>

ወይዘንድሮ... የማስክ የማስክ አነባብሮ...!!! (በእውቀቱ ስዩም) 

ወይዘንድሮ… የማስክ የማስክ አነባብሮ…!!!

(በእውቀቱ ስዩም) 

ወይ ዘንድሮ- አለ ስንዝሮ- አንድ ዶላር በአምሳ ሁለት ብር ዘርዝሮ !  እንደማመመጥ!    የተሻለ ይመጣል ብለን ስንጠብቅ፤  አዲሱ የፈረንጆች አመት  አዲስ የኮቪድ ጎረምሳ  ፈቶ ለቆብናል ፤ በአምናውና በዘንድሮው ኮቪድ መካከል ያለው ልዩነት ምን ብየ ላስረዳችሁ?  በልዩሃይል እና በሪፓብሊካን ጋርድ መካከል ያለው ያቅም ልዩነት እንደማለት  ነው ፡፡
አምና ሁሉም ቻይና ላይ ነበር  ጣቱን ብቻ ሳይሆን አንቴናውን  እሚቀስረው! አሁን እያንዳንዱ አገር የራሱን  ብራንድ ቫይረስ በማመንጨት ላይ ይገኛል ፡፡
ባለፈው  ወዳጄ በየነ  ዶክተሮች ምርመራ አድርገውለት
“ ኮቪድ አለብህ”ሲሉት ምን ብሎ መለሰ?
“ የእንግሊዙ ነው የደቡብ አፍሪካው?”
እኔን  አይያዘኝ አልልም ! ከያዘኝ የኢትዮጵያው  እንዲደደርሰኝ ፀልዩልኝ!  አንዳንዴ ሲደብረኝ አዲሳበባ ወይም ማርቆስ ለሚኖር ጉዋደኛየ እደውላለሁ ፤
“ እንዴት ነው ኮቪድ? ”
“  እኔማን ትናንት ይዞ ለቀቀኝ “ ይለኛል
“ ፍቅር እንኩዋ  ትንሽ ሳያሽ፥ ሳያከስል፥ ሳያከሳ አይለቅም !  እንዴት ዝምብሎ ይለቅሃል?”እላለሁ በቅናት ስሜት ፤
  የሆነ ነገር ትዝ ይለኛል ፤ ድሮ   መገናኛ ካልዲስ  ካፌ ፊትለፊት ቆሜ የኮንሮባንድ ጫማ ስመርጥ  የሆነ መዳፍ ትከሻየን ይነካኛል   ፤ ዞር ስል  አንድ  ሰውየ   “ኦ ይቅርታ  ከማጅራትህ ሳይህ ከማውቀው ሰው ጋር ተመሳስለህብኝ ነው”  ይለኝና  ለጥቂት ሰከንዶች ይዞት የነበረውን ትከሻየን ይለቀዋል፤ ሸገር ያሉ ጉዋደኞቼ “ ኮቪድ ይዞ ለቅቀኝ ሲሉኝ “ ይሄ ነው ትዝ እሚለኝ!
 እኔ ያለሁበት ከተማ  የማስክ አነባብሮ ሁሉ ተጀምሩዋል !  በሰርጀሪው ማስክ ላይ ሌላ ከገበርዲን የተሰራ ማስክ  ካልደረብሽ አገልግሎት አታገኝም ፤ ትንሽ ቆይተው፤  ኦክስጂን ራሱ በጉልኮስ መልክ የሚሰጡን ይመስለኛል ፤
ይህንና መሰል ጣጣዎችን ለመርሳት ዩቲውብ ላይ እጣዳለሁ ፤ዩቲውብ ለታታሪ ተመልካች መክፈል ቢጀምር እካሁን መኪና ብቻ ሳይሆን  የራሴ መጠበቂያ ድሮን ሁሉ  ይኖረኝ ነበር፤ ለመሆኑ ምንድነው እማየው?    ፖለቲካ? ለእድሌም አላሳየው! ትናንት በርካታ ቆነጃጅት አንዱን አልባሌ ዘፋኝ ከበው ሲደንሱ  አይቼ ዘና አልሁ ! ሌዲ ጋጋ የኢግዚቢሽን ማእከልን ድንኩዋን የሚያክል  ቀሚስ በምትለብስበት ዘመን ያገራችብን ጉብሎች  በከፊል መለመላ ሲቀውጡት አይቼ ተደነቅሁ  !   በእኛ ጊዜ ክሊፕ በአይናፋር ሙድ ነበር እሚሰራው! አለማየሁ እሼቴ  ኩኩ ሰብስቤን  “ እንግዳየ ነሽ የኔ እንግዳ በበሩ ገብተሽ  አረፍ በይ  ጉዋዳ” ይላታል፤ እሱዋም እየተሽኮረመመች  ያንኑ ትደግምለታለች!  ግን ሁለቱም ጉዋዳ ለመግባት አይደፍሩም!  ዘፈኑ ጀምረው እሚጨርሱት  ከግቢ ውጭ ነው ፤   ዛሬ አስራ ምናምን ወይዛዝርት ሊሞዚን ውስጥ አንዱን ጎረምሳ ከበው ሲደንሱ  አያለሁ!   መብታቸው  እንደሆነ ባምንም በዘፋኙ ላይ የተሰማኝን ቅናት የቀላቀለበት ንዴት መደበቅ አልቻልኩም !  እኔ እዚህ ተኮራምቼ ተቀምጨ የሰው አገር ብርድ እየጠጣሁ ፤ እንዴት  ዋናው ሰብአ ሰገጥ ፤  ጨረቃ በመሳሰሉ ኮረዶች ይከበባል? በውነት ፌይር አይደለም!
 የሆነ ቁምነገር  ነገር ልጨምር!  ብዙ ያገሬ ሰው በብልግና ነክ እንቶፈንቶ  ቪድዮዎች ሲማረር አየዋለሁ ፤ የሚሻለው አለማየት ነው!     እይታ በሌለበት  እንዲህ አይነት ቪድዮዎች አይለመልሙም! ግን ያገሬ ሰው ባፉ  እያማረረ ባይኑ ይቸክላል! ታድያ  ገበያው ካለ ሸቀጡ ለምን አይኖርም?
Filed in: Amharic