>

700 ሰአታት በአየር ላይ ስለ ኢትዮጵያ  ከአገር አገር የበረሩትን ትልቅ ሰው  ለማሳነስ መውተርተሩ ትዝብት ላይ ይጥላችሗል ...!!! (ጸጋው ማሞ)

700 ሰአታት በአየር ላይ ስለ ኢትዮጵያ  ከአገር አገር የበረሩትን ትልቅ ሰው  ለማሳነስ መውተርተሩ ትዝብት ላይ ይጥላችሗል …!!!
ጸጋው ማሞ

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መሥራያቤታቸውን የለቀቁ ሰሞን በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ እንዲህ ብለው ነበር… “ኢትዮጵያ አገራችን ካሏት በአገር ፍቅር ስሜት ከታነፁ አንጋፋ ተቋማት መካከል አንዱ በሆነውና እነ አክሊሉ ሃብተወልድና ከተማ ይፍሩ የመሳሰሉ አገር ወዳዶችና ስመ ጥር መሪዎችን ባፈራው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመድቤ አገሬን በፍቅር በማገልገሌ ሁልጊዜም ኩራት ይሰማኛል።” እሳቸው አክሊሉ ሃብተወልድን አገር ወዳድ ብለው ሲገልጿቸው እዛው ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ያሉት ድኩማኖች ደግሞ ጭቃ ሊቀቧቸው ሊያሳንሷቸው ሲውተረተሩ ስናይ አይ ኢትዮጵያዬ ማን ይሆን ሰው አይብቀልብሽ ብሎ የረገመሽ? ያሰኛል።  ግን ለምን ይሆን? ትልልቆቹ አንሰው ካልታዩ እኛ የማንታይ የሚመስለን???
 
*    *    *
ገድለ አክሊሉ ሀብተወልድ
  የአክሊሉ ጥፋት ኢትዮጵያ  ውስጥ መፈጠሩ ነው ። እሺ ሌላ ምን ይባላል ? በየትኛው ችሎት ማን ጠበቃ ይሆነዋል?  ይኸን ብንደፍርስ ? ጠ/ር አክሊሉ ሀብተወልድ ባይኖር  ኖሮ የአሁኗ ኤርትራም ሆነች ጠ/ር ዐብይ አህመድ ከነ ብልፅግና ፓርቲያቸው አይኖሩም ነበር ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣የኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት ፣ የወንጀለኛና የፍታብሔር ሕጎች ፣ የውጭ ፖሊሲዎቻችን እና ሌሎችም ተቋማት በነ ጆርጅና ሄነሪ እየተመሩ የባርነት ስነ ልቦና ጌጣችን ይሆን ነበር ።
 ————
  ”  እናትና ወንድሜን ግደሏቸው እንጅ ኢትዮጵያን አልክድም ” በማለት ከዲፖሎማሲ ተጋድሎ ባሻገር   ለኢትዮጵያ በገቢር ሊሞት ወደ ጎሬ ከአርበኞች ጋር ሊቀላቀል የወሰነና ከድል በኋላ ብቻውን ያለ ጸሐፊ  ኢትዮጵያን ከጠላት የተከላከለ ዓለም አቀፍ ጀግና ነው ። ይኸን መካድ እንዴት ሰውነት ይቻለዋል?
  አክሊሉ ሀብተወልድ ከሰሯቸው በጥቂቱ
  
— ግብፅንና የመንን አርፉችሁ ካልተቀመጣችሁ ጦር እናዘምትባችኋለን በማለት አርፈው እንዲቀመጡ አስጠንቅቋል  ።
-ራሽያን  በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ  ስለ ኢትዮጵያ ክብር አዋርዷታል ።
-ፈረንሳይን ቅኝ የተገዛችሁ ስለሆናችው ስለ ነጻነት አታወሩም በማለት በአደባባይ ስለ ኢትዮጵያ ክብር ንቋታል ።
-እንግሊዞችን ፈትኖአቸዋል
-የአሜሪካን መሪዎች እቅድ  በተደጋጋሚ አስቀይሮአል ።
– በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ላይ የዓለምን መንግስታት   በማስደነቅ ቁጭ ብድግ አስድርጓል ።
-አረቦችን ፣ላቲን አሜሪካኖችን ፣አውሮፓዎችን   ባየር እና በመርከብ እየበረረ  ከኢትዮጵያ  ጎን እንዲሰለፋ በብሩህ አእምሮው አሳምኖአቸዋል ።
——-
700 ሰአታት በአየር ላይ…!
– 700 ሰአታት በአየር ላይ ስለ ኢትዮጵያ በሯል ።
– ገና በ19 ዓመቱ ኢትዮጵያን በተባበሩት መንግስታት ላይ ወክሎአታል ።
– እየታመመ በዶክተሮች እየተጠበቀ ስለ ኢትዮጵያ ጥቅም ተሟግቷል ።
– የኢትዮጵያን አየር መንገድ ፣ ንግድ ባንክ  በራሳችን ልጆች  እንዲዘወሩ መሥርቷል ።
-የኢትዮጵያን ሕገ መንግስት ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ፣ የፍታብሔር ፣የንግድ  ፣ የባህር ህጎችን አስረቅቆአል…
– የአፍሪካ ህብረት አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን ሀሳቡን ከማመንጨት ጀምሮ ታግሎአል ።
– ጣሊያኖችን በአውሮፓ ምድር እረፍት ሲነሳቸው  ትልልቅ ማባበያ ቢሰጡት አልፈልግም ሲላቸው   እናትና ወንድምህን እንገድልብሀለን ሲሉት ከብዙሀን እናት ኢትዮጵያ አይበልጡም ብሎ መልስ   ሰጥቷቸዋል።
–ጋምቤላ ፣ኦጋዴን ፣አፋምቦን የኢትዮጵያ ግዛት ሆነው ይቀጥሉ ዘንድ ካለ እንቅልፍ በአየር እየበረረ በባህር እየተጓዘ የእንግሊዞችን ሴራ የበጣጠሰ የጭንቅ ቀን ልጅ መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል
-በአለም ህዝቦች ፊት ። ስለ ኤርትራ ብቻውን የቆመና በድል ያጠናቀቀ የምንግዜም ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት ነው ።
— በተባበሩት መንግስታት ፊት ተናገረ “እኛ መቼም ወገን የሌለን ትንሽ ሀገር ነን የምንጠብቀው ፍትህ ነው ” አያለ የጮኸ ።
— አክሊሉ ምንም  ቢሳቢስቲ ንብረት የሌለው ሚኒስቴር ነበር  እንደውም ሚስቱ በጠና ስትታመምበት  ለህክምና ብር በማጣቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 600ብር ተበድሮ  ከደሞዙ ላይ በየወሩ እየተቀነሰ  ከፍሎአል…
 –አክሊሉ ሀብተወልድን ለየት የሚያደርገው በሀገር ጉዳይ    ቁፍጥን ፣ምርር ፣ድርቅ ፣ጅግን ፣ፅንት የሚያደርገው  በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ለድርድር የማይቀመጥ ኩሩ መሆኑ ነው ።
 – ምን ዋጋ አለው ልጅነቱን የሰጣት ሀገሩ ግን ለውለታው ሽልማት  የግፍ  እና አጉል አሟሟትን ሸለመችው… ይህም ሳያንሰው ገድሉ  ለትውልድ እንዳይነገር  የሰራቸውን  ድንቅ ስራዎች ሳይቀር የውጭ ጉዳያችን በአርካይቭ ውስጥ  ደበቀው ።
–እባክህን  የውጭ ጉዳይ ጽፈት ቤት ከሺ ገጽ  በላይ የሚሆነውን የአክሊሉን  ገድል ስለ ሀገር  የከተበውን  የእጅ ጽሁፍ  አውጡልንና ጀግና እንፍጠር ?
–የኢትዮጵያ አየር መንገድ  ሃውልት ሊያቆምለት ይገባል !
– የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ቅርንጫፍ በስሙ ሊሰይምለት  ይገባል !
– የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሃውልት ሊያቆምለት ይገባል !
– በስሙ መንገድ ወይም ተቋም ሊሰየምለት ይገባል!
       ግን እኛ ምንድነው የሆንነው?  ምን  አይነት እርግማን ነው የተጠናወተን?  
          
ትልቅ ሥራ አበርክተው የሄዱትን የኢትዮጵያ መሪዎች ከሆነ ብሔር ናቸው ብለው ጥቂቶች ስለሚያምኑ ሊያሳንሷቸው ሲሞክሩ አያለሁ። ይሄ ድርጊት ስርም እየሰደደ ነው። ለምን እንደሚደረግም ግልፅ ነው። አንድን ብሔር ታሪክ አልባ አርጎ አንገት ለማስደፋት ሆን ተብሎ የተፀነሰ ሴራ ነው። አይ አለማወቅ። ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ከሀገርም አልፈው በአለም ደረጃም በሥራቸው የታወቁ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር እንደነበሩ ስለማያውቁ ነው። እሳቸው እኮ አንዱን ከሌላው የማያበልጡ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።
ኢትዮጵያ እንደማንኛውም አገር ታሪክ አላት። ታሪክ ተሰርቶ የተቀመጠ የቆየ ስራ ነው። ማየት እንጂ መቀየር የማንችለው። ሲያሻን ለእኛ ጥቅም ብለን ወደኅላ ሄደን ምናስተካክለው አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የማይሞከር ነገር ስለሌለ ወደ ኅላ ሄደን የተሠራውን ሁሉ እኛ በምንፈልገው መልክ ለማስቀመጥ ሙከራ እያደርግን ነው። ወደፊት እንደመሄድ ወደኅላን ምን አመጣው?
ጥላቻ ከሁሉም በላይ እራስን ነው የሚጎዳው። ለሀገር የመሥራት  አጋጣሚ ስታገኙ እባካችሁ ተጠቀሙበት። እናንተም ወደፊት ስማችሁ በጥሩ ሊነሳ ይችላል። ባሉበት ጊዜ ከተቻለ የበለጠ ሠርቶ ማለፍ ነው እንጂ ያለፉትን ታላላቅ የኢትዮጵያን ልጆች መንካት የራስን ጉድለት በአደባባይ ማሳየት መሆኑን ማን በነገራችሁ። እኔም ሆነ ሌላው የሚታየን ይሄው ነው።
እስቲ እንደ ምታሟቸው አባቶቻችን እስከ ዛሬ ድረስ ወደር የሌላቸውን እንደ እነ ኢትዮጵያ አየር መንገድን; አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ; የአፍሪካ ህብረት; ወዘተ የመሳሰሉትን ለመሥራትና እነሱ እንዳደርጉት እናንተም ለሚቀጥለው ትውልድ ለማበርከት ሞክሩ። እንደ አባቶቻችን አያቶቻችን እና ቅድመ አያቶቻችን በሥራ እንጂ በንግግር ግዚያችሁን አትጨርሱት። የኢትዮጵያ ህዝብ ከናንተ የሚጠብቀው የጎደለውን እንድታሟሉለት እንጂ ወደኅላ ሄዳችሁ ታሪክን እንድትቀይሩለት አይደለም።
Filed in: Amharic