>

እስስትነት እና በቀቀንነት - THE NEW NORMALS! (አሰፋ ሀይሉ)

እስስትነት እና በቀቀንነት – THE NEW NORMALS!

አሰፋ ሀይሉ

 

*..   ትናንት ከሥርዓቱ ሹመኞች ጋር በአደባባይ ቆሞ ‹‹ልማታዊ፣ ጅማታዊ፣ አብዮታዊ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ሰማዕታት፣ … ምናምን›› እያለ ሲበጠረቅና መከራችንን ሲያበላን የነበረ የሥርዓቱ ወደል ካድሬ – ዛሬ እነዚያ ልማታዊ አብዮተኞች አፈር እየቃሙ፣ እነዚያ አስጠሊ ቃላት ዱቄት እየሆኑ መምጣታቸውን ሲረዳ ወይም ገና ከሩቁ የሸተተው ሰሞን – በ180 ዲግሪ ግልብጥ ብሎ – በለውጥ ሃዋርያና በለውጥ አዋላጅነት፣ በለውጥ አጋፋሪና አሻጋሪነት አምሳል ብቅ ብሎ – በእነዚያው ተመሳሳይ መድረኮች ላይ ዓይኑን ድርቅ አድርጎ – የልማታውያን አብዮተኞች ጊዜ የማብቃቱንና የለውጥ ፊሽካ የመነፋቱን ጡሩንባ ሲነፋ ታገኙታላችሁ፡
እስስትነት የመጨረሻው ደረጃ የማስመሰል ብቃት ነው፡፡ በእስስት (chameleon) ተፈጥሮ የማይነቅ የለም፡፡ በእስስት የቆዳ ቀለም የመቀያየር ዙሪያ ለዘመናት የተነገሩ ብዙ ትንግርቶች አሉ፡፡ ብዙ ሳይንሳዊ ምርምሮች ተካሂደውባታል፡፡ ቆዳዋን የመቀያየርና ከአካባቢዋ ጋር የመመሳሰል ተፈጥሯዊ ብቃቷ ምስጢርም ሳይንሱ ደርሶበታል፡፡ እንደ ቀስተ ደመና በመላ አካሏ የሚሰራጭ ህብረቀለማዊ የተፈጥሮ ንዑድ ያላት ፍጡር ናት፡፡ በወታደራዊውና የስለላው ዓለም ሳይንሶች ውስጥ እስስትነት ‹‹camouflage›› ቁልፍ ሥፍራ የሚሰጠው ስልት ነው፡፡ ከአካባቢህ ጋር ራስህን ‹‹ማመሳሰል››፣ ከጠላትህ ጋር ራስህን ማመሳሰል፣ ከመልክዓ ምድሩ ጋር ራስህን ማመሳሰል – ባጠቃላይ በእስስትነት ችሎታህ ጣራ መንካት – ራስህን ለማዳንም፣ ጠላትህን ለማውደምም – ትልቅ ድርሻ ይወስዳል፡፡
ሰዎች በጦርነት ጊዜ እስስትነትን ህልውናን እንደማቆያ ዘዴ ቢጠቀሙበት እሺ እሠየሁ፡፡ ግን በሠላም ጊዜ ሰዎች ራሳቸውን ከመሆን ይልቅ እስስትነትን ለምን ይመርጣሉ? – ምክንያቱ ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ካላስመሰሉ የሚበሉ›› ሰዎች አሉ፡፡ ማስመሰል የህልውና ግዴታቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች እውነተኛ አቋማቸውን ከገለጡ፣ እውነተኛ ፍላጎታቸውን ካወጡ፣ እውነተኛ ሰብዕናቸውን ፊት ለፊት አውጥተው ካሳዩ – የእንጀራ ገመዳቸው ይበጠሳል፡፡ ካላስመሰሉ በልተው ማደር አይችሉም፡፡ ስለዚህ ለህልውናቸው ሲሉ ማስመሰላቸውን ይቀጥላሉ፡፡
በዚህ የተነሳ ብዙ ፖለቲከኞች እስስቶች ናቸው፡፡ ‹‹ጎርፍ ሲመጣ ለጥ፣ ጎርፍ ሲወጣ ቀጥ›› የማለቱ ሰንበሌጣዊ የመተጣጠፍ ችሎታቸው ከማንኛውም የፖለቲካ ማዕበል በህይወት ተርፈው እንጀራቸውን እየጋገሩ ለመቀጠል ያስችላቸዋል፡፡ እስስትነትን – ከመጣው ጋር ያንኑ ራሱን ሆኖ – አንዳንዴም ብሶ የመገኘትን አስገራሚ ብቃት – እንደ ባህርይ ተላብሰውታል፡፡ ከመጣው ባለጊዜና ከመጣው ፖለቲካ ጋር አብረው ተመሳስለው መንፈስን ተክነውበታል፡፡ ከትናንት ወዲያ የሶሻሊዝም አቀንቃኝ ሆኖ በአካዳሚክ ጆርናሎች ላይ ሲተነትን የኖረ ‹‹ምሁር››፣ ከጊዜው ጋር ግልብጥ ብሎ የካፒታሊዝም አቀንቃኝ ሆኖ ብታገኙት፣ አትፍረዱበት፡፡ እስስትነት የእንጀራ ጉዳይ ሆኖበት ነው፡፡
ትናንት የብሔር ብሔረሰቦች ወኪልና ጠበቃ ሆኖ ሰዉን አላስቀምጥ ያለ የጋርዮሽ ዘመን ሰባኪ፣ ዛሬ ዓይኑን በጨው እጥብ አድርጎ ፊታችሁ ቆሞ – የሠለጠነው ዓለም አንድ ሆኖ የአውሮፓ ህብረትን ፈጥረን በአንድ ገንዘብ እንገበያይ በሚልበት ዘመን በብሔር ብሔረሰብ እርስ በርስ ተነጣጥሎ የሚደረግ ጉዞ ከዘመናዊው ዓለም ፊታችንን መልሶ ወደ ጥንት የዝንጀሮ ዝርዮቻችን የሚመልሰን መሆኑን ሲሰብክ ብታገኙት ምን ትሉታላችሁ?
ትናንት ከሥርዓቱ ሹመኞች ጋር በአደባባይ ቆሞ ‹‹ልማታዊ፣ ጅማታዊ፣ አብዮታዊ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ሰማዕታት፣ … ምናምን›› እያለ ሲበጠረቅና መከራችንን ሲያበላን የነበረ የሥርዓቱ ወደል ካድሬ – ዛሬ እነዚያ ልማታዊ አብዮተኞች አፈር እየቃሙ፣ እነዚያ አስጠሊ ቃላት ዱቄት እየሆኑ መምጣታቸውን ሲረዳ ወይም ገና ከሩቁ የሸተተው ሰሞን – በ180 ዲግሪ ግልብጥ ብሎ – በለውጥ ሃዋርያና በለውጥ አዋላጅነት፣ በለውጥ አጋፋሪና አሻጋሪነት አምሳል ብቅ ብሎ – በእነዚያው ተመሳሳይ መድረኮች ላይ ዓይኑን ድርቅ አድርጎ – የልማታውያን አብዮተኞች ጊዜ የማብቃቱንና የለውጥ ፊሽካ የመነፋቱን ጡሩንባ ሲነፋ ታገኙታላችሁ፡፡ እስስትነትን መላበስ ብቻ አይደለም፡፡ በማስመሰል ብቃቱ እስስትን ራሷን በእጥፍ አስከንድቶ የሚገኝ – ስንት ዓይነት አውራ እስስት አለ መሰላችሁ?
ከዚህ ከእስስትነት ተነጥሎ የማይታይ ከፍተኛ የመመሳሰል መርህም ደግሞ አለ፡፡ በቀቀንነት፡፡ በቀቀንነት ራስን የሆነ ቦታ አርቆ ቀብሮ – ሌላው ባለጊዜና ባለተጽዕኖ ሰው ያለውን እየተቀበሉ እንደወረደ ማስተጋባት ነው፡፡ ያሳለፍነው እና እያለፍንበት ያለው ኢህአዴጋዊ ሥርዓት ካጋባብን አጉል እስስታዊ ልክፍቶች አንዱና ትልቁ – ፖለቲካዊ ‹‹በቀቀንነት›› ነው፡፡ ይህ በብዙ ሰው ላይ በስፋት የነገሠው የበቀቀንነት ባህርይ ‹‹ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት›› የሚባል ስታሊናዊ የጭቆና መዘውር የወለደው ያለፈው የጋርዮሽ ሥርዓታችን ክፉ የፖለቲካ ውርዴ ነው፡፡ ከሰው ሰው፣ ከዘር ዘር ሁሉ ይተላለፋል፡፡
በቀቀንነት ‹‹ልዩነታችን ውበታችን›› የሚባልለትን ሀገራዊ ዲስኩር ከነነፍሱ ዋጥ-ስልቅጥ አድርጎ የበላብን – እና ሁላችንንም በፖለቲካው አናት ላይ ፊጥ ባሉት አብዮተኞች አምሳል – አንድ ዓይነት ሰብዓዊ ጡሩንባዎች አድርጎ ሊያወጣን በየልሳናችን የተገጠመልን – ክፉ ኢህአዴጋዊ ልክፍት ነው፡፡ ይህ የበቀቀን ውርስ አሁንም ከውስጣችን አልጠፋም፡፡ ዛሬ ብዙዎች ራሳቸውን መሆን ትተው ቀላል ሆኖ ያገኙትን ሌላውን የመሆን ፈለግ ተከትለው እየነጎዱ ነው፡፡ ሌላውን የማስተጋባትን የበቀቀንነት እና የእስስትነት የባህርይ ውርስ የሙጥኝ ብለው ተመሳስለው እየከነፉ ነው፡፡
ዛሬ ብዙ ሰዎችን ስታናግር የሚያናግሩህ በራሳቸው መንፈስ፣ እና በገዛ አዕምሯቸው ሆነው አይደለም፡፡ ወይ በአብይ አህመድ መንፈስ ሆነው፡፡ ወይ በጃዋር መሀመድ መንፈስ ሆነው፡፡ ወይ በዶ/ር ብርሃኑ መንፈስ ሆነው፡፡ ወይ በአብን መንፈስ፡፡ ወይ በኦነግ መንፈስ፡፡ ወይ በሆነ የብኤል ዜቡል መንፈስ ተሞልተው ነው፡፡ ብዙ እስስት እና በቀቀን ከመሆን አልፈው – ወደ ራሳቸው ለመመለስ እስኪቸገሩ ድረስ ራሳቸውን በሂደት አጥተውታል፡፡ የራሳቸው የተፈጥሮ ቀለም የለም፡፡ የራሳቸውን ንጹህ ቃላት ትተው – የሚናገሯቸው ሁሉ ቃላት ከእነዚያ መንፈሶች የተቀዱ ቃላት ሆነው ይገኛሉ፡፡
በቀቀንነት እንዲህ የሰው መፍሰሻ ቧንቧ አድርጎ አስቀረን፡፡ እስስትነት ራሳችንን አስጥሎ ሌሎች የእንጀራ ገመዳችንን የያዙ ባለጊዜዎችን መስለን እንድናድር አደረገን፡፡ ሌላ ሰውን መሆን፣ ከሌላው ሰው አቋም ጋር የራስህንም አቋም በፍጥነት እየቃኘህ እየቀያየርክ መቀጠል – ትልቅ መርህ ሆኗል፡፡ ያልተገለባበጠ ያራል፡፡ እስስት ያልሆነ ይበላል፡፡ በቀቀንነቱን ያላስመሰከረ ይጨፈለቃል፡፡ ጊዜው የእስስትነት ነው! ከበቀቀን በላይ በቀቀን፣ ከእስስት በላይ ሰብዓውያን እስስቶች ሆነናል፡፡ ሳስበው በዚህ አያያዛችን እስስት ራሷየምትቀናብን ይመስለኛል፡፡
“ይድረስ ለአድርባዩ ጓዴ ፡-
“እየለየ ጊዜ — ቦታ እየመረጠ
እስስታማ መልክህ — ገፅህ ተለወጠ፣
አህያ እንዳልነበርህ — በሠርዶዎች መሐል
አህዮች ሲበዙ — ዛሬ ጅብ ሆነሃል፡፡”
  – በዕውቀቱ ስዩም፤ «ይድረስ ለአድርባይ ጓዴ»፤ “ስብስብ ግጥሞች”፡፡
ወንድሜ ሰው ሁን! ራስህን ሁን! በእስስታማ ማንነት የቀየርከውን ያንኑ የራስህን ቆዳ ፈልገህ አግኘው! የጨቆንከውን ራስህን ፈልገህ አውጣው! በበቀቀንነት ጉዞ ያጣኸውን የራስህ የሆነውን ልሳን እንደምንም ብለህ አውጣው! ሌሎች የሚደሰኩሩትን ሳይሆን – አንተ ራስህ – የራስህ አዕምሮ ያፈለቀውን እንዲናገር ፍቀድለት! ለራስህ ዕድል ስጠው! ለራስህ ጊዜ ስጠው! በቀቀንነት ያብቃ! እስስትነት ያክትም! ራሳችንን እንሁን!
“ፈጣሪ ኦሪጂናል አድርጎ ፈጥሮን እያለ፣ ስለምን ሌሎችን ለመምሰል እንሻለን?”
እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር።
አበቃሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic