በምርጫ ዋዜማ መጥፎ ምልክቶች፤
ያሬድ ኃይለማርያም (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)
የአገሪቱ ፖለቲካ ምርጫ፣ ምርጫ ባይሸትም ምርጫው ሊካሄድ የታቀደበት ወቅት ጥቂት ወራቶች ናቸው የቀሩት። ከጦርነት ማግስት ላይ ስላለን ወሬያችን ሁሉ ጁንታ እገሌ ተደመሰሰ፣ ጁንታ እገሌ እጅ ሰጠ፣ ጁንታ እገሌ እጅ አልሰጥ አለ፣ ወዘተ ነው። ጠቅላላ የፖለቲካ ድባቡ አገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ ወራቶች አይደለም አመትም የቀራት አትመስልም። የሆነው ሆኑ በእነዚህ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከተከናወኑ ነገሮች ሦስቱን ብጠቅስ እንኳ ወደ ምርጫ ለሚያመራ አገር መጥፎ ምልክቶች ናቸው።
1ኛ/ ፍርድ ቤቶች አካባቢ በፖሊሶች እና በታሳሪዎች ደጋፊዎች መካከል የሚታየው ውጥረት፤ ቀደም ሲል የእስክንድር ነጋን፤ ከዛም የጅዋር መሐመድን የፍርድ ሂደት ሊከታተሉ ወደ ችሎት ያቀኑ ደጋፊዎቻቸው በፖሊስ እስር እና መጉላላት ደርሶባቸዋል። በተለይም ቢጫ ልብስ ለብሰብ ድጋፋቸውን እና ተቃውሟቸውን ለማሳየት በጅዋር የፍርድ ሂደት ወቅት ፍርድ ቤት የተገኙ ወደ 80 የሚጠጉ ሰዎች ተይዘው በእስር ከቆዩ በኋላ በፍርድ ቤት ውሳኔ ተለቀዋል። የእነዚህ እስረኞች ደጋቺዎች የችሎቱን ሥራ እስካላስተጓጎሉ እና የፍርድ ቤቱን ሥርዓት እስካላወኩ ድረስ ያሻቸውን ለብሰው ፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ በመገኘት ለታሳሪዎቹ ድጋፍ ቢሰጡ ችግሩ ምን ላይ እንደሆነ አይገባኝም። ይህን በማድረጋቸውም የሚተላለፉት ወይም የሚጥሱት ሕግ የለም። ዛሬ ፍርድ ቤቱ እንዲለቀቁ ሲወስንም ያነሳው ጥያቄ ‘ተሰብሳቢዎቹ እረብሻ ፈጽመዋል ወይ?’ የሚል ነበር። የፖሊስ መልስ አልረበሹም ግን ቢጫ ልብስ ለብሰው ነበር የሚል ነው።
2ኛ/ ባልደራስ የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ የአዲስ አበባ መስተዳደር ግልጽ ባልሆነ ምክንያት እንዳይካሄድ ማድረጉ ሌላ በምርጫ ዋዜማ የታየ መጥፎ ምልክት ነው። ይህ እርምጃ የዜጎችን ሃሳብን በአደባባይ በነጻነት የመግለጽ እና በአደባባይ የመሰብሰብ መብትን የሚጥስ እርምጃ ነው። መንግስትን የሚደግፉ ሰልፎች በየጊዜው ያለምንም ችግር እና መሰናክል እንዲካሄዱ እየተደረገ ተቃዋሚዎች የሚጠሩዋቸው ሰላማዊ ሰልፎች፣ ስብሰባዎች እና ጋዜጣዊ መግለጫዎች በተደጋጋሚ መከልከላቸው የምርጫዊን ሂደት ላይ ከወዲሁ ጥላ ያጠላበታል።
3ኛ/ በቅርቡ አቶ ልደቱ እና አቶ ይልቃል የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት የራሳቸውን አረዳድ እና ምልከታ ለአንድ ሚዲያ ማካፈላቸውን ተከትሎ ከሹም እስከ ደቂቅ ድረስ ዛቻ፣ ስድብ እና ማጠልሸት ሲካሄድባቸው ማየት የቅድመ ምርጫውን ወቅት አስፈሪ እና የሃሳብ ልዩነቶችን የሚያስተናግድ የፖለቲካ ምህዳር ገና አለመፈጠሩን ያመላክታል። የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ሆኑ ዜጎች በመሰላቸው ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን በነጻነት የማንጸባረቅ ሕገ መንግስታዊ መብት አላቸው። በተለይም የፓርቲ መሪዎች የመንግስትን ፖሊሲዎች፣ አፈጻጸሞች፣ አገርን በሚመለከቱ ክስተቶች እና የተለያዩ ጉዳዮች ላይ በነጻነት ሃሳባቸውን የማራመድ እና ለሕዝብ ይፋ የማድረግ መብት አላቸው። እስከ አሁን በእነዚህ ሰዎች ላይ ከስም ማጥፋት እና ስብዕናቸውን ለማንቋሸሽ ከመሞከር በዘለቀ እነሱ ባነሷቸው ነጥቦች ላይ አንድ በአንድ ምክንያታዊ መልስ ወይም የመሟገቻ ሃሳብ የሰጠ ሰው አላየሁም። ብዙዎች ስድብ፣ እርግማን እና ዛቻ ነው ያዘነቡባቸው። ሁለቱም ግለሰቦች ከገለጹዋቸው በርካታ ሃሳቦቻቸው ጋር ባልስማማም ከተናገሯቸው ነገሮች መካከል ደምጥጠን ልናልፋቸው የማንችል እውነቶችንም ተጋግረዋል። ሃሳብን እያነጠፉ እና ሃሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹ ግለሰቦችን እያሸማቀቁ ፍትሐዊ ምርጫ ማሰብ ይከብዳል። የማንወደው ነገር ሲነገር መብታችን አለማዳመጥ ወይም ሃሳቡን በሃሳብ መተቸት እንጂ ተናጋሪዎቹ ላይ ኢላማ ያደረገ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ እና የጁንታ ደጋፊናቸው ይታሰሩልን እያሉ ማንቋረርን አይጨምርም።
ግን ፖለቲካችን ምርጫ ምርጫ ሳይሸት ምርጫው ሊካሄድ ነው? የምርጫ ውይይቶች አይታዩም። ብልጽግና እና ኢዜማ ጭልጭል የሚሉ ቅስቀሳዎች ሲያካሂዱ ይስተዋላል፤ ግን በቂ አይደለም። የሲቪክ ማህበራትም በምርጫ ዙሪያ ሲንቀሳቀሱ አይስተዋልም። ነው ወይስ ምርጫው …?