያውቅ የራሱንም ሚና እንዲረዳ እና እንደሚገባው ያሳስባል ” ገጽ 386 ” የዩኒቨርስቲው  ችግር ያለ ትምህርት ሥርዓቱ መስተካከል  ሊፈታ እንደማይችል ፤ የትምሕርት ሥርዓቱ ችግር መፍትሄ ደግሞ ያለ ፖለቲካ ሥርዓቱ ችግር እንደማይታሰብ ” በመደምደሚያው ላይ በመምከር ይጨርሳል ።
     ——
        መጽሐፉ በመረጃ የዳበረና ለገበያ ተብሎ የተጻፈ ሳይሆን ከአንድ እውነተኛ የሀገር ተቆርቋሪ ለትውልዱ የተበረከተ  እንደሆነ ይሰማኛል ። የአንድ ሀገር ህልውና በዩኒቨርስቲ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ የዩኒቨርስቲ አብርሇት የሀገርም አብርሇት ነውና ዓይኖች ሁሉ ወደ ዩኒቨርስቲ ትንሳኤ መመልከት አለባቸው ።
   መምሕር ብርሃኑ ደቦጭ እናመሰግናለን
Filed in: Amharic